“የትልልቅ ሰዎችን ታሪክ መሰነድ፤ ነገ ትልቅ ሥራ የሚሠሩ አገር ተረካቢዎችን ለማፍራት ይረዳል” አንዱዓለም አባተ (የአፀደ ልጅ) (ፒ.ኤች.ዲ.)

0
1006

ሦስቱ ትዝታዎች፣ የሕሊና መንገድ፣ ንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብ የሚል ርዕስ ያላቸው የአጫጭር ልብወለድና ታሪኮች ስብስብ፣ መኢኒት የተሰኘ በመኢኒት ማኅበረሰብ ትውፊት ላይ መሠረት ያደረገ ልብወለድ እንዲሁም የረዘመ ትንፋሽ እና ፍቅርና መዳፍ የተሰኙ የግጥም መጻሕፍትን ለአንባብያን አድርሷል። በኢትዮጵያ ቴሌዥቭን ጨምሮ በተለያዩ ጣቢያዎች በርካታ የቴሌቭዥን ድራማዎችን ጽፎ አዘጋጅቷል፤ በራድዮንም የተላለፉለት በርካታ ናቸው። በአዲስ አበባ ራስ ቴአትር ‹ረጃጅም ጥላ› እና ‹ሞት በቀጠሮ› የሚል ርዕስ ያላቸው ቴአትሮች ታይተውለታል። የአፀደ ልጅ አንዱዓለም አባተ (ፒ.ኤች.ዲ.)

አንዱዓለም በ1996 ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ዲፕሎማና በ2002 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቴአትር ጥበባት በዲግሪ በኋላም ኹለተኛ ዲግሪውን በሥነጽሑፍና ፎክሎር ተቀብሏል። በቅርቡም ከዛው ዩኒቨርሲቲ በአፈታሪክ (Mythology) ሦስተኛ ዲግሪውን አጠናቋል። ከተማርካቸው ከሠራህባቸውና ከምትሠራባቸውም ሙያዎች የትኛው ይበልጥብሀል ብለው ለሚጠይቁት፣ ‹ከሰውነት አካልህ የትኛው ያስፈልግሃል እንደመባል ነው› የሚል መልስ ይሰጣል።

‹‹የሚመጣልኝን ሐሳብ በምን መንገድ ላስተላልፍ የሚለውን ነው የማስበው።›› ይላል። ስለዚህም ሐሳቦችን ይናገራቸዋል፣ በግጥም ያሰናኛቸዋል፣ በተውኔት ገጻ ባህሪያት አንደበት ላይ ያኖራቸዋል… ወዘተ። ያኔ ሐሳቡም ቅርጽ እንደሚይዝ ይናገራል።

ብርቱና ታታሪ፤ ቁምነገረኛ ደግሞ ጨዋታ አዋቂም ነው። ባሳለፍነው ዓመት መጨረሻ ላይ የአርበኛና ሐኪም ማሞ ኃይሌን የሕይወት ታሪክ የሰነደ መጽሐፍ ለንባብ አብቅቷል። ‹የአርበኛና ሐኪም ማሞ ኃይሌ የሕይወት ታሪክ› የሚል ርዕስ ያለው ይህ መጽሐፍ ታድያ ዛሬ ቅዳሜ (ጥር 14/2014) ጠዋት ሦስት ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ቴአትር በድምቀት ይመረቃል።

ይህንን የመጽሐፍ ምርቃት መነሻ ምክንያት በማድረግ፣ የመጽሐፉ አዘጋጅ አንዱዓለም አባተ ከአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጋር ባደረገው አጠር ያለ ቆይታ፣ በመጽሐፉ ዝግጅት ዙሪያ እንዲሁም ወቅታዊ ጉዳዮችን አንስቷል።

በቅድሚያ እንኳን ደስ አለህ፣ እንኳን አደረሰህ!
አመሠግናለሁ! እንኳን አብሮ አደረሰን!

