ሐሙስ የካቲት 3 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የ6 ወራት የአስተዳደሩን ሪፖርት በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።
ከንቲባዋ በምክር ቤት ሪፖርት ካነሷቸው ዋና ዋና የአፈፃፀም ነጥቦች ውስጥ፡-
*ከተማችንን ነዋሪ በማስተባበር እንዲሁም የፀጥታ ሃይሉ ከሰላም ወዳዱ ህዝባችን ጋር በመሆን በተደረገው የሰላም ማስከበር እንቅስቃሴ የጥፋት ሴራን በመቆጣጠር የከተማችንን ሰላም ማስጠበቅ ተችሏል፡፡
*እኔ ለከተማዬ ሰላም ዘብ ነኝ’’ በሚል መሪ ቃል ለአካባቢያቸው ሰለም ዘብ በመቆም የከተማችን ሰላም እንዲረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ተወጥተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር 24 ሺህ የሚሆኑ የከተማችን ወጣቶች የህልውና ዘመቻውን በመቀላቀል የበኩላቸውን ሚና ተወጥተዋል፡፡
*400 የጤና ባለሙያዎች ወደተለያዩ የጦር ግንባሮች በማምራት ሙያዊ ሀላፊነታቸውን ከመወጣት በተጨማሪ በህውሃት ቡድን የወደሙ 18 የጤና ተቋማትን መልሶ በማቋቋም የተለያዩ የህክምና መድሃኒቶችንና መሳሪያዎችን በመላክ ከፍተኛ ድጋፍ ተደርጓል፡፡
*የአዲስ አበባ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፤ የዘማች አርሶ አደርና ሚሊሻ ቤተሰቦችን የደረሰ ሰብል ለመሰብሰብ 30 ሺህ የሚሆኑ መምህራንና ተማሪዎች ለአንድ ሳምንት በሰብል ስብሰባ በተለያዩ አካባቢዎች ድጋፋቸውንና አጋርነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
*ከ11ንዱም ክፍለ ከተሞች ግንባሮችን በመከፋፈልና የበሰለ ትኩስ ምግብና ቁሳቁሶችን ለሰራዊቱ በማቀበል ሰራዊቱን የማበረታታትና የማጀገን ሀላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ ተደርጓል፡፡
*የአስፈጻሚ አካላት ስልጣንና ተግባራት እንደገና ለመወስን የከተማ አስተዳደሩ ባካሄደው የመዋቅር ማሻሻያ ጥናት መሠረት አዋጅ ቁጥር 74/2014 በዚሁ ምክርቤት ፀድቆ 71 የነበሩትን የመንግስት ተቋማት ወደ 46 በመቀነስ መልሶ የማደራጀት ስራ ተሰርቷል፡፡
*ለየት ያለ ፖለቲካ አስተሳሰብ ያለውም የህዝብ ድምጽ በአስፈፃሚው እንዲወከል በመስራት ከከተማ ካቢኔ ጀምሮ እስከታች ባሉ መንግስታዊ አደረጃጀት በቁጥር በከተማ ደረጃ 2 በክፍለ ከተማ ደረጃ 9 የሚደርሱ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች በሃላፊነት እንዲመሩ ተድርጓል፡፡
*በተጨማሪም በአመራር ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ 32 በመቶ የደረሰ ሲሆን በምክር ቤታችንም 49 በመቶ ማድረስ ተችሏል፡፡
*መዲናችን አዲስ አበባን የሽብርና የሁከት ማዕከል በማድረግ ሀገርን ለማፍረስ የተያዙ እኩይ እቅዶችና ሙከራዎችን ሁሉ እንዲመከኑ ማድረግ ተችሏል፡፡ ለአብነትም በፍተሻ፣ በብርበራና ተጥለው የተያዙ የቡድንና የነፍስ ወከፍ 850 የጦር መሣሪያዎችን ከ314 ሺህ 188 ጥይቶች ጋር እንዲሁም 88 የጦር ሜዳ መነፅር፣ 84 መገናኛ ሬዲዮ፣ 2 የጦር ኮምፖስ እና 6 ጂፒኤስ መያዝ ተችሏል፡፡
*በተጨማሪም ለሽብር ተግባር ሊውል የተዘጋጀን ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጋ የተለያዩ ሀገራት የውጪ ሀገር ገንዘቦች እና ከ10 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ብርም በቁጥጥር ሥር እንዲውል ተደርጓል፡፡
*በግማሽ አመቱ ለ227 ሺህ 500 ሥራ ፈላጊዎች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ297 ሺህ 696 (131 በመቶ) ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል፡፡
*ለ1,514 ኢንተርፕራይዞች የካፒታል አቅማቸውን ለማሳደግ ከ449 ሚሊዮን ብር ብድር ለመስጠት ታቅዶ 269 ሚሊዮን 247 ሺህ ብር (60 በመቶ) ብድር ተሰጥቷል፤
*በአገር ውስጥ ገበያ ለ9 ሺህ 478 ኢንተርፕራይዞች 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር የገበያ ትስስር ለመፍጠር ታቅዶ ለ8 ሺህ 141 ኢንተርፕራይዞች የ 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የገበያ ትስስር ተፈጥሯል፡፡
*ትላልቅ (ሜጋ) ፕሮጀክቶች ግንባታ አፈፃፀም በተመለከተ፤ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ፤ በ19 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ተገንብቶ በቅርቡ የተመረቀው የአብርሆት ዘመናዊ ቤተ-መፃህፍት፤ በተቀመጠለት ጊዜና በጀት በፍጥነትም ሆነ በጥራት የመጨረስ አቅማችንን በድጋሚ ያረጋገጠ ትልቅ ፕሮጀክት ነው፡፡
*ከ57 ዓመት በላይ ያሰቆጠረው የመዘጋጃ ቤት ህንፃ፤ የቀድሞ ታሪካዊ ቅርፅን ሳይቀይር በ2.2 ቢሊዮን ብር የእድሳት ግንባታ ስራው ዘመናዊ ሆኖ ተጠናቆ ለምርቃት በቅቷል፡፡ ይህ ታሪካዊና የከተማዋ ምልክት የሆነው የህንፃ እድሳት የከተማዋ የዘመናት ጉዞ አሻራ የያዘ ታላቅ ቅርስ ጭምር የሆነው ህንፃው ከተማዋ አለም ከደረሰበት የከተሞች እድገትና ውበትን በማላበስ ለተገልጋይ ምቹና አስፈላጊ አገልግሎቶችን ሁሉ ባሟላ መንገድ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ እንዲሆንና አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ተደርጐ በከፍተኛ ጥረት እድሳቱ ተጠናቋል።
*በ4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በጀት እየተገነባ ያለው የአድዋ ዜሮ ኪሎ ሜትር ሙዝየም ፕሮጀክት፤ በግማሽ ዓመቱ የግንባታ አፈፃፀም 60 በመቶ ከነበረበት ወደ 74 ነጥብ 5 በመቶ ማድረስ የተቻለ ሲሆን፤ የታላቁ ቤተ-መንግሥት የመኪና ማቆሚያ ግንባታ ከነበረበት 83 በመቶ ወደ 85 ነጥብ 1 በመቶ ማድረስ ተችሏል፡፡
*በምግብ ዋስትና እና በልማታዊ ሴፍትኔት መርሃ ግብር 109 ሺህ 918 ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡
* በመጀመሪያው ምዕራፍ በምግብ ዋስትና ተጠቃሚ የነበሩ 49 ሺህ 205 የቤተሰብ ኃላፊዎች ተመርቀው ወደ ዘላቂ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራም እንዲሸጋገሩ ማድረግ ተችሏል፡፡
*በየሳምንቱ የእሁድ ገበያን በተለያዩ የከተማዋ 14 ቦታዎች በማቅረብ እንዲሁም የመሰረታዊ ፍጆታ ሸቀጦች ለከተማ ነዋሪ በአነስተኛ ዋጋ በማቅረብ የኑሮ ውድነት ችግር ለማቃለል ተሞክሯል፡፡
*የአስተዳደሩ ካቢኔ ቀደምሲል ከተሰጠው 500 ሚሊየን ተዘዋዋሪ ብድር በተጨማሪ የ500 ሚሊዮን ብር ሪቮልቪይንግ ፈንድ መድቦ የሸማች ማህበራት የፋይናንስ ችግሮቻቸውን በማቃለል በህብረተሰቡ የሚደርሰውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና አቃሏል፡፡
*በተጨማሪም ለህብረተሰቡ በድጎማ የሚቀርበውን ዳቦ በስፋት ተደራሽ ለማድረግ ለሸገር ዳቦ ፋብሪካ 309 ሚሊዮን 337 ሺህ ብር ድጎማ ተደርጓል፡፡
*የመሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን አቅርቦት በተመለከተ ባለፉት ስድስት ወራት 508 ሺህ 912 ኩንታል ስኳር፤ 170 ሺህ 352 ጥሬ ስንዴ እና ከ12 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይት ለሸማቹ ህብረተሰብ ማሰራጨት ተችሏል፡፡
*የከተማችንን ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ባደረግነው እንቅስቃሴ ለ899 የኢንቨስትመንት ፍቃድ ተሰጥቷል፡፡
*ገቢ ባለፉት ስድስት ወራት 26 ነጥብ 53 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ 31 ነጥብ 45 (118 ነጥብ 5 በመቶ) ቢሊዮን ብር መሰብሰብ የተቻለ ሲሆን፤ አፈፃፀም ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 8 ቢሊዮን ብር ብልጫ ወይም በ35 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡
*1 ነጥብ 75 ቢሊዮን ብር በጀት እየተገነባ ያለው የትራንስፖርት ቢሮ (ጂ+20) ሕንፃ ግንባታ ከነበረበት 27 ነጥብ 2 በመቶ ወደ 35 በመቶ እንዲሁም 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በጀት እየተገነባ ያለው የስልጠና ማእከል ግንባታ ከነበረበት 38 በመቶ ወደ 40 ነጥብ 5 በመቶ ደርሷል የሚሉት እንደሚገኙበት ኤ ኤም ኤን ዘግቧል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n






