‹ድኅረ ጦርነት› ውይይት እና ያልተቋጨው ጦርነት

0
1718

ቦግ እልም፣ ፈካ ጭልም የሚለው የኢትዮጵያ ሰላም የማግኘት ተስፋ አሁንም በዛው መንገድ የቀጠለ እንደውም ስጋቱ እያየለበት የመጣ ይመስላል። በሰሜኑ ክፍል አንድ ዓመት በላይ ካስቆጠረው ጦርነት ባለፈ በተቀሩት ሦስት አቅጣጫዎችም በተለያዩ አካባቢዎች በየእለቱ የንጹሐን ዜጎች ሕይወት ይቀጠፋል፤ ልጆች ያለአሳዳጊ፣ ወላጆች ያለጧሪ ይቀራሉ፣ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ይፈናቀላሉ ወዘተ።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሰሜኑ ክፍል የነበረው ጦርነት ‹አበቃለት!› ተብሎ ሲጠበቅ ነበር። መንግሥት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀውንና አማራ እንዲሁም አፋር ክልሎች ላይ ወረራ ፈጽሞ የቆየውን ሕወሓት እስከ መቀሌ ድረስ ገፍቶ ነገር ግን ወደ መቀሌ ሳይዘለቅ ባለበት ረግቶ እንዲቆይ ለሠራዊቱ ባስተላለፈው ትዕዛዝ መሠረት ጸንቶ ቆይቷል። ከሰሞኑ ታድያ የተለያዩ ምንጮች የሕወሓት ቡድኑ መልሶ ጥቃት እየሰነዘረ መሆኑን አስታውቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው ‹በዘላቂ ድል ወደ ብልጽግና፣ የድኅረ ጦርነት መዛነፎችና እርምቶቹ› የሚል ርዕስ ያለው ሰነድ ለውይይት መቅረቡ ይፋ የሆነው። ‹ጦርነቱ መች አበቃና!› ከሚሉ ጥያቄዎች ጀምሮ በጉዳዩ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችና ውዝግቦች ሲነሱ ሰንብተዋል።

የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ይህን ነጥብ በማንሳት ሰነዱ ምን ነጥቦችን እንዳካተተ፣ ባነሳዉ ዙሪያ የተነሱ ውዝግቦችንና የውይይቱ ተሳታፊ ከነበሩ የብልጽግና ፓርቲ አባላት የተገኙ አስተያየቶችን በማከል፣ የባለሞያዎችን አስተያየትም ጨምሮ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ነገር አድርጎታል።

በኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረውን የሰሜኑን ጦርነት ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ዓመታት ያስቆጠሩ ነገር ግን መቋጫ ያላገኙ ግጭቶች አሉ። የሰሜኑ ጦርነት በትግራይ ክልል፣ በአፋር እና በአማራ ክልሎች የተገደበ ሲሆን፣ በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ደግሞ እልባት ያላገኘው የታጣቂ ኃይሎች ጥቃት እንደቀጠለ ነው።

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚታዩት እና ዓመታት ያስቆጠሩት እነዚህ የጸጥታ ችግሮች ይህ ነው የሚባል መፍትሄ ሳያገኙ፣ ጥቀምት 24/2013 የጀመረው የሰሜኑ ጦርነት በተለያዩ ተለዋዋጭ ኹነቶች ዛሬ ድረስ ዘልቋል። በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በአማራ እና አፋር ክልሎች ወረራ መፈጸሙን ተከትሎ ለዓመት አካባቢ ከዘለቀ ውጊያ በኋላ ከወር በፊት በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ወደ ትግራይ እንዲመለስ መደረጉ የሚታወስ ነው።

ሕወሓት ወደ ትግራይ መመለሱን ተከትሎ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት እስከ ወረዳ የወረደ ‹በዘላቂ ድል ወደ ብልጽግና፣ የድኅረ ጦርነት መዛነፎችና እርምቶቹ› በሚል መሪ ቃል የድኅረ ጦርነት ውይይት አካሂዷል። የውይይቱ አጃንዳ በማዕከላዊ መንግሥት ተዘጋጅቶ ለክልሎች የተላለፈ እና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፤ ከፌዴራል እስከ ወረዳ የመከሩበት ነው።

