የአፍሪካ ኅብረት በ2030 የሴት ልጅ ግርዛትን የማጥፋት ትልም

0
702

የአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት መሪዎች ዘንድሮ በስብሰባቸው ከተነጋገሩባቸው አጀንዳዎች አንዱ ‘የሴት ልጅ ግርዛት’ ጉዳይ ተጠቃሽ ነው። ኅብረቱ ይህንን ኋላ ቀር ልማድ እስከ 2030 ከአፍሪካ ለማጥፋት ቃል ኪዳኑን አጠናክሯል። ይህንን አጋጣሚ በመንተራስ ቤተልሔም ነጋሽ የችግሩን ጥልቀት እና የመፍትሔውን መንገድ በዚህ መጣጥፋቸው ያመላክታሉ።

 

 

አሁንም በአፋርና በአማራ ክልል ሴት ልጅ በተወለደች በሰባተኛው ቀን እንደምትገረዝ ያውቃሉ? የአፍሪካ መዲና በምንላት አዲስ አበባችን በርካታ ሴቶች ልጆች ግርዛት እንደሚፈፀምባቸውስ?

የግርዛቱ ምክንያት ምንድን ነው? ቢሉ “ባሕል!” ለምን? “ሴት ልጅ እንዳትበላሽ፣ ወንድ ጋር እንዳትሔድ (ስሜቷን ለመቀነስ ወይም ለማጥፋት)፣ ዕቃ እንዳትሰብር፣ ኃይለኛ እንዳትሆን፣ ጨዋ እንድትሆን፣ ባሏን እንዳታስቸግር መገረዝ አለባት። ለዓላማ የተፈጠረ አካሏ በሰው ሰራሽ ዘዴ መጉደል አለበት” የሚል ባሕል።

ለዚህ ርዕስ መነሳት ምክንያት የሆነኝ የሰሞናችን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ ጋር ተያይዞ ኅብረቱ ካዘጋጃቸው ስብሰባዎችና አጀንዳዎች አንዱ የነበረ መሆኑ ነው።
የአፍሪካ ኅብረት ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራባቸው አጀንዳዎች አንዱ በሴት ልጅ ጤናና አካል ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ልማዳዊ ድርጊቶችን መዋጋት ነው። ባለፈው ሳምንት ከተካሔደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን ከተካሔዱት ስብሰባዎች አንዱም በተለይ ያለዕድሜ ጋብቻንና ግርዛትን በ2030 ከአፍሪካ ለማጥፋት የኅብረቱ አባል አገራት የገቡትን ቃል እንዲያድሱ ይረዳል የተባለውና በዛምቢያ ፕሬዚዳንት ክቡር ኤድጋር ሉንጉ መሪነት የተካሔደው ስብሰባ ተጠቃሽ ነው። ስብሰባው የተካሔደው የኅብረቱ ያለ ዕድሜ ጋብቻን የማስቀረት ዘመቻ ኹለተኛ ምዕራፍ (2019-2023) እንዲሁም የኅብረቱ የባሕል ሕዳሴ እና የአፍሪካ የወጣቶች ቻርተር፣ የተባበሩት መንግሥታት ዘላቂ የልማት ግቦች 5ኛ ግብ ንዑስ ቁጥር 3 የልጆች ያለ ዕድሜና የግዴታ ጋብቻ እንዲሁም ግርዛትን የመሳሰሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ማጥፋት፣ የማፑቶ ዲክላሬሽን እንዲሁም የኅብረቱ አጀንዳ 2063 በተቀመጠለት ጊዜ እንዲሳካ የሕግ ድጋፍና የማስፈፀሚያ መዋቅር መዘርጋት ነው።

በአፍሪካ በተለይም ከሰሃራ በታች ባለው የአህጉሪቱ ክፍል ያለ ዕድሜ ጋብቻ በከፍተኛ ቁጥር ይፈፀማል። አገራቱ ዝቅተኛ የጋብቻ ዕድሜን በሕግ ደንግገው ያንን የተላለፈ የሚቀጣበትን ሕግ ቢያወጡም፥ በብዙዎቹ አገራት ከሕግ ይልቅ ሃይማኖትና ባሕል ከፍተኛ ቦታ ስለሚሰጠው ያንን ለመቃወምና ድርጊቱ እንዳይፈፀም ለማድረግ፣ ተፈፅሞ ሲገኝም እርምጃ ለመውሰድ አዳጋች ያደርገዋል። ጥናትም የሚረጋግጠው እንደ ድህነት፣ የኢኮኖሚ አማራጭ ማጣት፣ በግጭትና ጦርነት ወቅት የደኅንነት ሥጋት መኖርና ሌሎችም ምክንያቶች ቢሆኑም ያለዕድሜ ጋብቻ እንዲስፋፋና እንዲቀጥል ዋነኛ ሰበቦቹ ሃይማኖትና ባሕል ናቸው።

