በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተቀሰቀሰው ጦርነት ኹለተኛ ዓመቱን ማስቆጠር ቢጀምር፣ አሁንም ድረስ ዕልባት አላገኘም። ትግራይ ክልል ውስጥ በተቀሰቀሰው ጦርነት ላይ እጃቸው አለበት ተብለው ከአንድ ዓመት በፊት በሕግ ቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው በሽብርተኝነት ክስ ሲታይ የነበሩት እነ ስብሐት ነጋን፣ መንግሥት ታኅሣሥ 29/2014 ክሳቸውን ተቋርጦ ከዕሥር እንዲፈቱ አድርጓል።
መንግሥት ክሳቸው ተቋርጦ ከዕሥር እንዲፈቱ ከወሠነላቸው ከእነ ስብሐት ነጋ በተጨማሪ፣ በእነ ጀዋር መሐመድ እና እስክንድር ነጋ የክስ መዝገብ የተያዙ ዕሥረኞችም ክሳቸው ተቋርጦ ከዕሥር ተፈተዋል። ይሁን እንጂ፣ በተለይ የእነ ስብሐት ነጋ ክስ መቋረጥ በብዙዎች ዘንድ ቁጣ ቀስቅሷል።
መንግሥት ለውሳኔው ማብራሪያ ለመስጠት ቢሞክርም፣ እስካሁን በመንግሥት በኩል የተሠጡ ማብራሪያዎች ሕዝብ እያሳመኑ እና ተቀባይነት እያገኙ ያለ አይመስልም። ውሳኔው ‹‹ሕጋዊ ውሳኔ ወይስ ፖለቲካዊ ውሳኔ›› የሚለው ጉዳይ ብዙዎችን እያወዛገበ ይገኛል። የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ በተለይ ቁጣ የቀሰቀሰውን የእነ ስብሐት ነጋ ክስ መቋረጥ እና ከዕሥር መፈታት ‹‹ሕጋዊ ወይስ ፖለቲካ ውሳኔ?›› ሲል፣ የሕግ እና የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያዎችን አነጋግሮ የሐተታ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።
ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ከምታስተናግዳቸው ግጭቶች በተጨማሪ፣ አውዳሚ ጦርነት ውስጥ ከገባች ከአንድ ዓመት በላይ አልፏል። በ2013 ጥቅምት መጨረሻ ሳምንት ላይ በትግራይ ክልል የተጀመረው ጦርነት ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀባቸው ጊዜያት የተለያዩ ተለዋዋጭ ኹነቶችን አስተናግዷል።
በትግራይ ክልል የተጀመረው ጦርነት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ ለአምስት ወራት ያክል መቆየቱ የሚታወስ ነው። በኹለቱ ክልሎች ለአምስት ወራት በወረራ የቆየው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) ወደ ትግራይ ቢመለስም ጦርነቱ አሁንም ድረስ ዕልባት አላገኘም። ጦርነቱ ባልተቋጨበት በዚህ ወቅት ከሠሞኑ በመንግሥት በኩል የተወሠነው በዕሥር ላይ የነበሩ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ክስ ማቋረጥ በብዙዎች ዘንድ ያልተጠበቀ እና ቅሬታ የፈጠረ ጉዳይ ሆኗል።
መንግሥት ክሳቸውን ያቋረጠላቸው ተከሳሾች በእነ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል(ዶ/ር) መዝገብ ከተከሰሱት መካከል የቀድሞው የህወሓት አመራሮች ስብሐት ነጋ፣ ቅዱሳን ነጋ፣ ዓባይ ወልዱ፣ አባዲ ዘሙ፣ ኪሮስ ሐጎስ እና ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር ናቸው። እንዲሁም በእነ ጀዋር ሲራጅ መሐመድ መዝገብ የተከሰሱ 20 ተጠርጣሪዎች እና በእነ እስክንድር ነጋ የከስ መዝገብ የተከሰሱ ሰባት ተጠርጣሪዎች ክሳቸው እንዲቋረጥ ተደርጎ ከዕሥር ተፈተዋል።
እነ ስብሐት ነጋ በሰሜኑ ጦርነት ተሳትፎ ክስ ቀርቦባቸው ጉዳያቸው በፍረድ ቤት እየታየ ለአንድ ዓመት በዕሥር ላይ የቆዩ ሲሆን፣ እነ ጀዋር እና እነ እስክንድር ደግሞ በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ምክንያት በተቀሰቀሰው ግጭት ክስ ቀርቦባቸው ለአንድ ዓመት ተኩል በዕሥር ላይ ቆይተዋል።
