በአዲስ አበባ የግንባታ ፈቃድ ገደብ ከተነሳ በኋላ የሲሚንቶ ዋጋ በኩንታል 100 ብር ጭማሪ አሳየ

0
813

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሕንፃ ግንባታ ዘርፍ ጋር የተያያዙ መሬት ነክ አገልግሎቶች ላይ ጥሎት የነበረውን እገዳ ማንሳቱን ተከትሎ የሲሚንቶ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

እገዳው በተነሳ አንድ ወር ውስጥ ብቻ አንድ ኩንታል ሲሚንቶ ዋጋ ላይ ከ100 ብር በላይ ጭማሪ የታየ መሆኑን ነው የሲሚንቶ ገዥዎች የሚገልጹት። አዲስ ማለዳም በአዲስ አባባ የተለያዩ የሲሚንቶ መሸጫ ቦታዎች ተዘዋውራ ባደረገችው ምልከታ መሠረት፣ የተለያዩ ፋብሪካዎች ውጤት የሆኑ ሲሚንቶዎች በኩንታል ከስድስት መቶ ሀምሳ እስከ ስድስት መቶ ሰማንያ ብር ሲጠራ ተመልክታለች።

ሥሜ ባይጠቀስ ያሉ አንድ የሲሚንቶ አከፋፋይ ግለሰብ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ቀደም ብሎ የተለያዩ የሲሚንቶ ዓይነቶችን ያከፋፍሉ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ግን በእጃቸው ያለው ኢትዮ ሲሚንቶ ብቻ ሲሆን እሱም የሚሸጠው 680 ብር ነው። አያይዘውም ከኹለት ሳምንት በፊት አንድ ኩንታል ሲሚንቶ እስከ ሰባት መቶ ብር ይሸጥ እንደነበርና በየሳምንቱ የዋጋ መውጣት እና መውረድ እንደሚስተዋል ነው ሻጩ የገለጹት።

ግለሰቡ አክለውም ከፍተኛ የሆነ የሲሚንቶ እጥረት ተፈጥሯል ካሉ በኋላ፣ ‹‹በዚህም የተነሳ ብዙዎቻችን ሲሚንቶ ስላጣን ጅብሰም ነው የምንሸጠው።›› ብለዋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሌላኛው የሲሚንቶ አከፋፋይ ተስፋሁን ደረጀ እንዲሁ፣ ሲሚንቶ ለመግዛት ለፋብሪካ ቅድሚያ ክፍያ ብዙ ብር ከፍለው ለረዥም ጊዜ ቢጠብቁም ሲሚንቶ ማግኘት እንዳልቻሉና ብሩም እንዳልተመለሰላቸው ገልጸዋል። አክለውም ፋብሪካዎች የብዙ ነጋዴዎች እዳ እንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት።

ተስፋሁን ከዚህ በተጓዳኝ ቀበሌዎች በሚሠሩት ወጥነት የሌለው አሠራር ተማረናል ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። ‹‹ድንገት ይመጡና ሲሚንቶ በውድ ዋጋ ትሸጣላችሁ ሲባል ሰምተናል በማለት ሊያሽጉብን ይሞክራሉ።›› ብለዋል።

የግንባታ ፈቃድ በተከለከለበት ወቅት የሲሚንቶ ዋጋ ከ450 እስከ 500 ብር እንደነበር አዲስ ማለዳ ከአከፋፋዮች ማረጋገጥ ችላለች።

ከዚያ በፊትም መንግሥት ቀደም ባለው ጊዜ የሲሚንቶ ገበያን ወደ ነጻ ገበያ አሰራር በቀየረበትና አከፋፋዮች እና ቸርቻሪዎች ከፋብሪካዎች በቀጥታ በመገናኘት የሚፈልጉትን ያህል ምርት በሚፈልጉበት ዋጋ እንዲገዙ ባደረገበት ወቅትም እንዲሁ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቶ እንደነበር ይታወሳል።

በአሁኑ ሰዓትም መንግሥት ቀድም ብሎ ከፈቀደው ነጻ ገበያ ጋር ተያይዞ፤ ጥቅማቸው የተነካባቸው፣ እሴት የማይጨምሩ፣ በመሀል ጣልቃ የሚገቡ ደላሎች የሲሚንቶ እጥረት እና የዋጋ መናር እንዲፈጠር አድርገዋል የሚሉ ቅሬታዎች ይቀርባሉ። በዚህም ምክንያት የሲሚንቶ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረ ሲሆን፣ እጥረቱም በዚያው ልክ ነው ተብሏል።

የግንባታ ባለሙያ የሆኑት ቸርነት ታሪኩ በበኩላቸው፣ ቀደም ብሎ በግንባታ ፍቃድ መከልከል የተነሳ አሁን ደግሞ በሲሚንቶ ዋጋ መናር ምክንያት የግንባታ ሥራ በመቀዛቀዙ ሥራ አጥተው እንደተቸገሩ ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በሲሚንቶ ዋጋ መናር እንዲሁም እጥረት ምክንያት ትልልቅ የግንባታ ድርጅቶች ተጎጂ ከመሆናቸውም በላይ፣ የብዙ ዜጎችን ሕይወት እንደሚያቃውስ እና ለአገራዊ ዕድገት መጓተትም ያለው ድርሻ የጎላ መሆኑን ባለሙያው ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ከነሐሴ 7/2013 ጀምሮ በመሬት አስተዳደር ተቋማት፣ በመሠረተ ልማት ቅንጅትና ግንባታ ፈቃድ ባለሥልጣን እንዲሁም በሁሉም ክፍለ ከተሞች፤ የመሬት እና መሬት ነክ አገልግሎቶች ላልተወሰነ ጊዜ ሙሉ በሙሉ እንዳይሰጡ ውሳኔ ማስተላለፉ የሚታወስ ነው። ይህም እገዳ ካሳለፍነው ታህሳስ 14/2014 ጀምሮ መነሳቱን ከተማ አስተዳደሩ ማሳወቁ አይዘነጋም።


ቅጽ 4 ቁጥር 168 ጥር 14 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here