አንዱዓለም ከዚህ ቀደም የግጥምና የልብወለድ እንዲሁም የቴአትር ሥራዎችን አበርክተሃል። ከቀደሙ የመጽሐፍ ሥራዎችህ አንጻር ይህኛው የግለሰብ ታሪክ ነውና በዘውግ ይለያል። ፈታኝ አልነበረም?
አዎን! እንዳልሽው መጽሐፉ ግለታሪክ ነው። ኹለተኛ ነገር ደግሞ በግለታሪኩም ጉዳይ ባለቤቱ በሕይወት የሉም። ባለቤቱ በሌሉበት ነው ግለታሪኩ የተጻፈው። እና ታሪኩን የተሟላ ለማድረግ ሌሎች ጥናትና ምርምሮችን፣ ብዙ ፍተሻዎችን እና ቃለመጠይቆችን ማድረግ ያስፈልጋል። ከዛም ላይ መሠረት ተደርጎ የተጻፈው የባለታሪኩ መረጃ ስለሆነ፣ እሱን የማመሳከርና መረጃን የማጣራት ነገርም በተመሳሳይ ጊዜ የጠየቀ ሂደት ነው።

ከዛ ውጪ ግን ግለታሪኮች ብዙ ጊዜ የአንድን ሰው ሕይወት፣ ከልደት እስከ መጨረሻው ኅልፈት ድረስ ያለውን ነገር ስለሚያሟሉ፣ በተቻለ መጠን እነዚህ ነገሮች እንዳይጎድሉ ተደርጎ የተሠራ ነው።

የጠቀስካቸውን መንገዶች አልፎ ለአንባብያን ለማድረስ ምን ያህል ጊዜ ወሰደ?
አንድ ዓመት ወስዶብኛል። አንዱ ጥሩ ነገር ይህ ግለታሪክ መጀመሪያ ሌላ ደራሲ ሊሠራው ጀምሮት ብዙ መረጃዎች ሰብስቦ፣ በርካታ ቃለመጠይቆችንና ቀረጻዎችን አድርጎ ነበር። በኋላ እኔ ሥራውን ስጀምር፤ የደራሲውን ማንነት አውቄ፣ ለምን እንዳቋረጠ ጠይቄ ስላልቻልኩኝ ነው ስላለኝና ደግሞም ስለጠየቅኩትም ክብር ተሰምቶት እሱ የሰበሰባቸውን መረጃዎችና ቃለመጠይቆች ሁሉ ሰጥቶኛል። ይህም ሥራውን በተወሰነ መንገድ አግዟል። በጽሑፍ ደረጃ ግን ዓመት ነው የወሰደው።

በመጽሐፉ ዝግጅት ሂደት ላይ ስታነብብ እንዲሁም ስትሰማ የተደነቅክበትና ያልተሰማ አዲስ ነገር ያገኘኸው ነበር?
እንደሚታወቀው ከ1928 እስከ 1933 ኹለተኛው የፈሽስት ጣልያን ወረራ በነበረ ጊዜ፣ በአገር በተለያየ አካባቢ ከፍተኛ ተጋድሎ ተደርጓል። በተለይ አርበኛና የባህል ሐኪም ማሞ ኃይሌ የነበሩበት ቡልጋ፣ በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠር አርበኛ የነበረበት አካባቢ ነው። በኋላም እነ ራስ አበበ አረጋይ የመጡበት ነው።

በተለይ ደጃዝማች ፍቅረማርያም በማይጨው ጦርነት ከመጡ በኋላ ቡልጋ አካባቢ ነበር የሰፈሩት። እና እዛ አካባቢ ማለትም ከአንኮበር እስከ ምንጃር ድረስ ያለው አጠቃላይ የከሰምን በረሃ ይዘው የነበሩት አርበኞች ተጋድሎ እጅግ በጣም ብዙ ያልተነገረለት ነው። ያላወቅናቸውም ብዙ ጀግኖች አሉ። ለምሳሌ ባላምባራስ ኃይሌ የተባለ ጀግና አለ። (ገድሉ የመጽሐፉ ምረቃ እለት በድራማ መልክ ይቀርባል) ይህንን አርበኛና የባህል ሐኪም ማሞ ኃይሌ ዘግበው በማስቀመጣቸውና እኔም አብራርቼ በመጻፌ፣ በታሪክ ፊት አዲስ ያላወቅናቸውን ጀግና አውቀናል።

