. ግዢው በአገሪቷ ያጋጠመውን የስንዴ እጥረት ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል
በአገሪቷ ያጋጠመውን የስንዴ እጥረት ለመፍታትና ገበያ ለማረጋጋት ሦስት የውጭ ድርጀቶች በ3 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ስንዴ ለማቅረብ ከመንግሥት ጋር ስምምነት ደረሱ።
ስንዴው ለዳቦ ቤቶች እና ለፋብሪካዎች የሚከፋፈል መሆኑ የታወቀ ሲሆን በተለያዩ ከተሞች የታየው የዋጋ ለውጥ ለማስተካከል አዎንታዊ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል።
ጨረታውን ያሸነፉት ቡንጂ ኤስ ኤ፣ አምሮፓ እና ኤዲ ኤም አንተርናሽናል፤ በአጠቃላይ 400 ሺሕ ቶን ስንዴ ለማቅረብ ተስማምተዋል።
ቡንጂ ኤስ ኤ የተባለው የስዊዘርላንዱ ድርጅት 200 ሺሕ ቶን ስንዴ ለመግዛት ጨረታውን በማሸነፍ በአጠቃላይ 61 ሚሊየን ሰባት መቶ ሺሕ ዶላር ያቀረበ ሲሆን፤ ሌላኛው የጨረታው አሸናፊ አምሮፓ የተባለው አቅራቢ ድግሞ 100 ሺሕ ቶን ስንዴ ለማቅረብ በ30 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር ለማቅረብ ተስማምቷል። ቀሪውን 100 ሺሕ ቶን ለማስረከብ ያሸነፈው ኤዲ ኤም ኢንተርናሽናል የተባለ ድርጅት ሲሆን ያሸነፈበት ዋጋም 29 ሚሊየን 700 ሺሕ ዶላር መሆኑ ተረጋግጧል።
ጨረታውን ያሸነፉት ድርጅቶች ያቀረቡት ዋጋ በዓለም ዐቀፍ የጥራጥሬ ምክር ቤት ካስቀመጠው አማካኝ የስንዴ ዋጋ ጋር ሲነፃፀር ቡንጂ ኤስ ኤ አና ኤዲ ኤም ኢንተርናሽናል ያሸነፉበት ዋጋ በ57 የአሜሪካ ዶላር ብልጫ ሲኖረው፤ አምሮፓ የተባለው ድርጅት ያስገባው ዋጋ የ68 ነጥብ 47 የአሜሪካ ዶላር ብልጫ አለው።
በተያያዘም አፕላስ ኢምፖርተር የተባለው ድርጅት መንግሥት ገቢያን ለማረጋጋት የታሰበውን አራት መቶ ሺሕ ኩንታል ስንዴ ሦስት ቢሊየን ብር ለማቅረብ ትንሹን ዋጋ ቢያቅርብም ቅድመ ግመገማውን ባለሟሟላቱ ውድቅ መሆኑ ታወቀ።
ከተጫራቾቹ መካከል አንድ የሆነው አፕላስ ውድድሩን ለማሸነፍ ዝቅተኛ ዋጋ ያቀረበ ዋነኛው ድርጅት ቢሆንም ውድድሩን እንዳያሸንፍ ካደረጉት ነገሮች የድርጅቱ ንግድ ፍቃድ አለመካተቱ ነው። በአፕላስ ኢምፖርተር ስም የቀረበ ንግድ ፍቃድ አለመካቱትንም አዲስ ማለዳ ማረጋገጥ ችላለች።
እንዲሁም አፕላስ ኢምፖርተር እና አሮን ኃይሌ ሥም የገባው ንግድ ፍቃድ ሁለቱ ድርጅቶች ግንኙነት እንዳላቸው የሚያሳይ ሕጋዊ ሰነድ ስለሌለ እና ጨረታው ላይ የተወዳደሩት በሽርክና ስምምነት በመሆኑ እንዲሁም ድርጅቱ በመንግሥት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በአቅራቢነት ዝርዝር ውስጥ የተመዘገበው በኮንስትራክሽን ማቴሪያልስ አቅራቢነት ስለሆነ፤ ከውድድሩ ውጪ መሆኑን የመንግሥት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ምክትል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አሰፋ ሰለሞን ገልጸዋል።
በግዢና ንብረት አገልግሎት ኤጀንሲ ጥር 23 በተከፈተው ጨረታ ላይ ለመሳተፍ 38 ድርጅቶች ቢሳተፉም የተወዳደሩት ስምንት ድርጅቶች ብቻ መሆናቸው ይታወሳል።
ቅጽ 1 ቁጥር 14 የካቲት 9 ቀን 2011