በእነ ጀዋር እና በእነ እስክንር መዝገብ የተከሰሱ ተጠርጣሪዎች ክስ መቋረጥን ተከትሎ የመጣው እና በብዙዎች ዘንድ ያልተጠበቀው የእነ ስብሐት ነጋ ክስ መቋረጥ ሲሆን፣ የእነ ስብሐት ክስ መቋረጥ ከመንግሥት ደጋፊዎች እስከ ተቃዋሚዎች፣ ከታዋቂ ሰዎች እስከ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተቃውሞ ገጥሞታል።
የእነ ስብሐት ነጋ ክስ መቋረጥ እና ከዕሥር መፈታት ያልተጠበቀ ጉዳይ መሆኑን ተከትሎ፣ በብዙዎች ዘንድ ቅሬታ እና ጥያቄ በመነሳቱ የፍትሕ ሚኒስቴር በውሳኔው ማግስት ማብራሪያ የሠጠ ሲሆን፣ ውሳኔው የተሠጠው ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀውን አገራዊ ምክክር አካታች ለማድረግ በማሰብ መሆኑን ገልጿል። በሌላ በኩል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በበኩሉ ዕሥረኞቹ የተፈቱት “የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋትና ለአካታች አገራዊ ምክክር ሲባል ነው” ያለ ሲሆን፣ መንግሥት አስረኞቹን የፈታው “በምሕረት” መሆኑን ገልጿል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እና ፍትሕ ሚኒስቴር በዕሥረኞች መፈታት ላይ በሕዝብ በኩል ለተፈጠረው ቅሬታ በሠጡት ማብራሪያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ “ክስ ማቋረጥ” ነው ሲል፣ አገልግሎቱ ደግሞ “ምሕረት” ነው ማለቱን ተከትሎ በጉዳዩ ላይ ለሕዝብ በቂ እና ተጨባጭ መረጃ የሚሠጡ አይደሉም በሚል ትችት እነዲቀርብባቸው ሆኗል።
በኹለቱ የመንግሥት ተቋማት በኩል የተሠጡት ማብራሪያዎች የሕዝቡን ቅሬታ እና ጥያቄ የመለሱ አለመሆናቸውን ተከትሎ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጥር 1/2014 በተካሄደው የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት የምረቃ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር እግረ መንገዳቸውን ምላሽ ሠጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዕሥረኞቹ ክስ መቋረጥ ቅሬታ መፍጠሩን “ክስ የተቋረጠላቸው የተሸነፉ ኃይሎች ክስ እንዲቋረጥና ከዕሥር ቤት እንዲወጡ ሲደረግ ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሷል” ሲሉ አምነዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሠጡት ማብራሪያ ቁጣው የተቀሰቀሰው በኹለት ቡድኖች መሆኑን ያብራሩ ሲሆን፣ “አንደኛው ቡድን ኹል ጊዜ እያጋጨ በሠበር ዜና ብር የሚሰበስብ እና ኹለተኛው ቡድን በዜናው ድንገተኝነት የደነገጠ፤ በጦርነቱ ጊዜውን፣ ገንዘቡንና ሕይወቱን ለመስጠት የወሠነ እና ይህን ዕኩይ ጠላት አምርሮ የሚጠላና ከዚህ እኩይ ጠላት ጋር የሚደረግ ማንኛውም ንግግር ኢትዮጵያን ይጎዳል ብሎ የሚያምን ቅን ተቆጭ ነው” ብለውታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው “ቅን ተቆጭ” ያሉትን ኃይል መንግሥታቸው ሙሉ በሙሉ እንደሚረዳ፣ እንደሚያደምጥ እና እንደሚያስገነዝብ የገለጹ ሲሆን፣ “ቅን አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊን በውስጥም በውጭም የሚገኙ የአንዳንዶችን ከእኛ ይቅር ማለት አምርረው የጠሉ እና