“መንግስት ከህወሃት ጋር ተደራደር ቢባል እንኳን ‘ህዝቤ አይፈቅድልኝም’ ማለት አለበት”፦ባልደራስ

0
387

ሐሙስ ጥር 5 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) መንግስት “ከህወሃት ጋር ተደራደር ቢባል እንኳን ህዝቤ አይፈቅድልኝም” ማለት እንዳለበት ባልደራስ ለእውነት ዴሞክራሲ ፓርቲ አሰታወቀ።

ፓርቲው ከፍተኛ አመራሮቹ ከተፈቱ በኋላ የመጀመሪያውን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የፓርቲው ፕሬዝዳንት እስክንድር ነጋ መንግስት የአገርን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል ውሳኔ መወሰን እንደሌለበት ገልጸዋል።

መንግስት ከህወሃት ጋር ለመደራደር ቢቀመጥ “ህዝቤ አይፈቅድልኝም” ማለት እንዳለበትም ፓርቲው ገልጿል።

ባልደራስ አመራሮቹና አባሎቹ የተከሰሱት “በሀሰት” መሆኑን ገልጾ፤ መንግስት ይቅርታ ጠይቋቸው፤ ካሳ ሊከፍላቸው ይገባልም ሲሉም የፓርቲው ፕሬዝዳንት እስክንድር ነጋ ገልፀዋል።

“በሃሰት ተከሰው የታሰሩትን የባልደራስ አመራሮችና አባላት መንግስት ይቅርታ ሊጠይቅና ካሳ ሊከፍላቸዉ ይገባል” ሲሉም ተናግረዋል በመግለጫው፡፡

ባልደራስ ከተመሰረትኩበት ጊዜ አንስቶ ገዢዉ ፓርቲ “ብርቱ በትር ሲያሳርፍብኝ” ነበርም ማለቱን አል አይን ዘግቧል፡፡

በተጨማሪም የህወሓት የጦርነቱና የፖለቲካ ዋና ቀያሾች የሆኑ እስረኞች ከእስር መዉጣት መጀመራቸዉ የህግ የበላይነትን የጣሰ ዉሳኔ መሆኑንም ባልደራስ በመግለጫው አስታዉቋል፡፡

በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም ሊገኝ የሚችለው መንግስት ተጠያቂነትን እና ፍትህ ሲያሰፍን ብቻ ነው ያለው ፓርቲው፤ ይህ መርህ በተቃራኒ መልኩ የሚደረግ ማናቸውም ቁማር ሀገርንን እና ህዝብን መልሶ ወደ ችግር እንደሚከት አያጠያይቅም ” ብሏል።

የእነ ስብሃት ነጋ መፈታት የሕግ የበላይነትን የጣሰ መሆኑንም ባልደራስ በመግለጫው ያስታወቀ ሲሆን፤ “የባልደራስ አመራር አባላትን ጨምሮ የክስ ማቋረጥ ተግባር ሕጋዊነትን የተላበሰ መሆን እንደነበረበት እናምናለን።” ሲልም በመግለጫው አስታውቋል።

መንግስት ምዕራፍ አንድ ያለዉን ዘመቻ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሳያረጋግጥ ማቆሙ “ትልቅ አደጋ ያዘለ” መሆኑን በመግለፅም፤ “ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክሬ መታገሌን እቀጥላለሁ” ሲል ባልደራስ ገልጿል፡፡

ይደረጋል የተባለው የምክክር ሂደትን በተመለከተ ባለቤቱ ህዝብ፣ የፖለቲካ ኃይሎችና የሲቪክ ተቋማት መሆናቸውን በማስታወስም ሂደቱ ሁሉም ባለድርሻዎች በባለቤትነት እንዲመሩት ጠይቋል፡፡

የምክክሩ ቅድመ ሁኔታ የኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት መሆን አለበት ያለው ባልደራስ በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀስን ያለ ቅድመ ሁኔታ መቀበል ይገባል ሲልም ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል።

የሰሜኑ ጦርነት ህወሃት በጀመረው ቅድመ ማጥቃት መቀስቀሱን እንደሚያምንም ባልደራስ በመግለጫው አስታውቋል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here