የተሟላ ዕውቅና ያላገኙ መንግሥታት

በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ በርካታ አገሮች በጊዜ ሒደት ሲሠፉ አሊያም ሲፈርሱ ኖረዋል። እንደየአገራቱ ታሪክ ሒደቱ ቢለያይም፣ አገር ሲፈርስ ትናንሽ ግዛቶች ራሳቸውን ችለው እንደአገር ለመቆየት የማያባራ ጦርነት ውስጥ ሲገቡ ቆይተዋል። ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ እንኳን ጥቂት የማይባሉ አገራት የትላልቅ አገራትን መፍረስ ተከትሎ ራሳቸውን እንደአገር ቢመሠርቱም የተወሰኑት ዕውቅናን አላገኙም። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ታደሰ ብሩ ኬርስሞ (ዶ/ር) ዕውቅና ያላገኙ መንግሥታትን ታሪክ አመጣጥ ለማሳየት የተወሰኑትን በመጥቀስ ያስከተሉትን ችግር ያትታሉ። አገር ነኝ ብሎ ማወጅም ሠላም እንደማያመጣ ምሳሌ በማስቀመጥ ችግሩ በምሥራቅ አፍሪካ እንዳይከሠት አስቀድሞ መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ በጽሑፋቸው አመላክተዋል።

በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተፈጠረው ችግር ወደየት ያመራ ይሆን የሚለው ጥያቄ የብዙ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ጭንቀት እንደሆነ እገነዘባለሁ። አሁን ያለው ችግር በጥበብ ካልተያዘ አንዱ የአገራችን አካል ዕውቅና ወደ አላገኘ መንግሥትነት (defacto state)ሊቀየር ይችላል የሚለው ሥጋት እኔም ውስጥ አለ። ይህ ጽሑፍ “ዕውቅና ያላገኘ መንግሥት” (ከዚህ በኋላ “ዕያመ” በሚል አሳጥረዋለሁ) ማለት ምን ማለት እንደሆነ፣ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት ወዲህ ምን ያህል ዕያመዎች የት የት ቦታ እንደተፈጠሩ እና ያሉበት ኹኔታ ለማሳየት፣ ብሎም ተመሳሳይ ነገር አገራችን ላይ እንዳይደደርስ ማድረግ ስለሚገቡን ነገሮችን ለማሳሰብ የተዘጋጀ አጭር ማስታወሻ ነው።

“ዕውቅና ያላገኘ መንግሥት”(ዕያመ) ምን ማለት ነው?
አንድ ግዛት ሙሉ ዕውቅና ያለው “አገር” ለመባል ቢያንስ ኹለት ነገሮች ማሟላት ይኖርበታል ተብሎ ይታመናል። የመጀመሪያው የ1933 የ‹‹ሞንቴቪዴኦ ኮንቬንሽን›› የመንግሥትነት መገለጫ ንድፈሀሳብ (declarative theory of statehood) የሚጠይቀውን መመዘኛ ማሟላት ነው። በዚህ ንድፈሀሳብ መሠረት አንድ ግዛት እንደ አገር የሕግ ሰብዕና እንዲኖረው (ሀ) ተለይቶ የታወቀ ግዛት (a defined territory)፣ (ለ) ቋሚ ሕዝብ (a permanent population)፣ (ሐ) መንግሥት (መስተዳደር) (a government)፣ እና (መ) ከሌሎች መንግሥታት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመፍጠር አቅም ሊኖረው ይገባል። ኹለተኛው፣ በሌላ የተባበሩት መንግሥታት አባል አገር ዕውቅና ያልተነፈገው ሊሆን ይገባል።

በሌላ አገላለጽ፣ ዕያመዎች በአብዛኛው ድንበራቸው ተለይቶ የማይታወቅ፣ “የእናት አገራቸው” (parent state) ዕውቅና የተነፈጋቸው፣ በአብዛኛው በእናት አገራቸው ባላንጣ አገሮች አይዞህ ባይነት ወይም ደጋፊነት (patron staes) የቆሙ፣ መንግሥት የመሠለ ተቋም ቢኖራቸውም ሌሎች አገሮች “አዎን መንግሥት ናችሁና ከእናነት ጋር በአቻነት እንደራደራለን” ያላሏቸው፣ ራሳቸውን “አገር ነን” ብለው የአገር ምልክቶች ቢኖራቸውም ሌሎች “አዎን አገር ናችሁ” ያላሏቸው ግዛቶች ናቸው። በአሁኑ ሰዓት ከደርዘን በላይ ሙሉ ዕውቅና የሌላቸው ራሳቸውን “አገር” ብለው የሚጠሩ ዕያመዎች አሉ። ለዚህ ጽሑፍ ግን ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት(ማለትም እአአ ከ1990) ወዲህ የተፈጠሩትን ብቻ ለይተን እናወጣለን።