ባላምባራስ ኃይሌ የቻለውን ያህል ከተዋጋ በኋላ መሣሪያም ስለጨረሰ፣ ጣልያኖች በባንዳዎች ተመርተው እጁን እንዲሰጥ አደረጉ። ከዛ በኋላ በቤተሰቦቹ ፊት ማንነቱን አረጋግጠው፣ ብዙ ጣልያን ገድሎብናል ብለው ገደሉት። መግደል ብቻ አይደለም፣ አንገቱን ቆርጠው ከምንጃር ሸንኮራ፣ ከሸንኮራ ደብረዘይት፣ ከደብረዘይት ሞጆ፤ ያም አልበቃ ብሏቸው አዲስ አበባ ድረስ አንገቱን መኪና ላይ አንጠልጥለው አዙረዉታል። ይህን ያደረጉት የአርበኞችን ትግል ለማኮላሸት ነው።

እና እንዲህ ያሉ ጀግኖችን አናውቃቸውም ነበር። እነዚህ ሰዎች ዛሬ እንደ አገር እንደዜጋ እኛ ነጻነት አለን፣ በነጻነት ነው የኖርነው፣ አልተገዛንም ስንል በየጉድባው እንዲህ አንገታቸው የተቆረጠና ለነጻነታችን ዋጋ የከፈሉ ናቸው። መጽሐፉ እንዲህ ያሉ በታሪክ ፊት ያልታዩት ጎልተው እንዲወጡ አድርጓል።

በሌላ በኩል ጣልያን ከ160 በላይ አብያተ ክርስትያናን አቃጥሏል። እነዚህን ሁሉ ኃይሌ ማሞ ዘግበዉታል። እና ብዙ ታሪክ ሰንደው በማስቀመጣቸው ይህ መጽሐፍ መውጣቱ በታሪክ ፊት ያላወቅናቸውን አዳዲስ ነገሮች እንድናይ አድርጎናል/ያደርገናል።

እንደ መጽሐፉ አዘጋጅ፤ አርበኝነትን በተመለከተስ ይህ መጽሐፍ የሰጠህ አዲስ ዕይታ አለ?
አዎን! ለምሳሌ አርበኞች በጊዜው አዲስ አበባን ነጻ ለማውጣት አቅደው ነበር። እነ ደጃዝማች ፍቅረማርያም ከቡልጋ፣ በእነ አቡነ ጴጥሮስ የሚመራው በሌላ አቅጣጫ እንዲሁም ከአምቦ በኩል የነበሩት አዲስ አበባን ነጻ የማውጣት እቅድ ነበራቸው። በተለይ በደጃዝማች ፍቅረማርያም (አባ ተጫኔ) የተመራው ጦር እንዴት ብሎ እንደመጣ፣ የት እንደደረሰና እንዴት ተዋግቶ እንደወጣ በትክክል በስፍራው በጊዜው ስለነበሩ በትክክል ጽፈውታል።

ከዛ በኋላም የሽንፈቶቻችን ምስጢር ምን እንደነበር፤ በተለይ የአርበኞች እርስ በእርስ ውጊያ፣ የባንዳዎች ሥራም በጣም ተገልጦበታል። ከጣልያን በላይ የጎዳን እርስ በእርስ ውጊያ እና በባንዳ እየተመራ ጀግኖች ያሉበት እየደረሰ ጠላት ያመጣው ጥፋት፣ ትልቅና አዲስ ዕይታን ይሰጣል።

ከመጽሐፉ ጉዳይ ሳንወጣ፤ መታወቅ ያለበትና አንባቢዎች እንዲህ ካሉ የታሪክ መጽሐፍት የሚያገኙት የምትለው ምን አለ?
ትልልቆችን ማንሳት ለእኛ ለትንንሾቹ አረአያ የሚሆኑ ሰዎችን ማምጣት ነው። ይህ ትውልድ ዝም ብሎ ተነስ ሲሉት የሚነሳ፣ ጩኽ ሲሉት የሚጮኽ፣ ይህ ነው ሲሉት የሚቀበል እንዳይሆን፤ ምክንያታዊ የሆነ አገር የሚረከብ ትውልድ ለማፍራት ማንበብና የሚነበብ ነገሮችን ተጋግዞ ማምጣት ያስፈልጋል። ከዚህ አንጻር የጽሑፉ ዓለም የሚታገዝበትን መንገድ መፈለግ አማራጭ የሌለው ነገር ነው።

