መድኃኒትን የሚቋቋሙ ተዋኅስያንን ለማጥፋት የተፈጠረ የመጀመሪያው ጥምረት

0
836

በሽታዎች በሰው ልጆት ላይ መከሠት ከጀመሩ ከጥንት ጀምሮ መድኃኒታቸውም ሲፈለግ ተኑሯል። ለአንዱ የሠራ ለሌላውም እንዲያገለግል ሕክምናው ከልጅ ወደ ልጅ ሲተላለፍ፣ በሽታ አምጪ ኅዋሳቶቹ ደግሞ ከሠው ወደ ሠው እየተላለፉ፣ አሊያም እንስሳት ላይ እየቆዩ ወይም የመጡበት ሳይታወቅ እንደአዲስ እየተከሠቱ የሠው ልጆችንም ሆነ እንስሳትን ሲፈጁ ኖረዋል።

ዘመናዊ የሕክምና ሒደት ከመጀመሩ አስቀድሞ ሥራ ሥርንና ቅጠላ ቅጠልን በመጠቀም፣ አሊያም የእንስሳት ተዋጽዖዎችን አገልግሎት ላይ በማዋል ሕክምና ሲሠጥ፣ ታማሚዎች ከሕመማቸው ድነው እንዲያገግሙ ሲደረግ ዘመናት አልፈዋል። የሕክምና ሒደቱ ዓመታትን ሲያስቆጥር ሥርዓት እየተበጀለት በጽሑፍም እየሠፈረ በትምህርት መልክ በሥፋት ሲሠጥ ቆይቷል።

ከአምስት መቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ ተመራማሪዎችና ፈላስፋዎች የተለያዩ በሽታዎችን በማጥናት መድኃኒት የሚሆንላቸውንና የሚታከሙበትን፣ እንዲሁም የሚከላከሉበትን መንገድ በሙከራ ማወቅ ችለዋል። ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በሙከራ የሚጣራውና ታውቆ ሕክምና የሚሠጥበት መንገድ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲኖረው የተለያዩ ጉባዔዎችና መድረኮች ተመቻችተው፣ አንዱ የሌላውን አንዲያውቅ ልምድ እንዲለዋወጡና ሙያው እንዲዳብር ተደርጓል።

በሕክምናው ዘርፍ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተገኘ ለውጥና የታየው መሻሻል ከመቼውም ጊዜ የሚወዳደር ባይሆንም፣ ‹ማይክሮስኮፕ› የተፈበረከ ሠሞን የተገኘ ውጤትን ያህል ሥር-ነቀል ለውጥ እንዳልመጣ ግን ይነገራል። በሽታው ካልታወቀ መድኃኒቱ ሊገኝ እንደማይችለው፣ በዓይን የማይታዩ ኅዋሳትን ለመለየትም ሆነ ባሕሪያቸውን አውቆ መከላከያቸውንም ሆነ መጥፊያቸውን ለማበጀት፣ የአጉሊ መነጸሩ ጥቅም ላይ መዋል ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክቶ ነበር።

በ16ኛው ክፍለዘመን መነጸር ሠሪ የሆኑ አባትና ልጅ ለመጀመሪያ ጊዚ የፈበረኩት ማይክሮስኮፕ፣ ከብዙ ዓመታት በኋላ ነበር ለሕክምናው ዘርፍ አስተዋጽዖ ያበረከተው። የሠው ልጅን ለበሽታ የሚዳርጉ ተዋኅስያንን በመለየት መድኃኒታቸውንም በዘመናዊ መልኩ ለማምረት የተቻለበት ወቅት ከዛ ጊዜ በኋላ ቀስ በቀስ ነበር የተከሠተው። ይህን የሕክምና ወርቃማ ጊዜ ተጠቅመው በርካቶች ለተለያዩ በሽታዎች እስካሁን ድረስ የሚያገለግሉ የሕክምና ዘዴዎችንና መድኃኒቶችን እንዳገኙ ይታወቃል።

ጥቅም ላይ ከዋሉ በርካታ ዓመታት ከሞላቸው መድኃኒቶች መካከል ከመጀመሪያዎቹ የፀረ-ተዋኅስያን ወይም አንቲ ባዮቲክ መድኃኒቶች መካከል ቀዳሚው በፈረንጆቹ 1928 የተገኘው ‹ፔኒሲሊን› እንደሆነ ይታወቃል። በ1909 ለአባለዘር በሽታ ማከሚያ የሚሆን መድኃኒት ተገኝቶ የነበረ ሲሆን፣ በተለምዶ ግን ብዙዎች የሚያውቁት በአሌክሳንደር ፍሌሚንግ የተገኘውን ፔኒሲሊንን ነው። ይህ መድኃኒት ለረጅም ጊዜ በመላው ዓለም እያገለገለ ከቆየ በኋላ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ውጤጣማነቱ ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ቆይቷል።

ፔኒሲሊንን እና ሌሎች ፀረ-ተዋኅስያንን የሚቋቋሙ ዝርያዎች ብቅ በማለታቸው ሒደቱ በዚሁ ቀጥሎ ሌላ ዓይነት መድኃኒት ማግኘት ካልተቻለ ለሠው ልጆች አደገኛ እንደሚሆን ሲነገር ቆይቷል። ተመራማሪዎች፣ የሕክምና ባለሙያዎችና የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች በየፊናቸው ለውጡን ለመቀልበስና አዲስ መድኃኒት ለማግኘት ደፋ ቀና ሲሉ ቆይተዋል። ልፋታቸው ግን እስካሁን ውጤት ባለማምጣቱ አዲስ ዘዴና መንገድን መከተል እንደሚገባቸው ሲመከር ቆይቷል።

