በባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ብቻ የተቀነባበረ አልበም ገበያ ላይ ዋለ

Views: 228

‹ኃይለ ጊዜ› የተሰኘ በባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያዎች ብቻ የተቀነባበረ የሙዚቃ አልበም ዛሬ ቅዳሜ የካቲት 14/2012 ለገበያ ሊቀርብ ነው።
በመሶብ የባህል ሙዚቃ ተጫዋቾች ቡድን የተዘጋጀው አልበሙ፣ በባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ብቻ የተቀነባበረ ሲሆን 10 ሙዚቃዎችን ይዟል። ሰባት የሙዚቃ ባለሙያዎችም የተሳተፉበት ነው።
ቡድኑ ከዚህ ቀደም ‹ፅሞና› የተሰኘ አልበም በ 2008 ገበያ ላይ አውሎ እንደነበር የተናገረው የቡድኑ መሪ እና ዋሽንት ተጫዋች ጣሰው ወንድም፣ አዲሱ አልበም የሙዚቃ መሣሪያዎችን አቅም በተሻለ መልኩ ለማሳየት የተሞከረበት እንደሆነ ተናግሯል።

ፅሞና የሙዚቃ አልበም መልካም የሚባል ተቀባይነት ነበረው ያለው ጣሰው፣ መሶብ የባህል ሙዚቃ ቡድንን ያስተዋወቀ እንደነበር አስታውሷል። ከአልበሙ መውጣት በኋላ የግጥም ምሽቶችን በባህል ሙዚቃ የማጀብ ዕድል ከመፈጠሩም በላይ፣ በርካታ ሰዎችን እንድንተዋወቅ ዕድሉን የከፈተ ነበር ሲልም ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል። አዲሱ አልበም ተመሳሳይ አቀባበል ይኖረዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጣሰው ገልጿል።

በመሶብ የባህል ቡድን በወር አንድ ጊዜ የሚዘጋጀው ‹አንዲር› የተሰኘ የባህል ሙዚቃ ምሽት የአዳራሽ ችግር እንደገጠመው ጣሰው የተናገረ ሲሆን፣ አዳራሽ በማፈላለግ በቅርቡ እንደገና እንደሚጀመር የባህል ቡድኑ አስታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 68 የካቲት 14 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com