ኹለተኛ እንዲህ ያሉ የተከበሩ ሰዎችን፣ ለምሳሌ ጋሽ ማሞ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በነጻ ያከሙ ናቸው። ከአርበኝነታቸው በላይ በባህል ሕክምና ከነገሥታት እስከ ተራው ሰው አክመዋል። በነገራችን ላይ ራሳቸው ጋሽ ማሞ እግራቸው ሊቆረጥ ነበር፣ ከ1933 በኋላ በ1937 እግራቸው እንዲቆረጥ በሆስፒታል ተወስኖ ነበር። ግን ከንጉሡ ጋር ከውጪ የመጣ ሐኪም ነው እንዳይቆረጡ ያደረገውና ያዳናቸው። ከዛ በኋላ እርሳቸው የባለቤታቸው ወንድም እግር ይቆረጥ ተብሎ፣ ‹እግሩ አይቆረጥም፤ አድነዋለሁ› ብለው እርሳቸውም አክመውታል።

ከዛም ባለፈ ዛሬ የእርሳቸው ተረካቢ የሆነ ዶክተር ግሩም የሚባል ሰው አለ። ዶክተር ግሩም አሁን ሜዲካል ዶክተር ነው፣ እንደገና የባህል ሐኪምም ነው። ይህ ሰው አስቀድሞ በልጅነቱ ኹለት የተለያዩ የመንግሥት ሆስታሎች እግሩ ይቆረጥ ብለው ነበር። ነገር ግን እርሳቸው ‹እኔ አድነዋለሁ፣ ልጁን ግን አልሰጥም አስተምረዋለሁ።› ብለው አዳኑት። ዛሬ ያ ልጅ ሜዲካል ዶክተርና የባህል ሐኪም ነው። እንዲህ ያለ ነገር ሰጥተውናል።

ሌላው አልማዝ ባለጭራ፤ አልማዝ በምትባል ሴት ምክንያት ነው የተሰየመው። እርሷ ገላ ላይ የሆነ ጭራ ነገር አዩ፤ ወርቃማ ነው። ይህን በሽታ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር ያዩት፤ አዳኗት። እና ሌላ ሰው በዛው በሽታ ተይዞ እርሳቸው ጋር ሲቀርብ ‹እንደ አልማዝ ጭራ አለው› ከሚለው ነው አልማዝ ባለጭራ የመጣው። እና እንዲህ ያሉ ትልልቅ ሰዎችን ታሪክ መሰነድና ለአሁኑ ትውልድ ማሳየት፣ ማቆየት፤ ነገ ትልልቅ ወጣትና ትልቅ ሥራ የሚሠሩ አገር የሚረከቡና የሚመሩ ወጣቶችን ለማፍራት ይረዳል።

እንደሚታወቀው የመጻሕፍት ዋጋ ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ ነው፤ የሕትመት ነገርም ከባድና ፈታኝ መሆኑ እየበረታ እንደሆነ ይነገራል። ምን መደረግ አለበት ትላለህ? ይህንን ለማስተካከልስ ማን ነው ትልቅ ድርሻ ያለው?
ዞሬ ዞሬ ከመንግሥት ራስ አልወርድም። ያን የማላደርገው ብዙ ጊዜ እንደምለው ቀድሞ የባህል ፖሊሲ አልነበረብንም። አሁን ግን የተወሰነ ጉድለት ቢኖረውን ጠንካራና ጥሩ የሚባል የባህል ፖሊሲ አለን። ይህን ፖሊሲ ወደመሬት ማውረድና ተፈጻሚ ማድረግ ያስፈልጋል። በባህል ፖሊሲ ላይ ያሉ የአገርን ባህል፣ ኪነጥበብ፣ ሥነጥበብና መልካም እሴቶች ሊያጎሉ የሚችሉ ነገሮችና ባህልና ቱሪዝም ካልሠራ፣ ካላወረደ ብናወራው መፍትሄ አይሆንም። ምክንያቱም እንደቅንጦት እየታየ ነው ያለው።