የደነገጡ ወንድም እና እህቶቻችን እንዲገነዘቡልን የምንፈልገው፣ ይህ ጉዳይ እኛም መጀመሪያ ስንሰማው ያስደነገጠን መሆኑን ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። ውሳኔው ለኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም የሚበጅ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “እየመረረን የዋጥነው እውነት ነው እና ደጋግማችሁ በማሰብ እናንተም ይህንን ውሳኔ እንድትቀበሉ በትህትና እጠይቃችኋለሁ” በማለት በውሳኔው ቅሬታ ያላቸው ወገኖች እንዲቀበሉ ጠይቀዋል።
ውሳኔውን ለምን? ብለው ለሚጠይቁ አካላት በሠጡት ምላሽ፣ “ይህ ውሳኔ የተወሰደው ኢትዮጵያን በጠንካራ ዓለት ላይ ለማኖር ነው፤ ጠላቶቿን ለመቀነስ ነው፤ ጉልበት ለመሰብሰብ ነው፤ ያልገባውና የሚከተል ማኅበረሰብ ካለ ከጥፋት ጎዳና እንዲመለስ ለማድረግ ነው፤ ሌላም በርካታ ምክንያቶች አሉት” ብለዋል።
“ክስ ማቋረጥ ማለት ምህረት መስጠት ማለት አይደለም፤ ክስ የተቋረጠለት ሰው በአግባቡ መጠቀም ካልቻለ መልሶ የክስ መዝገቡን መምዘዝ የሚቻል ስለሆነ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚሁ መድረክ ላይ ሽማግሌዎች በዕሥር ቤት እንዳይሞቱ ከዕሥር እንዲፈቱ መወሠናቸውን ገልጸዋል። በጦርነቱ ህወሓት አሸንፎ አዲስ አበባ ቢገባ “ምህረት ለመስጠት ሳይሆን ምህረት ለመቀበል የሚያበቃ ዕድል ማግኘት እንችል ነበር ወይ፣ ምህረት መስጠት ከማሸነፍ ጋር የሚያያዝ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ጉቦ በልተን እንዳለቀቅናቸው እንድታስቡ ላሳስባችሁ እወዳለሁ” ሲሉም ተደምጠዋል።
በፍትሕ ሚኒስቴር እና በኮሙኒኬሽን አገልግሎት ማብራሪያ ላይ ያጋጠመው የ“ክስ ማቋረጥ” እና የ“ምህረት” መምታታት ጉዳይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር ላይ ተደግሟል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ስለ “ክስ ማቋረጥ” እና ስለ “ምህረት” ልዩነት ቢያብራሩም “ጀግኖች፣ አሸናፊዎች፣ ምህረት ሰጭዎች ስላደረገን ፈጣሪያችንን እናመሰግናለን” በሚለው ንግግራቸው፣ ስለ ውሳኔውን ሲያብራሩ አንድ ጊዜ “ክስ ማቋረጥ” ሌላ ጊዜ “ምህረት” አድርገው መግለጻቸው አሁንም በብዙዎች ዘንድ ግልጽ ያልሆነ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል።
በውሳኔው የተቀሰቀሰው ቁጣ እና ተቃውሞ እስካሁን ባለው ኹኔታ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ አለመቀልበሱን የሚያሳዩ ሐሳቦች አሁንም እየተንጸባረቁ ነው። ከሠሞኑ በውሳኔው ተቃውሞ የሞቀው የማኅበራዊ መገናኛ መንደር የሚንጸባረቁ ሐሳቦች በመንግሥት ላይ ጥርጣሬ እና የቁጭት ድምጸት ያዘሉ ናቸው።
መንግሥት በተመሳሳይ ጊዜ ያቋረጠው ክስ የእነ ጀዋር እና የእነ እስክንድርን የሚያካተት ነው። በብዙዎች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ የቀሰቀሰው የእነ ሰብሐት ነጋ ክስ መቋረጥ ነው። የእነ ስብሐት ነጋ ክስ መቋረጥ ቁጣ የቀሰቀሰው የጦርነቱ ቀስቃሽ የሆነው የህወሓት አካል በመሆናቸው እና በተሳተፉበት ጦርነት የደረሰው ጉዳት ከዕሥር እንዲፈቱ የሚያስችል አለመሆኑ እንደ ምክንያት ተነሰቷል።
የእነ ጀዋር እና የእነ እስክንድር ነጋ ከዕሥር መፈታት በተወሰነው የማኅበረሰብ ክፍል የሚጠበቅ ጉዳይ እንደነበር እና ብዙ ድንጋጤና ተቃውሞ የፈጠረ አለመሆኑን የሚያሳዩ ሐሳቦች ሲንሸራሸሩ መታዘብ ይቻላል።