የውይይት አጀንዳው በአብዛኛው ድኅረ ጦርነት ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ተከትሎ፤ ጦርነቱ እልባት ሳያገኝ መንግሥት ስለ ድኅር ጦርነት የውይይት ሰነድ አዘጋጅቶ በየደረጃው መምከሩ በብዙዎች ዘንድ ጥያቄ ፈጥሯል።

ከፌዴራል መንግሥት እስከ መጨረሻው የመንግሥት እርከን በተለይ የብልጽግና ፓርቲ አባላት በተዘጋጀው ‹የድኅረ ጦርነት መዛነፎችና እርምቶች› ሰነድ ውይይት መካሄዱ ያለፉት ኹለት ሳምንታት አጀንዳ ነበር። በመንግሥት በኩል የተካሄደው የድኅረ ጦርነት ውይይት በኹሉም ክልሎች እና በኹለቱም ከተማ አስተዳደሮች ያሉ ጉዳዮችን ያካተተ ሲሆን፣ በድኅረ ጦርነት ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ችግሮች እና መፍትሔዎች የሚያትት መሆኑን አዲስ ማለዳ ከሰነዱ እና በውይይቱ ከተሳተፉ የብልጽግና ፓርቲ አባላት አረጋግጣለች።

የድኅረ ጦርነት መወያያ ሰነዱ በፌዴራል መንግሥት ለየክልሎቹ የተላለፈ ሲሆን፣ ክልሎች በዋና ሰነዱ መሠረት የየራሳቸውን መወያያ ሰነድ አዘጋጅተው ከክልል እስከ ወረዳ የብልጽግና አባላትን አወያይተዋል። ይህ የድኅረ ጦርነት ውይይት በኢትዮጵያ ጎልቶ የሚታየው የሰሜኑ ጦርነት እና በቤኒሻንጉል ጉምዝ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ያለው የጸጥታ ችግር እልባት ሳያገኝ እየተካሄደ ያለ መሆኑ፣ በብዙዎች ዘንድ ጥያቄ ከመፍጠሩ ባለፈ አከራካሪም አጀንዳ ሆኗል።

ውይይቱ በዋናነት ጥያቄ የተነሳበት ጦርነቱ እልባት ሳያገኝ ቀድሞ በመነሳቱ ብቻ ሳይሆን በውይይት ሰነዱ በተነሱ ሐሳቦችም ጭምር ነው። ጦርነቱ እልባት ሳያገኝ ስለ ድኅር ጦርነት ማውራቱ ተገቢ አይደለም የሚሉ ትችቶችን የሚያነሱ አካላት፣ የሰሜኑ ጦርነት ሕወሓት ወደ ትግራይ በመመለሱ ተጠናቋል ለማለት የሚያስችል አለመሆኑን ያነሳሉ።

ሕወሓት ወደ ትግራይ ክልል መመለሱ እና በወረራ ተይዘው የነበሩ የአማራ እና የአፋር ክልል አካባቢዎች ነፃ መውጣታቸውን ተከተሎ መንግሥት ሕወሓትን ማሸነፉን ሲገልጽ መሰንበቱ የሚታወስ ነው። ሕወሓት በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ጥቃት ተሸንፎ ወደ ትግራይ ቢመለስም፣ አሁንም በአማራ እና በአፋር አዋሳኝ አካባቢዎች ውጊያዎች መኖራቸውን አዲስ ማለዳ በኹለቱም ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ ከሚገኙ ነዋሪዎች አረጋግጣለች።