አሁን ከመጽሐፍ የተሻለ ጫት ዋጋ የሚያወጣበት ዘመን ላይ ነው ያለነው። ወረቀት ቫት የለውም፤ ነገር ግን ከደራሲው ይልቅ ነጋዴው ነው የሚጠቀመው። አንድ ደራሲ ራሱ ጽፎ፣ ራሱ አሳትሞና ራሱ ተሸክሞ ሰጥቷቸው እነርሱ 40 በመቶ ይወስዳሉ። ይህ እንዴት ሊቀጥልና ደራሲ እንዴት ሊበረታታ ይችላል?
አንድ ወጥ የሆነ ስርዓት እስካልተበጀ ድረስ፣ የሆነ ቦታ ላይ በድንገት ለውጥ ልናመጣ አንችልም። አንደኛ በዚህ ሰንሰለት ያለ ሁሉ መደጋገፍና መተዛዛን አለበት። ደራሲው፣ አሳታሚው፣ ነጋዴው፣ ቸርቻሪው፣ አዟሪው፤ እነዚህ ሁሉ በዚህ ሰንሰለት ውስጥ ነው ያሉት፤ አስፈላጊም ናቸው። ከዛ የተነሳ በመተዛዘን ሁሉም የድርሻውን ማግኘት መቻል አለበት።

የወረቀትና የህትመት ጉዳይ እንዳልሽው በጣም ከባድ ሆኗል። ይህን መንግሥት ነው በባህል ፖሊሲ እየደገፈ ማስተካከል የሚችለው። እንደውም ጥሩ ጥሩ መጻሕፍት ቢተዋወቁ፣ የሚሸጡበት መንገድ ቢዘረጋ፣ መንግሥት ለሚያስፈልጋቸው ተቋማት ትምህርት ቤቶችም ጭምር እንዲገዙ በማድረግ ቢደግፍ ይቻላል። የሆነ ስርዓት ቢፈጠር ለውጥ ይመጣል።

አንድ የሱዳን ደራሲ አንድ መጽሐፍ ካወጣ፣ ባለቤትና ባለመኪና ነው የሚሆነው። የህትመት ዋጋውን 10 በመቶ እጥፍ ገንዘብ ያገኛል። እኛ አገር ያ አይታሰብም። ሰዉ ለህትመት ዋጋው እንጂ ለአእምሮው ውጤት አይከፍልም። ስለዚህ የህትመት ዋጋን መንግሥት ነው ሊያስብበት የሚገባው። በሆነ ግለሰብና ተቋም ብቻ ለውጥ አይመጣም። ይሁነኝ ተብሎ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው።

ወደ ወቅታዊ ጉዳይ ላምጣህ፣ አሁን በአገራችን የጋራ የምክክር መድረክ፣ እርቅ ወዘተ የሚሉ ጉዳዮች ሲነሱ እንሰማለን። መንግሥትም ምክክርና እርቅን እያነሳ ነው። በበኩልህ በተለያየ ብሔረሰብ የባህል የእርቅ ስርዓት ዙሪያ ያደረግካቸው ጥናቶች አሉና፤ በዚህ ላይ ምን ሊታሰብ ይገባል ትላለህ?
ወቅቱ ብዙ ጥንቃቄ የሚፈልግ፣ ብዙ ነገዎችን ማሰብና በጣም ጥልቅ ትዕግስትን የሚጠይቅ ነው። በተለይ ባህላዊ የእርቅ አሠራርን ስናይ፣ ባህላዊ የእርቅ አፈታት ስርዓት ትልቁ ቁምነገሩ ወንጀለኛን አይደብቅም። ስርዓቱ ወንጀለኛን ለፍርድ ከማቅረብ ወደኋለ አይልም። ነገር ግን ጸብ፣ ደምና መገዳደል እንዳይቀጥል የእርቅ ስርዓቱ ደም ያደርቃል። ጸቡ እንዳይቀጥልና እንዳይተላለፍ የማድረግ ትልቅ ሚና አለው። ነገር ግን ወንጀለኛን በአግባቡ በፍትህ ይቀጣል።