የሦስቱም የክስ መዝገብ በፍትሕ ሚኒስቴር፣ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ፣ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት “በሕገ መንግሥት እና የሽብር ችሎት” እየታየ እንደነበር የገለጸው ፍትሕ ሚኒስቴር፣ የተከሳሾቹ ክስ የተቋረጠው በዐዋጅ ቁጥር 943/2008 መሠረት ነው ብሏል።
ውሳኔው ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተቋውሞ የገጠመው ሲሆን፣ ጉዳዩን ከተቃወሙት ውስጥ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) እና እናት ፓርቲ ይገኙበታል። ፓርቲዎቹ የመንግሥትን ውሳኔ ተቃውመው መግለጫ አውጥተዋል።
ኢዜማ በጉዳዩ ላይ፣ “ኹልጊዜ ወገንተኝነታችን ከኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ጋር ይሁን” በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ፣ “በሕግ ጥላ ሥር የነበሩ ሰዎች በክስ ማቋረጥ የተለቀቁት በእነሱ አነሳሽነት የተቀጠፉ ሕይወቶች ቁስል ባልሻረበት እና የወደሙ አካባቢዎች እስካሁን ባላገገሙበት ኹኔታ ነው” ብሏል። “ተበዳይ ፍትሕ ሳያገኝ እንዲሁም ሳይካስ፣ በዳይን ነፃ ማውጣት በፍትሕ ሥርዓቱ መቀለድ፣ የሕዝባችንን ጉዳትም ማቃለል ነው። እንደዚህ በጥድፊያ የሚደረጉ ውሳኔዎች ፍትሕን በመጨፍለቅ በተቋማቱ ላይ ያለንን ዕምነት በሒደት የሚሸረሽሩ ናቸው” ያለው ኢዜማ፣ ከሕዝብ ጋር ምክክር የጎደለው ግብታዊ ዕርምጃ የአገር ባለቤትነት እና መብትን ለአመፀኛው፣ የፈለገው ነገር እስካልተፈፀመ ድረስ አገር ብትጠፋ ከቁብ ለማይቆጥረው እና የሕዝቧ ሥቃይ ግድ ለማይሰጠው ኃይል አሳልፎ ይሰጣል ብሏል።
የመንግሥትን ውሳኔ ተቃውሞ መግለጫ ያወጣው እናት ፓርቲ በበኩሉ፣ “ኹሉ በሕግ እና በሕግ ብቻ ይሁን” ያለ ሲሆን፣ የመንግሥት ውሳኔ የትኛውም አካል የአገር መሪዎችን ጨምሮ ኹሉም ሰው ከሕግ በታች መሆኑ ግልጽ ጉዳይ ሆኖ ሳለ፣ በወንጀል የተጠረጠረን ግለሰብም ይሁን ድርጅት በሕግ ጥላ ሥር አውሎ የመመርመር፣ ነጻ መሆናቸውን አረጋግጦ የማሰናበትም ሆነ ጥፋተኛ መሆናቸውን ለይቶ ተገቢውን የዕርምት ዕርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት የሕግ ሥርዓቱ ተግባር ሆኖ ሳለ፣ ሕግ በብዙ ሰዎች ሞትና የንብረት ውድመት ጠርጥሬያቸዋለሁ ብሎ በቁጥጥር ሥር ያዋለቸውን ግለሰቦች ጨምሮ፣ በአገር ክህደት ተግባር ተሳትፈዋል፣ አልፎም በሽብርተኛነት የተፈረጀ ድርጅት መሥራችና ዘዋሪዎችን ሕጋዊ ሒደትን ባልጠበቀ ሁኔታ “ክስ በማቋረጥ” ማሠናበት በሕግ ተቋማት ሥራ ላይ ያለውን ጣልቃገብነት ከማሳየቱም ባሻገር፣ የፈላጭ ቆራጭነት ማሳያ ነው ብሏል።
ሌላኛው የመንግሥትን ውሳኔ የተቃወመው አብን፣ “በአገር ላይ ይቅር የማይባል ክህደት የፈፀሙና ሕዝብ ቀስቅሰው፣ ጦር አደራጅተው በመምራት ለዚህ ኹሉ አገራዊ ውድመት የዳረጉንን፣ በአገሪቱ ፓርላማ በአሸባሪነት የተፈረጀው ድርጅት ቁንጮ አመራሮችን ያለምንም ቅድመ ኹኔታና ማብራሪያ ከዕሥር በመፍታት የአገርና የሕዝብን ጥቅምና ክብር በፅኑ የሚጎዳ ታላቅ ታሪካዊ ስህተት መንግሥት ፈጽሟል። ለአገር ሕልውናና ለሕዝባችን ሠላምና ደኅንነት በመላው ኢትዮጵያውያን የተከፈለውን መሰዋዕትነት ዋጋ የሚያሳጣ፣ በይቅርታና በሰብዓዊነት ስም የተፈፀመ ኢ-ሰብዓዊና ኢ-ፍትሐዊ ውሳኔ መሆኑንም ያምናል” ያለ ሲሆን፣ ውሳኔው ሠላማዊና ሕጋዊ ፖለቲካን ክፉኛ የሚጎዳ ውሳኔ በመሆኑ በአፋጣኝ ዕርምት እንዲደረግ ጠይቋል።
የዕሥረኞች መፈታት ሕጋዊ ወይስ ፖለቲካ ውሳኔ?