ሕወሓት በኹለቱ ክልሎች አዋሳኝ ድንበሮች ላይ ዳግም በከፈተው ጥቃት በአማራ ክልል በራያ ቆቦ በኩል ከታህሳስ 19/2014 ጀምሮ ጥቃት መፈጸሙን አዲስ ማለዳ ከአካባቢው ነዋሪዎች ሰምታለች። በአፋር ክልል በኩል ደግሞ በኪልበቲ ረሱ በአብአላ በኩል ከታህሳስ 10/2014 ጀምሮ የተጠናከረ ጥቃት መክፈቱን የክልሉ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን መገልጹ የሚታወስ ነው።

ትግራይን በሚዋስኑ የአማራ እና የአፋር ክልል አካባቢዎች ሕወሓት የሚያደርሰው ጥቃት ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ ከተፈናቀሉበት ቦታ ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው የነበሩ ዜጎች ዳግመኛ እየተፈናቀሉ መሆኑን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች። ጦርነቱ እንደተጠናቀቀ የሚያመላክተው የመንግሥት የውይይት ሰነድ በሕወሓት በኩል ከሚደርሱ ጥቃቶች ጋር የማይጣጣም መሆኑን ብዙዎች እየገለጹ ነው።

በ“ድኅረ ጦርነት” ሰነዱ ምን ተመከረ?
በመንግሥት በኩል የተመከረበት ‹የድኅር ጦርነት› ሰነድ በብዙዎች ዘንድ መነጋጋሪያ አንጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል። ከፌዴራል እስከ ክልል የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና በየደረጃው የሚገኙ የብልጽግና አመራሮችና አባላት የመከሩበት ይኸው ሰነድ፣ ከፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የወረደ ቢሆንም፣ በዋና ሰነዱ መሠረት ክልሎች የየራሳቸውን ሰነድ አዘጋጅተው መክረዋል።

የተወሰኑ ክልሎች ውይይት ያደረጉበት ነው ተብሎ ሰነዱ ለሕዝብ መሰራጨቱን ተከትሎ፣ በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ውዝግብ ማስነሳቱ የሚታወስ ነው። ለሕዝብ የተሰራጨው ሰነድ ላይ የፌዴራል መንግሥት ባዘጋጀው ሰነድ ላይ የሌሉ ነገሮች የተካተቱበት መሆኑን፤ በተለይ ጥያቄ የበዛበት የአማራ ክልል መንግሥት ብልጽግና ፓርቲ አስተባብሏል።

በወሳኝነት ውይይቶቹ ከከፍተኛው አመራር እስከ ታችኛው አመራር ድረስ የደረሱና የተጠናቀቁ ሲሆን፤ በቀጣይም በተመሳሳይ ሁኔታ ወደ መላ ሕዝቡ የሚወርድ ይሆናል ተብሏል።

የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ በጉዳዩ ላይ ውዝግብ መፈጠሩን ተከትሎ ጥር 6/2014 ባወጣው መግለጫ ‹‹ለውይይት የሚሆን ሰነድ በማዕከል ደረጃ ተዘጋጅቶ የወረደ ሲሆን፤ ክልሎች ደግሞ የቀረበላቸውን ሰነድ መነሻ አድርገው ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ተነስተው የራሳቸውን ክልላዊ የመወያያ ሰነድ አዘጋጅተው ወደ ውይይት ገብተዋል። የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤትም በዚሁ አግባብ ከማዕከል የወረደውን መነሻ የውይይት ጽሑፍ መሰሠት አድርጎ፤ የአማራን ሕዝብ፣ ክልላዊ መንግሥትን እና መሪ ፓርቲው በዚህ ጦርነት የነበራቸውንና ዛሬም እያሳዩ ያለውን ተሳትፎ፤ በሂደቱ የተስተዋሉ ችግሮችና በቀጣይም ሊከተሏቸው ስለሚገባቸው አቅጣጫዎች በሚገባ ተንትኖ ወደ ውይይት ገብቷል።›› ብሏል።