የደቡብ ኦሴቴ ሪፑብሊክ (Republic of South Ossetia)
ደቡብ ኦሴቴ በቀድሞ ሶቭየት ኅብረት ደቡብ ካውካሰስ ግዛት የምትገኝ ራስገዝ ዞን (ኦብላስት) ነበረች። ሶቭየት ኅብረት ስትፈርስ ጆርጂያ ግዛቴ ናት ብትልም፣ ደቡብ ኦሴቴ ግን “አገር ነኝ” በማለት እአአ በ1991 ነፃነትዋን አወጀች። በደቡብ ኦሴቴ ምክንያት በሩሲያ እና በጆርጂያ፣ እንዲሁም በኦሴቴና በጆርጂያ መካከል ለዓመታት የዘለቀ ጦርነት ተካሂዷል፤ የበርካቶች ሕይወት ተቀጥፏል፤ ንብረት ወድሟል። ከ193 የተባበሩት መንግሥታት አገሮች ውስጥ አምስቱ ዕውቅና ሰጥተዋታል፤ እነዚህም ሶሪያ፣ ሩሲያ፣ ቬኔዙዌላ፣ ኒኳራጓ እና ናኡሩ ናቸው። ከእነዚህ አምስት በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት አባል ያልሆኑ አራት ዕያመዎች ዕውቅና ሰጥተዋታል፤ እነሱም አብሃዚያ፣ አርሳክ፣ ትራንስኒስትራ እና ሰሃራዊ አረብ ዲሞክራሲያዊት ሪፑብሊክ ናቸው። “አገሪቷ” 53,000 ሕዝብ እንዳላት ይገመታል። ከዚህ ውስጥም 30,000 የሚሆነው በዋና ከተማዋ ትሽንቫሊ (Tskhinvali) ነዋሪ ነው። እውቅና ከሠጧት አምስት አገሮች ውጭ ሌሎች አገሮች የሚያውቋት የጆርጂያ አካል መሆኗን ነው። ደቡብ ኦሴቴ ነፃነትዋን ስላወጀት ቅራኔው እልባት አላገኘም፤ ችግሩ አሁንም እንደቀጠለ ነው።

የአብሃዚያ ሪፑብሊክ (Republic of Abkhazia
አብሃዚያ 250 000 ያህል ሕዝብ ያላት ሩሲያና ጆርጂያ የተዋጉባት ግዛት ነች። በ1999 አብሃዚያ ነፃ አገርነቷን አወጀች። ሆኖም እስካሁን ዕውቅና የሠጧት ስድስት የተባበሩ መንግሥታት አባል አገሮች ናቸው። እነሱም ሩሲያ፣ ቬንዚዌላ፣ ኒኳራጓ፣ ናኡሩ፣ ሶርያ እና ቫንኑአቱ ናችው። የተቀሩት የተባበሩት መንግሥታት አገሮች አብሃዚያ የጆርጂያ አካል እንደሆነች ነው የሚያውቁት። ጆርጂያ ቢሮውን ከአብሃዚያ ውጭ ያደረገ “የአብሃዚያ አስተዳደር” አላት። በሌላ በኩል ግን፣ ራሳቸው ዕያመ የሆኑ ደቡብ ኦሴቴ፣ አርትሳክ (ኖጎርኖ ካራባኽ) እና ትራንሲኒስትሪያ ዕውቅና ሰጥተዋታል። በአብሃዚያ ምክንያት የአብሃዚያ፣ የኦሴቴ፣ የጆርጂያና የሩሲያ ነገዶች ተዋግተዋል፤ ሞተዋል፤ በብዙ መቶ ሺሕዎች ተፈናቅለዋል። የአብሃዚያ ሪፑብሊክ ነፃነት ማወጅ ቅራኔውን አልፈታውም።