በተለይ የእነ ስብሐት ነጋ ክስ መቋረጥ እና ከዕሥር መፈታት ሕጋዊ ውሳኔ ነው አይደለም በሚለው ጉዳይ ላይ ብዙ የሕግ ባለሙያዎች ሐሳባቸውን እየገለጹ ይገኛሉ። በውሳኔው ሕጋዊነት ላይ ጥያቄዎች መበርከታቸውን ተከትሎ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማብራሪያ የሠጠ ሲሆን፣ ፍትሕ ሚኒስቴር በሦሶት መዝገቦች የቀረቡ ክሶች እንዲቋረጡ ለሚመለከተው ችሎት ባቀረብኩት ጥያቄ መሠረት ሕጋዊ ሥርዓቱን ተከትለው መዝገቦቹ ተስተናግደዋል ብሏል።
“የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የሕገ-መንግሥት እና ሽብር ጉዳዮች አንደኛ ወንጀል ችሎት የፍትሕ ሚኒስትሩን ማመልከቻ በመመርመር በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ ዐዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6(3)ሠ መሠረት ክሱን ያነሳ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ፣ “ተከሳሾች በሌላ ወንጀል የማይፈለጉ ከሆነ ከዕሥር እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ለማረሚያ ቤት አስተላልፏል” ብሏል ፍድር ቤቱ በሰጠው ማብራሪያ። ፍርድ ቤቱ አክሎም አሁን በሥራ ላይ ባለው ሕግ መሠረት፣ ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ በተለያዩ ምክንያቶች ክሱን መቀጠል እንደማይፈልግ ሲያመለክት ፍርድ ቤቱ የክስ ይቋረጥ ጥያቄውን በመቀበል በዕሥር ላይ የሚገኙት ተጠርጣሪዎች እንዲለቀቁ ማዘዙ ሕጋዊ አሠራር መሆኑን አስታውቋል።
ፍትሕ ሚኒስቴር እና ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ ውሳኔው ሕጋዊ መረት እንዳለው ለማስረዳት በየፊናቸው ማብራሪያ ቢሰጡም፣ ብዙዎች የውሳኔውን ሕጋዊነት እየተቀበሉ አይደለም። ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ የደረጉት የሕግ ባለሙያው ጥጋቡ ደሳለኝን የመንግሥት የተከሳሾች ክስ ማቋረጥ፣ በተለይ የእነ ስብሐት ነጋን ክስ መቋረጥ፣ ሕጋዊ መሠረት የሌለው መሆኑን ጠቁመዋል።
የሕግ ባለሙያው የእነ ስብሐት ነጋ ክስ መቋረጥ ሕጋዊ መሠረት የለውም ያሉበት ምክንያት፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀ ድርጅት አባል በመሆናቸው እና የሰሜኑ ጦርነት ዋና ዋና ቀስቃሾች ውስጥ ስለሚካተቱ ጉዳዩ አገር የማፍረስ በመሆኑ የአገር ጉዳይ ክስ ሊቋረጥ አይችልም ብለዋል። የሕግ ባለሙው አክለውም፣ መንግሥት በእነ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል(ዶ/ር) መዝገብ የተከሰሱ ስድስት ተከሳሾችን ለይቶ ክሳቸውን ለማቋረጥ እንደ ምክንያት ያስቀመጠው የዕድሜ መግፋት እና የጤና ችግር ከሕግ አንጻር ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።
