አማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም በ2 ቢሊዮን ብር በአዲስ አበባ ዋና መሥሪያ ቤት እየገነባ ነዉ

Views: 351

ከአንድ ዓመት በኋላ ዋና መሥሪያ ቤቱን ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ ለማዘዋር አቅዷል

የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የፋይናንስ ዲስትሪክት ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ዋና መሥሪያ ቤቱን ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ ለማዘዋወር በኹለት ቢሊዮን ብር ሕንፃ እያስገነባ መሆኑን አስታወቀ።

ግንባታው በቀጣይ ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። ሕንፃውም በ3 ሺሕ 500 ካሬ ሜትር ያረፈ ሲሆን በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለከተማ ከብሔራዊ ባንክ ፊት ለፊት ይገኛል። ከተጀመረ አንድ ዓመት ተኩል የተጠጋው የሕንፃው ግንባታ፣ አንድ አራተኛው የተጠናቀቀ ሲሆን በታቀደለት ጊዜ እየሄደ መሆኑን የፕሮጀክቱ አማካሪ ሄኖክ ግርማ ገልፀዋል።

ሕንፃው 35 ወለሎች የሚኖሩት ሲሆን ግንባታው እየተከናወነ የሚገኘው ቻይና ሁዪ ተብሎ በሚጠራ ድርጅት ነው። ድርጅቱ በሚቀጥለው ዓመት ሙሉ ለሙሉ ግንባታውን አጠናቆ ለተቋሙ እንደሚያስረክብ ይጠበቃል ሲሉ የፕሮጀክቱ ማናጀር ሙሉጌታ መንገሻ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ግንባታው እንደተጠናቀቀ ሕንጻው የቢሮ፣ የመኖሪያ ቤት፣ የመዝናኛ ቦታንና የመሰብሰቢያ አዳራሽን ጨምሮ ጥቅል አገልግሎቶች ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የቁጠባ ተቋሙ በአዲስ መልኩ ለሚጀምረው የባንክ እንዲሁም ከዚህ ቀደም ይሰጥ የነበረውን የማይከሮ ፋይናንስ አገልግሎቶ በይበልጥ እንደሚሰጥም ሙሉጌታ ጠቁመዋል።

ተቋሙ ወደ ባንክ ለማደግ የብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ያገኘ ሲሆን፣ ይህንንም ተግባራዊ ሲያደርግ የሕንፃው ግንባታ ስለሚጠናቀቅ የአገልግሎት አድማሱን ለማስፋት እንደሚረዳው ሙሉጌታ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ግማሽ ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል በቂ ቢሆንም፣ ይህንን ካሟላ የአማራ ቁጠባ ዓመታት እንዳለፈው መረጃዎች ያሳያሉ። በአሁኑ ሰዓት ወደ ሰባት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ካፒታል ያለው ተቋሙ፣ ይህም ከማይክሮ ፋይናንስ ድርጅቶች መካከል ቀዳሚ ያደርገዋል።

የተቋሙ ሥራ አስኪያጅ መኮንን የለውምወሰን እንደገለፁት፣ በቅርቡ በፓርላማ በፀደቀው ሕግ መሰረት ማይክሮ ፋይናንሶች የባንክ አገልግሎቶችን መስጠትም ሆነ ወደ ባንክ ማደግ የሚችሉ ሲሆን፣ ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችንም ድርጅታቸው እንዳሟላ ተናግረዋል።

ከተመሠረተ 25 ዓመታት የሆነው የአማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋም (አብቁተ) አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ደንበኞችን አፍርቷል። በአሁኑ ጊዜም ካሉት ማይክሮ ፋይናንሶች በትርፍም ሆነ በደንበኞች ብዛት እና ቁጠባ በመሰብሰብ በመሪነት ተቀምጧል።

ተቋሙ በመቋቋሚያው አምስት መሥራች አባላት የነበሩት ሲሆን፣ የአማራ ክልል መንግሥት 25 በመቶ፣ አመልድ 35 በመቶ፣ አማራ ልማት ማኅበር 20 በመቶ፣ ጥረት ኮርፖሬት 10 በመቶ እና የአማራ ሴቶች ልማት ማኅበር 10 በመቶ ድርሻዎች ይዘው በኹለት ሚሊዮን ብር እንደመሠረቱት መረጃዎች ያሳያሉ።
ተቋሙ በአሁኑ ወቅት 473 ቅርንጫፎች አሉት። 12 ሺሕ 686 የሚጠጉ ሠራተኞችን ይዟል።

ቅጽ 2 ቁጥር 68 የካቲት 14 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com