የአርትሳክ ሪፑብሊክ (Republic of Artsakh)
አርትሳክ “ናጎርኖ ካራቫኽ” በሚለው ስሟ ይበልጥ ትታወቃለች። 200 ሺሕ ያህል ሕዝብ እንዳላት ይገመታል። ኹሉም የዓለም አገራት የሚያውቋት የአዘርባጃን አካል እንደሆነች ነው። እሷ ግን እአ አ በ1991 ነፃ አገር መሆንዋን አውጃለች። እስካሁን ዕውቅና የሠጣት አንድም የተባበሩት መንግሥታት አገር የሌለ ቢሆንም፣ ሦስት ዕያመዎች ራሳቸው አገር ባይሆኑም የአገርነት ዕውቅና ሠጥተዋታል። እነዚህም አብሃዚያ፣ ደቡብ ኦሴቲያ እና ትራንስኒስትራ ናቸው። አርትሳክ (ናጎርኖ ካራባኽ) ከአብሃዚያ ጋር በገባችበት ጦርነት የበርካታ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። በመቶ ሺሕዎች የሚገመቱ ቤተሰቦች ተፈናቅለዋል። እአአ 1994 የተኩስ አቁም ሥምምነት ቢደረግም ቅራኔው እስካሁን አልተቋጨም።

ፕሪድኔስትሮቫ ሞልዶቭያን ሪፑብሊክ (Pridnestrovian Moldavian Republic)
ይህች ትራንስኒስትራ (Transnistria) የምትባለው የሞልዶቪያ ሪፑብሊክ (Republic of Moldova) አካል ናት። የቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ስትፈርስ ሞልዶቫ ከሩማኒያ ጋር ትዋሀዳለች የሚል ግምት ነበር። የትራንስኒስትራ ፓለቲከኞች ከሩማኒያ ጋር መዋሀድም ሆነ ከሞልዳቪያ ጋር ነፃ አገር መሆን አልፈለጉም። በዚህም ምክንያት ፕሪድኔስትሮቫ፣ ሞልዶቫ፣ ሩማኒያ እና ሩሲያ ግጭት ውስጥ ገቡ። በ1991 ግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ፕሪድኔስትሮቫ የራሷን ነፃ አገርነት አወጀት። እስካሁን አንድም በአገርነት ዕውቅና የሠጣት የተባበሩት መንግሥታት አባል አገር የለም። ሆኖም 3 ዕያመዎች (አብሃዚያ፣ አርትሳክ እና ደቡብ ኦሴቲያ) ዕውቅና ሠጥተዋታል። ፕሪድኔስትሮቫም ነፃ አገር ነኝ በማለቷ ግጭቱ ዕልባት አላገኘም።

ሶማሊላንድ ሪፑብሊክ (Republic of Somaliland)
ጎረቤታችን ሶማሊላንድ 3.6 ሚሊዮን ሕዝብ አላት። ኹሉም የተባበሩት መንግሥታት አገሮች የሚያውቋት የሶማሊያ አካል መሆኗን ነው። እስካሁን ዕውቅና የሠጣት አገር ሆነ ዕያመ የለም። ሆኖም ግን ከብዙ አገሮች ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነት አላት። ሶማሊላንድ የብሪታኒያ ቅኝ አገዛዝ እና በሶማሊያ የተፈጠረው የእርስበርስ ግጭት ውጤት ናት። ሶማሊላንድ ከሌሎች ዕያመዎች በብዙ መንገዶች ትለያች – (ሀ) እናት ሀገሯ (parent state) ሶማሊያ ደካማ ናት፤ (ለ) የጎረቤት ባላንጣ የላትም፤ (ሐ) ከሞላ ጎደል ራሷን ችላ የቆመች ደጋፊ አገር (patron state) የማትፈልግ ናት። ይሁን እንጂ፣ ሶማሊያ ስትጠናከር የሶማሊላንድ ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን መተንበይ አይቻልም።

ከላይ ከተዘረዘሩት 5 ዕያመዎች ውስጥ 4ቱ የቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት መፍረስ ውጤት ናቸው። ከቀዝቃዛው ጦርነት አልፈን ወደኋላ ከሄድን ጥቂት ተጨማሪ ዕያመዎችን – ለምሳሌ፣ ታይዋን (Republic of China)፣ ሰሃራዊ አረብ ሪፑብሊክ (Sahrawi Arab Democratic Republic)፣ ሰሜን ቆጽሮስ (Turkish Republic of Northern Cyprus) – መጨመር እንችላለን።