የአፍሪካ ኅብረት በተለያዩ ዲፓርትመንቶቹ በኩል በመሪዎችና በሚኒስትሮችደረጃ አባል አገራቱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲቀሩ፣ በተለይም የሴት ልጆችን ጤና በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዳውንና የሰብኣዊ መብት ጥሰት የሆነውን ግርዛት፣ እንዲሁም ያለ ዕድሜ ጋብቻ ለማስቀረት እንዲሠሩ ለዚሁ ዓላማ ተብሎ የወጡ አህጉራዊ ማዕቀፎችን እንዲዘረጉና የራሳቸውን ሕጎች ተግባራዊ እንዲያደርጉ የተለያዩ ዘመቻዎችን ያካሒዳል።

 

በኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 49 ከሚሆናቸው ሴቶች 65.2 በመቶ ያህሉ ግርዛት የተፈፀመባቸው ሲሆን፥ በዚህም ኢትዮጵያ ከግብጽ ቀጥሎ በአፍሪካ ኹለተኛዋ ብዙ ሴቶች የተገረዙባት አገር ሆናለች

 

የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት በሚደረገው ጥረት ለምሳሌ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካኝነት በተወሰነ ውሳኔ በየዓመቱ እ.ኤ.አ. ፌብሩዋሪ ስድስት (በእኛ አቆጣጠር ዘንድሮ ጥር 29) “ዓለም ዐቀፍ የሴት ልጅ ግርዛትን የመቃወም ቀን” ይከበራል። ይህነኑ ቀን አስመልክቶም የአፍሪካ ኅብረት በሰጠው መግለጫ አባል አገራቱ ግርዛትን ለማስቀረትና የልጃገረዶችንና የሴቶችን መሠረታዊ መብት ጥሰት ለማስቆም ተጨባጭ እርምጃዎች እንዲወስዱ አሳስቧል።

በዓለም የጤና ድርጅት ትርጓሜ መሠረት የሴት ልጅ ግርዛት ወይም ብልት ትልተላ፣ የሴትን የመራቢያ አካል፣ ተፈጥሯዊ ሁኔታ ለመቀየር የሚሠራ በሕክምና ያልታዘዘ ማናቸውንም ዓይነት ድርጊት ያካትታል። በአብዛኛው ትልተላው የሴትን የመራቢያ አካል የውጪ ክፍል በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በማንሳት የሚፈፀም ሲሆን፥ እንደ አፋር ክልል ባሉ የአገራችን አካባቢዎች ደግሞ መስፋትን ይጨምራል። ድርጊቱ ለልጃገረዶችና ሴቶች የሚሰጠው ምንም ዓይነት ጥቅም አለመኖሩ በጥናት ተረጋግጧል። ይልቁንም ድርጊቱ ከፍተኛ መድማትን፣ ሽንት ለመሽናት መቸገርን እዲሁም በኋላ ላይ ለሚመጣ የዕጢ እና ኢንፌክሽን ችግር መጋለጥን አልፎ ተርፎም በወሊድ ወቅት ውስብስብ ሁኔታዎችንና የሚወለዱ ልጆችን ሞት የመሳሰሉ ከባድ ችግሮችን ያስከትላል።

በዓለማችን በአሁኑ ሰዓት በሕይወት ያሉ፣ ግርዛት የተፈፀመባቸው 200 ሚሊዮን ሴቶች ሲኖሩ፣ አብዛኞቹ በአፍሪካ በመካከለኛው ምሥራቅና እስያ በሚገኙ 30 አገራት ውስጥ የሚኖሩ ናቸው። ድርጊቱ ከሕፃን እስከ 15 ዓመት ዕድሜ የሚፈፀም ሲሆን በልጃገረዶችና በሴቶች ላይ የሚፈፀም የሰብኣዊ መብት ጥሰት ነው።

የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም አንድ ተቋም በሐምሌ 2010 ባወጣው መረጃ በኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 49 ከሚሆናቸው ሴቶች 65.2 በመቶ ያህሉ ግርዛት የተፈፀመባቸው ሲሆን፥ በዚህም ኢትዮጵያን ከግብጽ ቀጥሎ በአፍሪካ ኹለተኛዋ ብዙ ሴቶች የተገረዙባት አገር ሆናለች። አሐዙ በክልሎች ስርጭቱ ሲታይ ሶማሌ ክልል 98.5 በመቶ በመሆን ከፍተኛውን ቁጥር ሲይዝ፥ ትግራይ ክልል 24.2 በመቶ በመሆን ዝቅተኛውን ቁጥር ይዟል። ብዙዎችን ያስደነገጠው አሐዝ የቱ ነው ቢባል በአዲስ አበባ የመውለድ ዕድሜ ክልል ውስጥ ካሉ ሴቶች መካከል 54 በመቶው ግርዛት ተፈፅሞባቸዋል። ሌሎቹ ከፍተኛ አሐዝ ያላቸው ክልሎች አፋር 91.2፣ ሐረሪ 81.7፣ ኦሮሚያ 75.6 እንዲሁም ድሬዳዋ 75.3 በመቶ ናቸው።

ግርዛት የሚፈፀምበትን ዕድሜ በሚመለከት ግርዛት ከተፈፀመባቸው ሴቶች ውስጥ 64 በመቶው ድርጊቱ ሲፈፀም አራት ዓመት አልሞላቸውም። “መቁረጥና የአካል ክፍላቸውን ማስወገድ” ከሚፈፀመው የግርዛት ዓይነት ዋነኛው ነው። ሁሉም ግርዛት የሚፈፀመው በልምድ/ባሕላዊ ገራዦች አማካኝነት ነው።

አገራችን እንደ አብዛኞቹ የአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት እንዲሁም የጉዳዩን አሳሳቢነት አይተው እንቅስቃሴ በሚያደርጉ አካላት ጥረትም ጭምር ግርዛትን በሕግ የሚያስቀጣ ወንጀል አድርጋ አስቀምጣለች። በቀጥታ ግርዛትን ጠቅሶ በማንኛውም ዕድሜ ክልል ላይ ባለች ሴት ላይ ተፈፅሞ ቢገኝ ወንጀል መሆኑን ከመደንገጉ ባሻገር በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠው የዜጎችን በአካላቸው ላይ ከሚደርስ ጉዳት የመጠበቅ መብት (አንቀፅ 16)፣ እንዲሁም ሴቶች በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና ባሕሎች አማካኝነት ከሚደርስባቸው ጉዳት ለመጠበቅ እርምጃ ይወስዳል (አንቀጽ 35 (4) እስከሚለው ድረስ የተለያዩ ሕጎችን ተጠቅሞ ከለላ ይሰጣል። ነገር ግን የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ባለፈው ሳምንት (ጥር 29 እና 30) ባካሔደው ሴቶችንና ሕፃናትን በሚመለከት ያሉትን ሕጎች ክፍተት የተመለከተ ስብሰባና የጥናት ውጤት ይፋ ማድረጊያ ሥነ ስርዓት እንዳለው፣ የወንጀሉ በቅጣት አወሳሰን መመሪያ አለመካተትና ደረጃ ያልወጣለት መሆንና የፍትሕ አካላት በቅንጅት መሥራት አለመቻላቸው፣ እንዲሁም ማስረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑና ወደ ሕግ ለመውሰድም ቸልተኝነት መኖሩ፥ በሕጉና በአፈፃፀሙ በኩል የሚታዩ ክፍተቶች መሆናቸው ተገልጧል።

በተለያዩ አካባቢዎች በሲቪል ማኅበረሰቡ አማካኝነት በተደረጉ ዘመቻዎችና ልዩ ልዩ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ድርጊቱ በተወሰነ መልኩ መቀነሱን መረጃዎች ያሳያሉ። እዚህ ላይ በደቡብ ክልል ዱራሜ አካባቢ፣ በከንባታ ሴቶች ራስ አገዝ ማኅበር በኩል በተደረገ ዓለም ዐቀፍ ዕውቅና ጭምር የተቸረው ተግባር ድርጊቱ እስከ መቅረት መድረሱን እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል።

“ምን መደረግ አለበት?” ወደ ሚለው ስንመጣ እስከዛሬ ተግባር ላይ የዋሉትን ዘዴዎች ቀጥሎ አዳዲስና ፈጠራ የታከለባቸው፣ ከዚህ በፊት በየአካባቢው ያልተሞከሩ ነገር ግን በሌላ አካባቢ ውጤታማ የሆኑ ዘዴዎችን መጠቀም አንድ አማራጭ ነው። ለምሳሌ እንደ ቢቢሲ ዘገባ ድርጊቱ ከሚፈፀምባቸው አካባቢዎች ለምሳሌ በኬንያ የማሳይ ጎሳ አባላት የሆኑ ይህን ጎጂ ባሕል ለማጥፋት የሚሠሩ ወጣት ወንዶች የተጠቀሙበት ዘዴ ወጣት ወንዶች ግርዛት ሲፈፀም ምን እንደሚመስል በማሳየት ሚስቴ የተገረዘች መሆን አለባት የሚለው እሳቤያቸውን ደግመው እንዲያጤኑት ማድረግ ነው።

ከላይ መግቢያዬ ላይ ያነሳሁት የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ለምሳሌ በአፍሪካ ባሕላዊ የጎሳ መሪዎችና ሽማግሌዎች በማኅበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት በማየት፣ እነሱን ተጠቅሞ ተፅዕኖ ለማሳደር ይቻል ዘንድ በማለም ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት፣ ሽማግሌዎችን በመጋበዝ አንድ ላይ ያሰባሰበ ሁነትም ጭምር ነበር።

ድርጊቱ ከባሕልና ከእምነት የተጋመደ ድርጊት የማይጠፋ ቢመስልም፣ በተለይ እንደኛ ማኅበረሰብ ባለ የወሲብንና የመራቢያ አካልን ጉዳይ በጓዳ የሚል ማኅበረሰብ ለዚያ የሚመጥን መፍትሔና የሁሉም አካላት ርብርብ ከተጨመረበት፣ የማይገታበት ምክንያት የለም። ለዚህም በአፍሪካ እ.ኤ.አ. በ2015 ኅብረት ግርዛትን ከአገሯ ጨርሶ በማጥፋት የተመሰከረላት የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ጋምቢያ ታሪክ ምስክር ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 14 የካቲት 9 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here