እናም ይህን አገር በቀል የሆነ፣ በባህል፣ በአባቶችና በሽማግሎች የተቃኘውን ባህላዊ የእርቅ ስርዓት በትክክል ወደ መሬት ማውረድ በጣም ያስፈልጋል። ፓርላማ የተቀመጡ ብቻ ሕግና ስርዓት እንዲህና እንዲያ ነው ከማለት በዘለለ፣ ተፈጻሚ የሚሆነው ሕዝብ ውስጥ ስለሆነና ሕዝብም ይህን የሚያደርግበት የራሱ የሆነ ጠንካራና ዘመናት የኖረበት እሴቶች ስላሉት፣ እሱን መሠረት ማድረግ በጣም ወሳኝ ነው።

ለምሳሌ በአፄ ምኒልክና በአፄ ዩሐንስ መካከል ከፍተኛ ጦርነት ሊነሳ ነበር፤ ያኔ። የንጉሠ ነገሥትና የንጉሥነት ጥያቄ ነው። ያንን ጦርነት ፍቼ ላይ፣ የፍቼ ስምምነት በሚባለው ያበረዱት የአንኮበር ካህናትና የደብረሊባኖስ ካህናት ናቸው። ይህም የሃይማኖት አባቶችና ሸማግሎች ያላቸውን ሚና የምናይበት ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት የጋሞ አባቶችን ማየት ይቻላል። የጋሞ አባቶች መሬት ተንበርከክው ቄጠማ ይዘው ጸብ አብርደዋል።

ስለዚህ ባህላዊ የእርቅ ስርዓቱ ላይ መሠረት ማድረግ ጠቃሚ ነገር ነው። ሌላው ግን ባህላዊ እርቅ ስርዓት እንዳልኩት ወንጀለኛን ሳይቀጣ አያልፍም። በወንጀል መጠየቅ ያለባቸው አካላት መጠየቅ አለባቸው፤ ላጠፉት ጥፋት መጠየቅ ይኖርባቸዋል። ነገር ግን ቂሙ እንዳይተላለፍና ለትውልድ እንዳይሻገር የእርቅ ስርዓቱ በሰዎች የእርስ በእርስ መስተጋብር ውስጥ ጤናማ ግንኙነት ለመፍጠርና አገር ለመሥራት እርቁ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው።

በመጨረሻ ከቴአትሩ ምነው ጠፋህ? ቀጣይስ ምን እንጠብቅ?
ረጅም ዓመት በትምህርትና በምርምር ነው ያሳለፍኩት። ግን ምንም ጥርጥር የለውም፤ በተለያዩ ሥራዎች መምጣቴ አይቀርም። በሰፊው ስመጣ ባወራው ይሻላል። ከመጽሐፍ ጋር ተያይዞ ግን ወርልድ ቪዥን አሸንፌ የምሠራው አንድ ሥራ ነበር። የ1977 ድርቅን መሠረት ያደረገ ታሪካዊ ልብወለድ አለ፣ እርሱ አሁን አልቆ ኢንግሊዘኛው ተተርጉሞ በቅርቡ ማተሚያ ቤት ይገባል፤ በኹለቱም ቋንቋ። ኢትዮጵያ ከ1977 በኋላ ከብርሃኑ ዘሪሁን መጽሐፍ በኋላ በጉዳዩ ላይ ያተኮረ መጽሐፍ የላትም። ይህ አንድ ጥቅም ነው የሚሆነው።

ሌላው የዘርዓ ያዕቅብ ሕይወትና ሥራዎቹ የሚል ደብረብርሃን ከሚኖር ቴዎድሮስ ደመቀ ከሚባል ጓደኛዬ ጋር ያዘጋጀነው የኢትዮጵያ መካከለኛ ዘመንን መሠረት ያደረገ ትልቅ መጽሐፍ፣ ተጠናቆ እርሱም ወደ ማተሚያ ቤት የሚገባበትን መንገድ እያመቻቸን ነው። በዚህ በቅርቡ መምጣቴ አይቀርም።


ቅጽ 4 ቁጥር 168 ጥር 14 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here