በር ላይ ለቆሙት

0
261

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

“እስቲ ከበሩ አፍ ፈቀቅ በይ…ሰው ይመላለስበት” ትላለች፤ አያታችን። አንሰማትም “ያው ያሳልፋልኮ!” ብለን ተነጫንጨን ከመንገዱ የሚሆነውን አሻግረን እናያለን። በር አፍ ላይ መቆም ምን ያህል ደስ እንደማይል ማን ያውቃል? ቤት ውስጥ የሚገኝና ከቤት ውስጥ ለመውጣት ለሚያስበው።

አሁን አሁን በከተማ የሚታየውንና ከሴቶች ገዳይ ጋር የሚነሳውን ነገር ስመለከት፤ በር አፍ ላይ የመቆምን ነገር አስታወሰኝ። የሴቶች መብቶችን ከሚመለከቱ ብዙ ጉዳዮች መካከል በከተማ እየተነሳ ያለው በገጠሪቱ የአገራችን ክፍል ያለውን የዘነጋ ይመስለኛል። በከተማው ሴቶች ሁሉን ማድረግ እንደሚቻል ወንዶች ደግሞ አጋር መሆን እንደሚችሉ አሳይተዋል።

ይህ በከተማ ችግር የለም፤ የሴቶች ጥቃት ዜና አይሰማም፤ ሴቷን ዝቅ አድርጎ ማየት የለም…ወዘተ ማለት አይደለም። እንኳን በእኛ አገር በአእምሮ ብስለት በሚልቁን አውሮፓውያን ዘንድ የሴቶች መብት ተነስቶ አብቅቷል የሚባል ነገር የለም። ይሁንና በአገራችን ከበፊቱ በተሻለ መብትን ለማስከበርና እንደ ሰው ተቆጥሮ ለመኖር በሩ ላይ መድረስ ተችሏል።

‘በገጠሩስ?’ ቤት ውስጥ እንዳለና የበሩ አፍ ላይ ሰዎች ቆመው እንደጋወዱት፤ የገጠሩ ጉዳይ ተዘንግቷል። ከአንድ ወዳጄ ጋር ስለሴቶች ጉዳይ ሲነሳ፤ “ልዩ ድጋፍ የሚባለው ነገር እስከመቼ ነው የሚቆየው?” አለኝ። ለዚህ መልስ አልነበረኝም፤ ግን አስፈላጊነቱ እንደማይቀንስ ነገርኩት። እርሱ የሚመለከተው በተመቻቸ የኑሮ ሁኔታ የሚኖሩትንና ልዩ ጥቅም ማግኘት የለባቸውም ብሎ ያሰባቸውን ነው። በዚህ ልክ የሚያስቡ ሰዎች እንዲኖሩ ያደረገው ደግሞ በሩ አፍ ላይ የቆመውና ቤት ውስጥ ያለውን የጋረደው ሐሳብ ነው። ይህ የእኔ ዕይታ ነው።

ሰሞኑን አንዲት ትንሽ ልጅ (ዕድሜዋ 18 ያልሞላት) በጋብቻ መታሰሯን የሚያሳይ ምስል በማኅበራዊ ድረ ገፅ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፤ አዲስ ማለዳም ያለዕድሜ ጋብቻ ላይ ትኩረት ሰጥታ ማስነበቧም ይታወሳል። ይህን በፌስቡክ ብዙዎች ስለተቀባበሉት ሁሉም ታዘበ እንጂ አሁንም በዛ መልኩ የሚዳሩ ትንንሽ ልጆች ሳይኖሩ ቀርተው አይደለም። ለእነዚህ ልጆች ሲባል ነው ከበሩ ፈቀቅ ብሎ ወጥተው እንዲያዩና ጉዳያቸው እንዲነሳ ማድረግ የሚያስፈልገው።

የሬድዮ ተከታታይ ድራማ ላይ ያለች ገፀ ባሕሪ፤ ራሷን ካለዕድሜ ግብቻ ለማትረፍ የምታደርገውን ጥረት ተከትለው ራሳቸውን ለማዳን የሚጥሩ ሴቶች አሁንም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ አሉ። የሴቶችን የመብት ጥያቄ ላይ ጥያቄ ለሚያነሳ ሁሉ በሩ አፍ ላይ ቆሞ መልስ በመስጠትና በመከራከር ጊዜን ማጥፋት ትቶ፤ የተጋረዱ ችግሮችን ማየት ያስፈልጋል። ከተስማማችሁ አላውቅም፤ ግን በሩ ላይ የቆመ ሰው አሻግሮ ለማየትና ለመነጋገር ይችላል። ከውስጥ ላለውና መውጣት ለሚፈልገው ግን መንገድ መዝጋቱ አይቀርም፤ እና ፈቀቅ እንበል።

መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 14 የካቲት 9 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here