ሱማሌ ክልል በተከሠተው ድርቅ ከ683 ሺሕ በላይ የቤት እንስሳት ሞተዋል

0
1295

-ከ60 ሺሕ በላይ አባወራዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል

በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል በተከሠተው ድርቅ ምክንያት እስካሁን ከ683 ሺሕ በላይ የቤት እንስሳት መሞታቸውን የክልሉ አደጋ ሥጋት አመራር ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

በዚህም እስከ ጥር 30/2014 ባለው ጊዜ ብቻ 683 ሺሕ 465 የቤት እንስሳት መሞታቸውን ነው ቢሮው ያሳወቀው። የቢሮው የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን ኃላፊ በሽር አረብ እንደገለጹትም፣ 32 ሺሕ 729 ግመሎች፣ 188 ሺሕ 242 ከብቶች፣ 442 ሺሕ 628 ፍየሎች፣ እንዲሁም 19 ሺሕ 866 አህያዎች በድርቁ ሳቢያ በክልሉ የሞቱ የቤት እንስሳት ናቸው። የቦረና ዞን አጎራባች በሆነው ዳዋ ዞን የሞቱት የቤት እንስሳት ብቻ ከ447 ሺሕ በላይ ሲሆኑ፣ በአፍዴራና ሸበሌ ዞኖችም እንዲሁ ብዙ የቤት እንስሳት ማለቃቸውን ተናግረዋል።

ድርቁ በዐሥር ዞኖች፣ በ84 ወረዳዎች እና በአንድ ሺሕ 776 ቀበሌዎች የተከሠተ ሲሆን፣ በተለይ በዘጠኙ ዞኖች ከፍተኛ የውኃ ዕጥረት አጋጥሟል ነው የተባለው። ከክልሉ መልክዓ-ምድራዊ ሥፋት እንጻርም ውኃ በቦቴ ለማቅረብ መንገዶች ምቹ ባለመሆናቸው እና ያሉት የውኃ ጉድጓዶችም በቁጥር ትንሽ ከመሆናቸው ባለፈ በ100 ኪሎሜትር ገደማ ርቀት ላይ ስለሚገኙ፣ ድርቁ እያስከተለ ያለው ጉዳት ጥልቅ እንደሆነ ኃላፊው ገልጸዋል።

በዚህም፣ አንድ ቀበሌ በወር አንድ ጊዜ ቢበዛ ደግሞ ኹለት ጊዜ ውኃ እንደሚያገኝ ገልጸው፣ በአጠቃላይም ሦስት ሚሊዮን 200 ሺሕ ሕዝብ የውኃ ዕጥረት እንዳጋጠመው ነው የጠቆሙት። አያይዘውም፣ ሱማሌ ክልል 50 ሚሊዮን የሚጠጋ የእንስሳት ሀብት ያለው ቢሆንም፣ አሁን ላይ ወደ 6 ሚሊዮን የሚጠጉ የቤት እንስሳት የሞት አደጋ ተጋርጦባቸዋል ሲሉ አመላክተዋል።

85 በመቶ የሚሆነው የክልሉ ማኅበረሠብ የዕለት ምግቡንና ሌላ ወጪውን የሚሸፍነው የቤት እንስሳቶቹን ሽጦ በመሆኑ፣ አሁን ላይ ያሉት እንስሳት በመጎሳቆላቸውና ዋጋ የማያወጡ በመሆኑ ወደ ኹለት ሚሊዮን 400 ሺሕ ሕዝብ የዕለት ምግብ ዕርዳታ እየተጠባበቀ እንደሚገኝ ነው ያስረዱት።

ከዚህም ውስጥ እስካሁን የምግብ ዕርዳታ ማድረስ የተቻለው ለ589 ሺሕ 176 ዜጎች ብቻ ነው ያሉት ኃላፊው፣ ከችግሩ ጥልቀት የተነሳ እየቀረበ ያለው ዕርዳታ በቂ አለመሆኑን ለፌደራል መንግሥትና ለዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች አሳውቀናል ብለዋል። እስካሁን ዕርዳታ ይዞ የቀረበ ዓለም አቀፍ ድርጅት አለመኖሩንም እግረ መንገዳቸውን ጠቁመዋል።

እንዲሁም፣ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለከብቶቻቸው ውኃና ግጦሽ ፍለጋ ወደ 60 ሺሕ 305 አባዎራዎች፣ ከአንድ ሚሊዮን 500 ሺሕ በላይ የቤት እንስሳቶቻቸውን ይዘው ጅግጅጋ አካባቢ መስፈራቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ ብዙ የቤት እንስሳትም መንገድ ላይ እንደሚሞቱ አውስተዋል።

እስካሁንም በ41 ወረዳዎች ለሚገኙ አርብቶ አደሮች 20 ኪሎ ግራም የሚመዝን 89 ሺሕ እስር የከብት መኖ ማድረስ መቻሉንም አክለው አንስተዋል። በ159 ቦቴዎችም ድርቁ በበረታባቸው 73 ወረዳዎች ለሚገኙ ሰዎችና ቤት እንስሳት ውኃ እየቀረበ እንደሆነም ነው አይይዘው የጠቆሙት።

ድርቁ እስከ ሚያዝያ ወር ተባብሶ እንደሚቀጥል ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት ያሉት ኃላፊው፣ በድርቁ ምክንያት በክልሉ የደረሰውን ጉዳት ለማወቅ ጥናት እየተደረገ መሆኑን እና እንዳለቀም ይፋ እንደሚደረግ ሳይጠቅሱ አላለፉም።

በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት እንደገለጸው፣ በኢትዮጵያ እየጨመረ በመጣው ድርቅ ሳቢያ ከ6.8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ይሻሉ። እንደ ድርጅቱ ገለጻ በድርቁ ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባቸው የኦሮሚያ፣ ሱማሌ ክልሎች ወደ 225,000 የሚጠጉ ሕፃናት፣ እንዲሁም ከ100,000 በላይ ነፍሰ ጡር እና የሚያጠቡ እናቶች ለተመጣጠነ የምግብ ዕጥረት ተጋልጠዋል።

መረጃዎች እንደሚጠቁመትም፣ በቦረና የተከሠተው ድርቅ ምንም መሻሻል ያላሳየ ሲሆን፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በድርቁ የተነሳ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ከብቶች አልቀዋል። እስካሁን በዞኑ ወደ 262 ሺሕ ከብቶች የሞቱ ሲሆን፣ ከ280 ሺሕ በላይ ከብቶች ደግሞ በሰው ጉልበት እንደሚነሱ ነው የተገለጸው።

ተመሳሳይ ጽሑፍ

በሱማሌ ክልል ፋፋን እና ሲቲ ዞኖች ከፍተኛ ምርት መታጣቱ ተገለጸ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)

በሱማሌ ክልል በተከሠተው ድርቅ የዱር እንስሳት ለአደጋ መጋለጣቸው ተገለጸ – Addis Maleda

በሱማሌ ክልል የተከሠተው ድርቅ ተባብሶ ሊቀጥል ይችላል ተባለ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)


ቅጽ 4 ቁጥር 171 የካቲት 5 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here