ፓርቲው በመግለጫው የአማራን ሕዝብ መሪ ድርጅት እና መንግሥትን በተለያዩ አጀንዳዎች በመጥመድ በሴራ ፖለቲካ አገር በማመስ የጠላት አጋር የመሆን ዓላማ ያላቸው አካላት፣ ‹ውይይት እየተካሄደበት ያለውን ሰነድ አዛብተውና ከአውዱ ውጭ ኤዲት አድርገው› በማሰራጨት መሪውን ድርጅት እና የክልሉን መንግሥት እያብጠለጠሉ ነው ብሏል። ይሁን እንጂ እየተዘዋወረ ያለው ሰነድ በተለይም በአማራ ክልል ውይይት እየተካሄደበት ካለው ሰነድ የተለየ ነው ብሏል።

አዲስ ማለዳ ለሕዝብ የተሰራጨው ሰነድ ላይ የተካተቱ ጉዳዮችን የተመለከተች ሲሆን፣ ሰነዱ ስለ ሁሉም ክልሎች እና ስለ ኹለቱም ከተማ አስተዳደሮች ያሉ ስጋቶችን እና መፍትሔዎችን ያካተተ ነው። ሰነዱ በአማራ ክልል ውይይት ከተደረገበት ሰነድ ጋር ልዩነት አለው መባሉን ተከትሎ አዲስ ማለዳ በክልሉ የብልጽግና አባላት ባካሄዱት ውይይት ላይ የተነሱ ሐሳቦችን ከውይይቱ ተሳታፊዎች በዝርዝር አግኝታለች።

ሰነዱ ሆን ተብሎ የተስተካከለ እና ትክክለኛ ሰነድ አይደለም ያለው የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ በየደረጃው ከአባላቱ ጋር ባደረገው ውይይት፣ ስለ ሁሉም ክልሎች የድኅረ ጦርነት ችግሮች እና መፍትሔዎች በጽሑፍ ተዘጋጅቶ የቀረበበት መሆኑን አዲስ ማለዳ ከውይይቱ ተሳታፊዎች አረጋግጣለች። የክልሉ የብልጽግና አባላት ባካሄዱት ‹የድኅረ ጦርነት› ውይይት፣ ለውይይቱ ተሳታፊዎች ጦርነቱ መጠናቀቁን እና ሕወሓት ዳግም ወረራ የሚያደርግበት እና ለኢትዮጵያ ስጋት የሚሆንበት አቅም እንደሌለው እንደተገለጸላቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደገለጹት፤ በአማራ ክልል ወደፊት ስለሚኖረው የጸጥታ ሁኔታ የመከሩ ሲሆን፣ ጦርነቱ እንዳለቀ እና በድኅረ ጦርነት ወቅት ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ስጋቶች መክረዋል። ክልሉ በሕወሓት ወረራ ከፍተኛ ጉዳት እንዳስተናገደ በውይይቱ ላይ የተገለጸ ሲሆን፣ የተበዳይነት ስሜትን በማስቀረት ወደ መልሶ ግንባታ መግባት እንደሚገባ በውይይቱ ተነስቷል።

ክልሉ በየደረጃው ከብልጽግና አባላት ጋር ባካሄደው ውይይት ላይ ለውይይቱ ተሳታፊዎች ከቀረቡ ሐሳቦች መካከል ሰሞኑን አጀንዳ ሆኖ የከረመው የአማራ ሕዝባዊ ድርጅት (ፋኖ) ጉዳይ አንዱ ነው። በክልሉ በተካሄደው ውይይት በክልሉ በድኅረ ጦርነት ስለሚኖረው የጸጥታ ሁኔታ ሲነሳ ‹‹ከመደበኛ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ልዩ ኃይል፣ ፖሊስ እና ሚኒሻ ሲሆኑ፣ ፋኖ ኢ-መደበኛ ኃይል ነው ተብሏል›› ሲሉ በውይይቱ የተሳተፉ አዲስ ማለዳ ምንጮች ጠቁመዋል። በመሆኑ በፋኖ ስም ሰላም የሚያውኩ አካላት ስለሚኖሩ ከጦርነት በኋላ በሚኖረው የክልሉ ሁኔታ ኢ-መደበኛ ኃይል ሰላም እንዳያውክ ትጥቅ የማስፈታት ሂደት እንደሚኖር በውይይቱ ተነስቷል ተብሏል።

