“ሂሩት አባቷ ማን ነው?” የተሰኘው ፊልም ከ57 ዓመት በኋላ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተመርቆ ተከፍቷል፡፡
በ1957 “ሂሩት አባቷ ማን ነው?” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ባለጥቁርና ነጭ ፊልም ከ57 ዓመት በኋላ በዛሬው ዕለት በሸራተን አዲስ ለእይታ የበቃ ሲሆን በከንቲባ አዳነች አቤቤ አማካኝነት በይፋ ተመርቋል።
በምርቃቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባዋ እንደተናገሩት ይህ ፊልም በኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ከፋች ፊልም ብቻ ሳይሆን ከዚያ በኋላ ለመጡት የጥበብ ሥራዎች ሁሉ መነሻ መሆን የቻለ፤ አይን የገለጠና በርካታ የጥበብ ሰዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት የሆነ ታሪካዊ ሥራ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያም ይህንን ሥራ የጀመረችው ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ቀደም ብላ ቢሆንም በፊልሙ ኢንደስትሪ የሚፈለገውን ያህል ተጠቃሚ ሳትሆን ዛሬ ላይ ደርሳለች ብለዋል።
“ኢትዮጵያ የብዙ ባህሎችና ቋንቋዎች፤ እሴቶች አገር ስትሆን አሸባሪው ቡድን ይህንን አብሮነት ለማፍረስ ቢሞክርም አልተሳካለትም።” ሲሉም ገልፀዋል፡፡
በመሆኑም ኪነጥበብን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልፀው፤ የኪነጥበብ ስራዎቻችን የኢትዮጵያውያንን አብሮነትና አንድነት ፤የሚያጎላ ለሀገራችን የትንሳኤ ጉዞ የሚያግዝ ትልቅ አቅም መሆን አለበት በማለት መግለፃቸውን ከከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው በመክፈቻው እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በእዳ ተይዞ የነበረውን ፊልም በጥንቃቄ ይዞ በማቆየት እና ለዚህ በማብቃቱ አመስግነው፤ አሁንም ለፊልሙ ኢንደስትሪው ብድሮች እንዲመቻቹ ጥሪ አቅርበዋል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይም ይህ ሥራ ለህዝብ እንዲደርስ አስተዋፅኦ ያበረከቱ የተለያዮ ባለሙያዎች ከከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እጅ እውቅና ተበርክቶላቸዋል።
____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA








