በስድስት ወር ውስጥ 17ሺሕ 756 ሠዎች ኤች አይ ቪ ተገኘባቸው

0
1217

በ2014 የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ምርመራ ከተደረገላቸው ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች መካከል 17ሺ 756 ሰዎች (0.5 በመቶዎቹ) በደማቸው ውስጥ የኤች አይ ቪ ኤድስ እንደተገኘባቸው የፌደራል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት የዕቅድ ክትትልና ግምገማ ተወካይ አብነት አሰፋ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በስድስት ወር ውስጥ በአገሪቱ በሚገኙ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በጠቅላላው ሦስት ሚሊዮን 258 ሺሕ 778 የሚሆኑ ሰዎችን ለመመርመር ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ ከታቀደው ውስጥም ሦስት ሚሊዮን 547 ሺሕ 831 ሰዎች ምርመራ አድርገው፣ 17 ሺሕ 756 ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው ታውቋል።

በ2014 ግማሽ ዓመት ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሠዎች ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር እንደየአካባቢው ከፍና ዝቅ ማለቱን ለማወቅ በእርግጠኝነት አልተቻለም የተባለ ሲሆን፣ ይህም የሆነው በትግራይ ክልል ያለውን ትክክለኛ ቁጥር ማወቅ ባለመቻሉም እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል።

ተወካዩዋ አክለውም፣ አገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ኹኔታ አንጻር የ2014 ግማሽ ዓመት ሪፖርት ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የዘንድሮው እንደሚቀንስ ይታወቃል ነው ያሉት።
አያይዘውም፣ የዘንድሮውን የስድስት ወር ቁጥር ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር በማነጻጻር ቁጥሩ የቀነሰበት ወይም የጨመረበት ምክንያቱን ማቅረብ እንደሚያስቸግርም አልደበቁም።

በግማሽ ዓመቱ በየክልሎቹ የኤች አይ ቪ ምርመራ ሲደረግ በአፋር ክልል 318፣ በአማራ ክልል ሦስት ሺሕ 192፣ በኦሮሚያ ክልል ስድስት ሺሕ 560፣ በሱማሌ ክልል 227፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል 83 ሰዎች ኤች አይ ቪ በደማቸው ተኝቷል ተብሏል።

እንዲሁም፣ በደቡብ ክልል አንድ ሺሕ 969፣ በጋምቤላ ክልል 323፣ በሐረሪ 129፣ ሲዳማ ክልል 460፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አራት ሺሕ 296 እና በዴሬዳዋ ከተማ አስተዳዳር 199 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፣ በትግራይ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ምንም ዓይነት ዕቅድም ሆነ ምርመራ ማድረግ አልተቻለም ነው የተባለው።

በዕቅዱ መሠረትም ተጋላጭ ተኮር የምርመራ አገልግሎት በአገር አቀፍ ደረጃ አፈጻጸሙ ከፍተኛ ቢሆንም፣ የቤኒሻንጉል እና የጋምቤላ ክልሎች በጣም ዝቅተኛ አፈጻጸም ማስመዝገባቸውን አብነት ለአዲስ ማለዳ በላኩት ሪፖርት ማረጋገጥ ተችሏል።

በሌላ በኩል፣ የአማራ፣ የሶማሌ እና የአፋር ክልሎች መካከለኛ አፈጻጸም አስመዝግበዋል። የጋምቤላ ክልል በምርመራ ደረጃ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ቢሆንም፣ የምርመራና ምክር አገልግሎት ካገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ኤች አይ ቪ በደማቸው የተገኘ ሰዎች መጠን ግን ከፍተኛ በመሆኑ ተጋላጭ ተኮር የምርመራ አገልግሎት አፈጻጸማቸዉን በሚገባ በማሻሻል ውጤታማነቱን ከፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተመላክቷል።

ከዚህም በተጨማሪ፣ በበጀት ዓመቱ በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት 443 ሺሕ 658 አዋቂዎች (ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በላይ) እና 21 ሺሕ 188 ሕጻናት (0-14 ዓመት) በጥቅሉ 464 ሺሕ 846 ሰዎች የፀረ-ኤች አይ ቪ መድኃኒት እንዲወስዱ ለማድረግ ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ በዚህም 362 ሺሕ 635 አዋቂዎች እና 11 ሺሕ 992 ሕጻናት በድምሩ 374 ሺሕ 627 ሰዎችን በማዳረስ ከዕቅዱ አንፃር 80.6% ማከናወን መቻሉን ለማወቅ ተችሏል።

በአገር አቀፍ ደረጃ የፀረ-ኤች አይ ቪ ሕክምና አገልግሎት አፈጻጸሙ ከዕቅድ አንፃር ከፍተኛ ቢሆንም፣ የፀረ-ኤች አይ ቪ መድኃኒት የሚወስዱ 21 ሺሕ 118 ሕጻናት (0-14 ዓመት) መድኃኒት እንዲወስዱ ቢታቀድም አፈጻጸሙ 11 ሺሕ 992 በመሆኑ ከዕቅዱ ለመድረስ ዝቅተኛ ነው ተብሏል።

በመሆኑም፣ በተለይ በጸጥታ ችግር ምክንያት ዝቅተኛ አፈጻጸም ያላቸው ክልሎች መድኃኒታቸውን ለማቋረጥ የተገደዱ ዜጎች መልሰው እንዲጀምሩ በማድረጉ በኩል በቀጣይ የተጠናከረ ሥራ በመሥራት የአገልግሎቱን ሽፋን ለማሻሻል የሚያግዙ አሠራሮችን መዘርጋት እንደሚያስፈልግም ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ ባለፈው ዐሥር ዓመት ባደረገችው የኤች አይ ቪ ሥርጭትን የመከላከል ተግባር ውጤታማ አፈጻጸም አስመዝግባለች። በ2020 መጨረሻ ላይ በተሠራው “HIV Estimation and Projection” መሠረት አገራዊ የኤች አይቪ ሥርጭት ምጣኔ በአዋቂዎች (15-49) 0.86 በመቶ ሲሆን፣ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ብዛት 622 ሺሕ 326 መሆኑ ይነገራል።

ከእነዚህም ውስጥ 44 ሺሕ 138 የሚሆኑት ደግሞ ከ15 ዓመት በታች የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሕጻናት ናቸው።

ተመሳሳይ ጽሑፍ 

ሲዘነጉት የማይዘነጋው ኤች አይ ቪ ኤድስ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)

በከተሞች ያለው የኤች አይ ቪ ሥርጭት መጠን በገጠር ካለው በሰባት እጥፍ እንደሚልቅ ተገለጸ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)

10ከኤች አይ ቪ ኤድስ ጋር የሚኖሩ ዜጎች ያሉባቸው ቀዳሚ 10 አገራት – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)


ቅጽ 4 ቁጥር 171 የካቲት 5 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here