ከሰነዱ ውይይት በኋላ የክልሉ መንግሥት ፋኖን ትጥቅ ሊያስፈታ ነው ተብሎ አጀንዳ መሆኑን ተከትሎ ክልሉ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል። ክልሉ በሰጠው ማብራሪያ ፋኖን ትጥቅ የማስፈታት እቅድ እንደሌለው የገለጸ ሲሆን፣ በፋኖ ሥም ሰላም ለማወክ ይንቀሳቀሳል ያለውን አካል ክልሉ ከፋኖ ጋር በጋራ በመሥራትና በመከላከል ሰላም እንደሚያስከብር ገልጿል።

የሰሜኑ ጦርነት መንግሥት እንደሚለው ወይስ…?
የሰሜኑ ጦርነቱ በተለያዩ ተለዋዋጭ ኹነቶች ታጅቦ እስከ አሁን ድርስ እልባት ሳያገኝ የዘለቀ ጦርነት ነው። ሆኖም በተለይ ሕወሓት ወደ ትግራይ መመለሱን ተከትሎ፣ ‹ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት የመጀመሪያ ምዕራፍ› በመንግሥት አሸነፊነት መጠናቀቁ በመንግሥት በኩል ተገልጿል። ይህንኑ ተከትሎ መንግሥት ድኅረ ጦርነት ሰነድ አዘጋጅቶ ውይይት አካሄዷል።

የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ‹በዘላቂ ድል ወደ ብልጽግና፤ የድኅረ ጦርነት መዛነፎችና እርምቶች› በሚል ርዕስ በተዘጋጀው ሰነድ ላይ ባካሄዱት ውይይት ‹‹በኢትዮጵያዊያን አሸናፊነት የተጠናቀቀው የዘመቻ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የመጀመሪያ ምዕራፍ በሌሎች ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ድሎች በሚጠናከርባቸው አቅጣጫዎች ላይ መክረዋል›› ሲል ፓርቲው መግለጹ የሚታወስ ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በመንግሥት በኩል በ‹ድኅረ ጦርነት› ውይይት ላይም ይሁን በሌላ ሁኔታ ጦርነቱ እንዳለቀ ተደርጎ የሚቀርብበት ሁኔታ በብዙዎች ዘንድ ጥያቄ እየተነሳበት ይገኛል። በጉዳዩ ላይ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት መምህር ‹‹የሕወሓት ወደ ትግራይ መመለስ ጦርነቱ አልቋል ማለት አይደለም።›› ይላሉ።

የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ እንደሚሉት የሰሜኑ ጦርነት አልቋል ሊባል የሚችለው በኃይል ወይም በሰላማዊ መንገድ መቋጫ ሲያገኝ እና ዳግም ሊቀሰቀስ የሚችልበት ሁኔታ አለመኖሩ ሲረጋገጥ ነው። ይሁን እንጂ በመንግሥት በኩል የሚነገሩ የአሸናፊነት እና የድኅረ ጦርነት ውይይት በሰላማዊ መንገድ ወይም በኃይል መቋጫ ባላገኘ ጦርነት ላይ የተሳሳተ ግንዛቤ የሚፈጥር ነው።›› ብለውታል።

መንግሥት በየደረጃው ባካሄደው ‹ድኅረ ጦርነት› ውይይት ላይ ስለ ጦርነቱ በኢትዮጵያ አሸናፊነት የተጠናቀቀ እና ቀጣዩ ሥራ የመልሶ ግንባታ እና ዘላቂ ሰላም መፍጠር መሆኑ መግለጹ፣ ሕወሓት በአፋር እና በአማራ ክልሎች የሚያደርገውን ትንኮሳ ያላገናዘበ መሆኑንም ብዙዎች እየገለጹ ይገኛሉ።

