11 ክስ ቀርቦባቸው የነበሩት የፖሊስ አባል የዋስትና መብት ተከለከሉ

0
570

በከባድ ሰብኣዊ መብት ጥሰት እና ሥልጣንን አለአግባብ በመጠቀም 11 ክስ ቀርቦባቸው የነበሩት የቀድሞ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዋና አባል ሳጅን እቴነሽ አረፈአይኔ የዋስትና መብት ተከለከሉ።

ሳጅን እቴነሽ ላለፉት ሦስት ወራት በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን ተከሳሽዋ ከዚህ ቀደም በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ወደ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ (ማዕከላዊ) የሚገቡ የአርበኞች ግንቦት 7፣ ኦነግና ሌሎች ድርጅቶች አባላትን ሰብኣዊ መብት በመጣስ የተለያዩ ጉዳቶችን በዋና ወንጀል አድራጊነትና በአባሪነት መፈጸማቸውን የተመሠረተው ክስ ያስረዳል። ተከሳሽዋ በተለይም ምርመራ የሚከናወንባቸው የተለያዩ ግለሰቦችን እስኪብርቶ በአፍንጫቸው ውስጥ በመክተት፣ ብልት በፒንሳ በመጎተት፣ ሽንት በመሽናትና በስቴፕለር በመምታት የተለያዩ ዓይነት የመብት ጥሰቶችን መፈጸማቸውን የዐቃቤ ሕግ ክስ ያመላክታል። በተጨማሪም ተጠርጣሪዋ ምንም ዓይነት ሥልጣንና ኃላፊነት ሳይኖራቸው የተለያዩ ተጠርጣሪዎችን በሌሊት ከታሰሩበት በማስወጣት የመብት ጥሰቶችን እንደፈጸሙባቸው፥ በዚህም ሥልጣንን ያላግባብ በመጠቀም የተለያዩ ጉዳቶችን ማድረሳቸውንም ክሱ አትቷል። በዚህም የአካል ጉዳት በእስረኛ ተጠርጣሪዎች ላይ እንዲደርስና የሥነ ልቦና ቀውስ ውስጥ እንዲገቡ አድርገዋል ብሏል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ማክሰኞ፣ የካቲት 5 ባቀረበው አቤቱታ ተከሳሿ ከቀረቡባቸው 11 ክሶች ውስጥ በተለይም በ1ኛ እና በ2ኛ ክስ ላይ ሥልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም የሙስና ወንጀል ከ10 ዓመት በላይ የሚያስቀጡ በመሆናቸው የተከሳሽ ዋስትና መብት እንዲከለከል ለፍርድ ቤቱ የገለፅ ሲሆን፤ ተከሳሿ በበኩላቸው የዋስ መብታቸው ተከብሮ ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉና ላለፉት 3 ወራት ሕፃን ልጅ ይዘው በማረሚያ ቤት መቆየት አዳጋች ስለሚሆንባቸው የዋሰትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ጠይቀዋል።

ተከሳሿ ሰብኣዊ መብታቸውን በሚነካ መልኩ በተለያዩ ሚዲያዎች ሥማቸው እየጠፋ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አቤቱታቸውን አቅርበዋል። አያይዘውም በእስር ላይ ልዩ ጥንቃቄ እንዲደረግላቸውና በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ማረሚያ ቤት ውስጥ እንዲቆዩ ጥያቄ አቅርበውዋል።

ፍርድ ቤቱ ተከሳሿ የተከሰሱበት ሥልጣንን ያለአግባብ መገልገልና ሙስና ወንጀል የዋስትና መብት የሚያስከለክል በመሆኑ ተከሳሿ ጉዳያቸውን በአዲስ አበባ ማረሚያ ሆነው እንዲከታተሉ እና የክስ መቃወሚያ እንዲያቀርቡ ለየካቲት 13 ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 14 የካቲት 9 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here