ከጥቂት ወራት በፊት በ3 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ወደ ግል ይዞታ እንዲዘዋወር ወሳኔ ተሰጥቶበት የነበረው ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ የባለቤትነት ጉዳይ የማወዛገቡ ጉዳይ እልባት አለማግኘቱን ተከትሎ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግዢው ሒደት እንዳይቀጥል የእግድ ትዕዛዝ አስተላለፈ።
በትውልድ ኤርትራዊ በዜግነት አሜሪካዊ የሆኑት ብርሃኔ ገብረመድህን ፋብሪካውን የባለቤትነት ጥያቄ ማንሳታቸውን ተከትሎ፤ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ኤጀንሲ ፋብሪካውን ወደ ግል ይዞታ ለማዘዋወር የሚያደረገውን እንቅስቃሴ እንዲያቆም በፍርድ ቤት የታዘዘ ሲሆን የጨረታው ቀጣይ ሒደቶች እንዳይካሔዱ ፍርድ ቤቱ እግድ ጥሏል። ኤጀንሲው እግዱን በመቃወም ቅሬታ ቢያቀርብም የካቲት 8 ፍርድ ቤቱ በዋለው ችሎት እግዱ እንዲፀና ወስኗል፡፡
ይሁን እንጂ በንብረቱ ላይ ጨረታ ወጥቶ አሸናፊ መለየቱንና ከገዢው ድርጅት (ሎሚናት መጠጥ ፋብሪካ) ጋር ውል ለመፈራረም ዝግጅት ላይ መሆኑን ኤጀንሲ መግለፁን ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ፤ ወሳኔው ከእግድ ትዕዛዝ በፊት የተከናወኑ ተግባራትን የመሰረዝ ውጤት እንደማይኖረው ገልጿል።
የቀድሞ ኤሊያስ ፓፓሲኖስ መጠጥ ፋብሪካ አሁኑ ብሔራዊ አልኮል በመባል የሚታወቀው ከዛሬ 106 ዓመታት በፊት የተመሰረተ ሲሆን እስከ 1969 ድረስ ከቀድሞ የድርጀቱ ባለቤት በገዙት ብርሃኔ ባለቤትነት ሥር ሆኖ ይተዳደር ነበር። በተጨማሪም አቃቂ እና ሰበታ የሚገኙት የአልኮል ፋብሪካዎችን ጨምሮ በቀድሞ የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ዋና ፀሀፊ ፍቅረስላሴ ወግደረስ ትዕዛዝ በመንግሥት በ1969 እንዲወረስ ተድርጎ ነበረ።
በ1983 የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ በአፈቀላጤ የተወረሱ ንብረቶች በባለቤቶቻቸው እንዲመለሱ ፓርላማ ሕግ ካፀደቀ በኋላ ብርሃኔ ድርጅቱ እንዲመለስላቸው ጥያቄ አቅርበው ነበር። ይህንን ተከትሎ በ1990 በቀድሞ የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ቦርድ ሊቀ መንበር በነበሩት ከዚያም በሙስና ጥፋተኛ ተብለው ሰባት ዓመት በእስር በነበሩት አሰፋ አብረሃ እና ሌሎች የቦርድ አባላት ትዕዛዝ የአልኮል ፋብሪካውን 26 ሚሊየን ብር ከፍለው አልያም አቅሙ ከሌላቸው ካሳ እንዲከፈላቸው አዞ ነበር።
ይሁን እንጂ በ1991 በኢትዮጵያና ኤርትራ መንግሥታት የተፈጠረውን ጦርነት ተከትሎ የቀድሞ ባለቤቱ ከአገር እንዲወጡ በመደረጋቸው ኹለቱንም ማድረግ አልቻሉም ነበር። ከዚያም በ2001 ወደ ኢትዮጵያ አንዲገቡ ከተፈቀደላቸው በኋላ ግለሰቡ ድርጅቱ ይመለስልኝ የሚለውን ጥያቄ አቅርበው፤ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር ካሳ እንዲከፍላቸው ቢወስንም ሳይቀበሉት ቀርተዋል።
ይህንንም ተከትሎ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝ የፕራይቬታይዜሽን ሰብሳቢ በነበሩት ወቅት በ2002 በፃፉት ደብዳቤ የቀድሞ ባለቤቱ የካሳ እንዲከፈላቸው የማይቀበሉ ካልሆነ በስተቀር የድርጅቱ ይመለስልኝ ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጎት ነበር። ከሦስት ዓመታት በኋላ የቀድሞ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መኮንን ማንያዘዋል በሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት በፃፉት ደብዳቤ ባለቤቱ ለተወረሰባቸው ንብረት መንግሥት በሕጉ መሰረት ተገቢው ካሳ እንዲከፈላቸው ከሰጠው ውሳኔ የተለየ አቋም መሥሪያ ቤታቸው እንደሌለው ገልፀው ነበር።
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል የሆኑት ዳና ሮህባቼር ፋብሪካው ለብርሃኔ እንዲመለስላቸው የሚጠይቅ ደብዳቤ ለመንግሥት ልከው ነበር። ይሁን እንጂ በመንግሥት የተወሰነ ምንም ዓይነት የውሳኔ ለውጥ የለም።
በተጨማሪ የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ፋብሪካውን ለመሸጥ ጨረታ ማወጣቱን ተከትሎ በርካታ ድርጅቶች ለመግዛት ፍላጎት ቢያሳዩም፤ ከፍተኛው ገንዘብ (3 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር) ያቀረበው ሎሚናት እንዲጠቀልለው ተወስኖለት ነበር። ነገር ግን ቢኒያም ብርሃኔ እና ብሩክ ወርቁ በተባሉ ኹለት ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች የተቋቋመ ድርጅት በቅድሚያ መክፈል ያለበትን 35 በመቶ ጠቅላላ ክፍያ በሰዓቱ መፈፀም አለመቻሉ ከዚህ ቀደም በአዲስ ማለዳ መዘገቡ ይታወሳል።
ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ የአራት ፋብሪካዎች ጥምረት ሲሆን ኹለቱ በአዲስ አበባ ከተማ ሲገኙ አንዱ ፋብሪካ ደግሞ ከአዲስ አባባ በስተምዕራብ አቅጣጫ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘዉ ሰበታ ከተማ ላይ ይገኛል።
ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ወደ ግል ይዞታ ካቀዳቸዉ ድርጅቶች ዉስጥ አንዱ ሲሆን ከፍተኛ ሽያጭ እና ትርፍ በማስመዝገብ ስኬታማ እንደሆነም የሚታወቅ ነዉ። ፋብሪካዉ 42 ከመቶ የሚሆነዉን የኢትዮጵያን የአረቄ ገበያ ተቆጣጥሯል። ፋብሪካዉ በ2008 በጀት ዓመት ብቻ 475 ሚሊዮን ብር ሽያጭ ያስመዘገበ ሲሆን ትርፉም ከታክስ በፊት 132 ሚሊዮን ነበር።
ቅጽ 1 ቁጥር 14 የካቲት 9 ቀን 2011