ሕወሓት ወደ ትግራይ ቢመለስም በኹለቱ ክልሎች አሳዋኝ አካባቢዎች አሁንም ጥቃት እየፈጸመ መሆኑ እና ወደ ትግራይ የሚላኩ ሰብዓዊ እርዳታዎችን ጉዞዎችን እያስተጓጎለ መሆኑ እየተገለጸ ነው። ታዲያ ሕወሓት ዳግም የጦርነት ትንኮሳ በጀመረበት እና ጦርነቱ እልባት ባላገኘበት ሁኔታ ጦርነቱ እንዳለቀ አደርጎ ማቅረብ ለከፋ ችግር እንደሚዳርግም ብዙዎች እያሳሰቡ ነው።

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ሕወሓት ያለበት ሁኔታ እና በመንግሥት በኩል ጦርነቱ እንዳለቀ ተደርጎ የሚሳልበት ሁኔታ፣ ሕዝብን ከማዘናጋት በተጨማሪ ለዳግም ወረራ የሚዳርግ ነው ይላሉ። በተለይ የጦርነቱ ገፈት ቀማሽ የሆነው የአፋር እና የአማራ ክልል ሕዝብ ከደረሰበት ጉደት ሳያገግም በሕወሓት ዳግም ወረራ ከተፈጸመበት ችግሩ የከፋ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

መንግሥት ጦርነቱ እንዳለቀ አድርጎ ወደ ሕዝብ የሚያሰራጫቸው መረጃዎች መሬት ላይ ያለውን ሀቅ ያገናዘቡ አይደሉም የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ፣ ጦርነቱ በኃይልም ይሁን በሰላማዊ ሁኔታ እልባት ማግኘት እንዳለበት ጠቁመዋል። ነገር ግን ሕወሓት በትግራይ ክልል ዝግጅት እያደረገ ነው እንደሚባለው ዳግም ወረራ ከጀመረ የጦርነት ሰላባ ለሆነውና ለሚሆነው ለአማራ እና ለአፋር ክልል ሕዝብ ብቻ ሳይሆን እንደ አገር ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር ችግሩ ውስብስብ እና አክሳሪ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

ከጦርነት በኋላ ስለሚኖሩ ሁኔታዎች መንግሥት ያካሄደው ውይይት በራሱ ጦርነቱ እንዳለቀ አድርጎ የመረዳት ዝንባሌ እንደሚታይበት የገለጹት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ፣ በሕዝቡ በኩል በተለይ የጦርነት ሰለባ በሆነ ማኅበረሰብ እና በመንግሥት መካከል አለመተማመን እና ጥርጣሬ የፈጠረ ነው ብለውታል።

‹የድኅረ ጦርነት› ሰነዱ በአንዳንድ የውይይቱ ተሳታፊዎች ተቃውሞ እንደገጠመው አዲስ ማለዳ ሰምታለች። አዲስ ማለዳ በአዲስ አበባ እና በአማራ ክልል በተደረጉ ውይይቶች ላይ ከተሳተፉ ሰዎች ያገኘችው መረጃ እንደሚያሳየው “የድኅረ ጦርነት” ውይይቱ ተሳታፊዎች በአንድ ድምጽ ያልተስማሙበት ሆኗል።

የውይይት ሰነዱ ከገጠሙት ተቃውሞዎች መካከል ‹‹ጦርነቱ ሳያልቅ ስለ ድኅረ ጦርነት ማውራት ተገቢ አይደለም›› የሚለው በአብዛኛው የውይይት ተሳታፊ ጥያቄ የተነሳበት መሆኑን አዲስ ማለዳ ውይይቱ ከተሳተፉ ከአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ አባላት ሰምታለች። የውይይቱ ተሳታፊዎች ሕወሓት ለዳግም ጦርነት እየተዘጋጀ ባለበት ሁኔታ ስለ ‹ድኅረ ጦርነት› ከማውራት ይልቅ ጦርነቱን ማጠናቀቅ ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት በውይይቱ ወቅት መግለጻቸው ተሰምቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 168 ጥር 14 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here