2. ከእነዚህ ዕያመዎች ምን መማር ይቻላል?
እያንዳንዱ ቅራኔ ልዩ እንደሆነ ኹሉ፣ እያንዳንዱ ዕያመ የራሱ የተለየ ታሪክ አለው። ይሁን እንጂ የጋራ የሆኑ ጥቂት ባህሪያትንም ማውጣት ይቻላል። እኔ የሚከተሉትን ነጥቦች ለውይይት መነሻነት አቀርባለሁ።
ኹሉም ዕያመዎች የቅራኔ ውጤት ናቸው – ኹሉም ወደ ዕያመ ያመሩ ቅራኔዎች ምንጭ ዘር፣ ድንበር እና የታሪክ አረዳድ ልዩነቶች ናቸው። ዕያመዎች የዘር ፓለቲካ አስከፊነት ማሳያዎች ናቸው።

ዕያመዎች ወታደራዊ ጡንቻው ባፈረጠመ እና የአሸናፊነት ስሜት በተሰማው የዘር ፓለቲካ አራማጅ አካል በሚወሠን ውሳኔ (ዐዋጅ) የተቋቋሙ ናቸው፤ ሆኖም ከተመሠረቱ ኹለት አስርት ዓመታት በኋላ እንኳን መረጋጋት አልቻሉም፤ ቅራኔዎችን ማፈን እንጂ ማርገብ አልቻሉም።
ከሶማሊላንድ በስተቀር (ሶማሊላንድም በአንፃራዊ መንገድ ነው) ራሱን ችሎ የቆመ ዕያመ የለም፤ ሁሌ ደጋፊ (patron) ይፈልጋሉ። በዚህም ምክንያት ለውጭ ጣልቃ ገብነት ሠፊ በር ይከፍታሉ።

ዕያመዎች የኃያላን አገሮች የመሣሪያ፣ የመድኃኒት፣ የቴክኖሎጂ መሞከሪያ፤ የተዘረፈ ንብረት “ማጠቢያ”፤ የአደገኛ ቁሻሻዎች ማራገፊያዎች ናቸው።
ዕያመዎች ለሽብር እንቅስቃሴ እና ለተደራጀ ውንብድና ምቹ ናቸው፤ የዓለም አቀፍ ወንጀሎች መናኽሪያ ናቸው።

አንድ አገር ሲፈርስ ከአንድ በላይ ዕያመ የመውጣት ዕድሉ ከፍተኛ ነው። ዕያመዎች እርስ በርሳቸው እውቅና በመሠጣጠት ሕግ አልባነትን በማባዛት ለዓለም አቀፍ ሥርዓት አደጋ ይሆናሉ።

3. ምን ይደረግ?
ዕያመ ከተፈጠረ በኋላ ተጨማሪ ችግሮችን መፈልፈሉ አይቀርም፤ አንዴ መኖሩን ያሳወቀ ዕያመ በቀላሉ አይጠፋም። ስለሆነም፣ መከላከል የሚያዋጣው ከመፈጠሩ በፊት ነው። ቅራኔዎች ተካረው ወደ ዕያመ ከማምራታቸው በፊት መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል።
የዕያመ መፈጠርን እንደ ቀላል ክስተት ፈጽሞ ልናየው አይገባም። የአፍሪቃ ቀንድ ተጨማሪ ዕያመ መሸከም አትችልም። በአፍሪቃ ቀንድ አንድ ተጨማሪ ዕያመ እንዲፈጠር ከተፈቀደ ዕያመዎች እርስ በርስ በመደጋገፍ በቀጠናው በርካታ ዕያመዎች መፈጠራቸው እና መላው ቀጠና መረበሹ የማይቀር ይመስለኛል። ስለሆነም፣ ጠንክረን መሥራት ያለብን አሁን ነው። ልዩነቶቻችንን በውይይት በመፍታት እየመጣ ያለውን አደጋ በጋራ መከላከል ይገባል።

የጽሑፉን አቅራቢ ታደሰ ብሩ ኬርስሞ (ዶ/ር) በ tkersmo@yahoo.com ኢሜል አድራሻ ያገኙዋቸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 167 ጥር 7 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here