በመንግሥት በበኩሉ የዕሥረኞች ክስ ያቋረጠበትን ምክንያት ሲያስረዳ ወደፊት ይካሄዳል ተብሎ ለሚታሰበው አገራዊ ምክክር አካታችነት ለመፍጠር ነው ብሏል። የሕግ ባለሙያው እንደሚሉት አገራዊ ምክክሩን አካታች ለማድረግ ለሚለው ጉዳይ ክሳቸው ቢቋረጥ የእነ ጀዋር እና የእነ እስክንድር ክስ መቋረጥ የተሻለ አግባብነት ይኖረዋል ብለዋል።
ይሁን እንጂ፣ የእነ ስብሐት ከስ መቋረጥ ከሕግ አንጻር ለአገራዊ ምክክር የሚኖረው ፋይዳ እንደማይኖር ጠቁመዋል። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀ ድርጅትም ይሁን የድርጅት አባል መካተት አይችልም ብለዋል። በመሆኑም፣ በሕጋዊ አካሄድ በአገራዊ ምክክር መሳተፍ የማይችል ድርጅት አባላትን ክስ ማቋረጥ ለአገራዊ ምክክሩ ፋይዳ እንደማይኖረው የሕግ ባለሙያው ይገልጻሉ።
“ከውሳኔው ጀርባ ፖለቲካዊ ውሳኔ አለ” የሚሉት የሕግ ባለሙያው፣ መንግሥት እስካሁን የሠጣቸው ማብራሪያዎች እርስበራሳቸው የሚጣረሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በሕዝቡ በኩል የሚታየው ቅሬታ መንግሥት ለውሳኔው መነሻ እንደ ምክንያት ያቀረበው ሐሳብ አሳማኝ ባለመሆኑ ነው የሚሉት የሕግ ባለሙው፣ ምንም አንኳን ኹሉ ነገር ለሕዝብ የማይነገር ቢሆንም እንደ ሕዝብ ምን እየተካሄደ እንደሆነ የማወቅ መብት ስላለው መንግሥት ይህን ጉዳይ ግልጽ ማድረግ አለበት ብለዋል።
መንግሥት የወሠነው ዕሥረኞችን የመፍታት ውሳኔ፣ በተለይ ክሳቸው የተቋረጠላቸው የህወሓት አባላት በሚካሄደው አገራዊ ምክክር ላይ ከሕግ አግባብ ውጭ የመሳተፍ ዕድል ከተሠጣቸው፣ የአገራዊ ምክክሩ ሕጋዊነት እና ውጤታማነት ላይ መጥፎ ጥላ የሚያጠላ ጉዳይ እንደሚሆን የሕግ ባለሙው ጠቁመዋል።
ከውሳኔው በኋላ ብዙዎች በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 28 ሥር በሰብዕና ላይ ስለሚፈጸሙ ወንጀሎች የተጠቀሰውን የሕግ ድንጋጌ በማንሳት የእነ ሰብሐትን ክስ ማቋረጥ እየተቃወሙ ነው። አንቀጽ 28 “ኢትዮጵያ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና በሌሎች በኢትዮጵያ ሕጎች በሰው ልጅ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ተብለው በተወሰኑት ወንጀሎች ላይ፣ ለአብነትም፣ ሰው ዘር ማጥፋት፣ ያለፍርድ የሞት ቅጣት ዕርምጃ መውሰድ፣ በአስገዳጅ ሰውን መሰወር፣ ወይም ኢ-ሰብዓዊ የድብደባ ድርጊቶችን መፈጸም ላይ ክስ ማቅረብ በይርጋ አይታገድም። በሕግ አውጪው ክፍል ሆነ በማንኛውም የመንግሥት አካል ውሳኔው በምህረት ወይም በይቅርታ አይታለፍም።” ተብሎ ተደንግጓል።
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና የፖለቲካ ተንታኙ ዳምጠው ተሰማ(ረ/ፕ) በበኩላቸው፣ በተለይ የእነ ስብሐት ነጋ ክስ መቋረጥ ሕጋዊ ውሳኔ እንዳልሆነ እና ፖለቲካዊ ውሳኔ መሆኑን ለማረጋገጥ አንቀጽ 28 በቂ ማስረጃ ነው ይላሉ። የእነ ስብሐት ክስ መቋረጥ መንግሥት እንዳለው ትክክለኛ መሠረቱ የጤና ችግር ከሆነ እና ሰዎቹ ህወሓትን ወክለው ከማንኛውም አካል ጋር ግንኙነት የማያደርጉ እና ከህወሓት ጋር የማይገናኙ ከሆነ የከፋ ችግር ላያስከትል ይችላል ይላሉ።
መንግሥት የእስረኞችን ክስ ያቋረጥኩት ለአገራዊ ምክክር አካታችነት ነው ያለው ምክንያት የሚያገለግለው ለእነ እስክንድር እና ለእነ ጀዋር እንጂ፣ ለእነ ስብሐት አይደለም ይላሉ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ። እነ ስብሐት ነጋ ወደፊት በሚካሄደው አገራዊ ምክክር ላይ ህወሓትን ወክለው የሚመጡ ከሆነ ሌላ እንደሚሆን መምህሩ ጠቁመዋል።
መንግሥት የእነ ስብሐትን ክስ ለማቋረጥ ያበቃውን መሠረት ለማስረዳት የሄደበት ሒደት ትክክል አይደለም የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ፣ የህወሓት መሪዎች እና ህወሓት እንደ ድርጅት ያያዘው አቋም ኢትዮጵያን የማፍረስ ወይም በፈለገው መንገድ የመግዛት ዓላማ በመሆኑ፣ እንደ ድርጅት ለአገራዊ ምክክር ሚና አይኖረውም ብለዋል። በመሆኑም መንግሥት ለወጠነው አገራዊ ምክክር እና መግባባት የትግራይ ሕዝብ የኢትዮጵያ አካል በመሆኑ ከህወሓት ውጪ በታዋቂ ሰዎች እና በሲቪል ድርጅቶች መወከል እንዳለበት ጠቁመዋል።
የጦርነት መቋጫው ሠላማዊ ድርድር ነው የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ዳምጠው፣ የጦርነት ዓላማ ሠላም ማምጣት መሆኑን ይገልጻሉ። ለዚህም በጦርነት ወቅት ድርድር የሚካሄደው የግድ ጦርነት ሲያልቅ አይደለም፣ በጦርነት መካከል ድርድር ይኖራል ይላሉ።
በሰሜኑ በኢትዮጵያ ክፍል ያለው ጦርነት ምንም እንኳን ህወሓት ወደ ትግራይ ቢመለስም ጦርነቱ ቆሟል ወይም አልቋል ማለት እንደማይቻል የሚገልጹት ዳምጠው፣ አሁን ባለው ኹኔታ ጦርነቱ ቆሞ በደርድር የሚፈታበት ዕድል መኖሩን ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ጠቁመዋል። ምንም እንኳን ጦርነቱ ባያልቅም ደርድር ጦርነት እስከሚያልቅ አይጠብቅም የሚሉት ዳምጠው፣ መንግሥትም ይሁን በሕዝብ በኩል የሚባለውን ሳይሆን መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ኹኔታ መገንዘብ እና በዚያው ልክ መጓዝ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
በመንግሥት በኩል በተለይ ከሠሞኑ በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ስለ ድህረ ጦርነት ኹኔታዎች እየተወያዩ ነው። በመንግሥት በኩል ስለ ድህረ ጦርነት የሚወራው ነገር ጦርነቱ እንዳለቀ አድረጎ የመሳል ሁኔታ ማሳየቱ እና ጦርነቱ ዕልባት አለማግኘቱም በብዙዎች ዘንድ ቅሬታ ፈጥሯል።
ህወሓት ወደ ትግራይ ክልል መመለሱን ተከትሎ ጦርነቱ ከወትሮው ግለት የመቀዝቀዝ ኹኔታ ቢያሳይም፣ በአፋር እና በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ትንኮሳ እያደረገ መሆኑ እየተገለጸ ነው። ጦርነቱ ሳያልቅ እንዳለቀ አድርጎ የሚሳልበት ኹኔታ ትክክል አለመሆኑን የሚገልጹት የፖለቲካ ሳይነስ መምህሩ ዳምጠው፣ “በሕዝቡ የተባለውን ብቻ ሳይሆን ነባራዊ ኹኔታውን መረዳት አለበት” ብለዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 167 ጥር 7 2014