የኮቪድ ወረርሽኝ መከሠትና ከብዙ ድካም በኋላ መከላከያው ተገኝቶ ውጤታማ አለመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎችን ያስጨነቀ ጉዳይ ነበር። ቫይረሱ ባህሪውን በቀያየረ ቁጥር መከላከያውን መቋቋም መቻሉ ኹሌ በአንድ ዓይነት መንገድ መተማመን እንደማይቻል ያመላከተ በመሆኑ ችግሩ ተመራማሪዎችን ያቀራረበ ነበር። ከወረርሽኙ ሥጋትና ሒደት በመማር ለሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ሕክምናቸው አስቀድሞ መዘጋጀት እንደሚገባ ያመኑ የተለያየ አካላት ጥምረት መፍጠር እንዳለባቸው አምነው በቅርቡ ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችላቸውን ዕርምጃ ጀምረዋል።

መቀመጫውን እንግሊዝ ያደረገው ‹ቢዝነስ ዋየር› እንዳስነበበው፣ ከዚህ ቀደም ሆኖ በማያውቅ መልኩ የሕክምና ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎችና በሕክምናው ዘርፍ ላይ በአምራችነትም ሆነ በአገልግሎት መስጠት ዘርፍ የተሠማሩ ተቀናጅተውና በጋራ ሆነው ለውጥ የሚያመጣ መፍትሔን ለመፈለግ መዘጋጀታቸውን አሳውቋል። የኮቪድ 19 መከሠት የሠው ልጆችን የሚያጠቁ ተዋኅስያንን ለመቆጣጠር አዲስ መንገድና አደረጃጀት እንደሚያስፈልግ የተረዱት እነዚህ አካላት፣ ይበልጥ ትኩረት ማድረግ የፈለጉት ለዘመናት ስንገለገልባቸው የነበሩ ‹አንቲባዮቲኮች› ላይ ነው።

የፀረ-ተዋኅስያን መድኃኒቶችን የሚቋቋሙ የበሽታ አምጪ ዝርያዎች መበራከታቸውን በማስመልከት በቅርብ ጊዜ ለችግሩ መፍትሔ ካልተገኘ ቀላል ይባሉ የነበሩ ጭምር ጅምላ ገዳይ ሊሆኑ እንደሚችሉ ታምኖበታል። “ድብቁ ወረርሽኝ” እያሉ የሚገልፁት ይህ መድኃኒትን የመቋቋም ችግር ሥር ከሠደደ ቀጣዩ የዓለማችን አስጨናቂ የጤና ጉዳይ ይሆናል በሚል ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ። ይህ እንዳይሆን ወጥ የሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ መደረግ ያለበት አስገዳጅ መመሪያ መኖር ይኖርበታል ሲሉም ይሞግታሉ። በሽታ አምጪ ኅዋሳቱን ለይቶ ከማወቅ ጀምሮ፣ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይዛመቱ መቆጣጠር የሚቻልበትን መንገድ ለማወቅና ተግባራዊ ለማድረግ እንዲሁም፣ አስቀድሞ ለመከላከልና ሕክምናውን ለመስጠት የሚያስችል ተግባር ለማከናወን ኹሌም ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ እንደሚገባ ጥምረቱን ያስተዋወቁት አካላት ተናግረዋል።

‹ኢንፌክሽን ማኔጅመንት ኮአሊሽን(IMC)› የተሠኘው አዲሱ ጥምረት፣ ለወቅታዊ ወረርሽኞች ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት በሽታ አምጪዎችን ለማወቅ፣ ለመከታተል፣ ለመቆጣጠርና መከላከያቸውን ለማግኘት ወጥ የሆነ ተግባር እንዲከናወን በቋሚነት የሚሠራ ነው ተብሏል። በዓይነቱ የመጀመሪያ ነው የተባለው ይህ ጥምረት እስከዛሬ ያልነበረን ትልቅ ለውጥ በሕክምናው ዘርፍ ለማምጣት በር ይከፍታል ተብሎለታል። በጥምረቱ የተፈጠረው ቅንጅት በፉክክር ይሠራ የነበረውን በማስቀረት አንዱ ያገኘውን መደበቅ ሳይኖርበት በጋራ ለሠው ልጆች ጤና የሚሠራበት ነው ተብሏል።

ሐሳቡ የመነጨው ከዓመት በፊት የኮሮና ወረርሽኝ ዓለምን ባስጨነቀበት ጊዜ ቢሆንም፣ በውጥን ደረጃ የነበረውን ዕቅድ ተግባራዊ በማድረግ ሠሞኑን እንቅስቃሴው በይፋ መጀመሩ ተነግሯል። በጥምረቱ የቀረበው ሐሳብ፣ “ነጭ ወረቀት” በተባለ ሠነድ መሠረት የመድኃኒት አምራቾች፣ ተመራማሪዎች የሕክምና አገልግሎት ሰጪዎችና ባለሙያዎች፣ እንዲሁም ከዘርፉ ጋር ግንኙነት ያላቸው አካላት ጥምረት በመፍጠር በሕክምና ዘርፉ ወረርሽኝን የመሳሰሉ አሳሳቢ ክስተቶችን መቋቋም እንዲችሉና ብቁ ለመሆን እንዲሠሩ ጥያቄ ቀርቦበታል።

በሕክምናው ዘርፍ ሥር-ነቀል ለውጥ ለማምጣት የሚያስችልን መሻሻል ለመጀመር እንዲሠራ መንገድ ያመላክታል የተባለው ይህ አዲስ ጅማሬ፣ የሰው ልጆች ላይ አደጋ የሚያስከትሉ ጅምላ ገዳይ ሊሆኑ የሚችሉ በሽታዎች ላይ ትኩረት ይደረጋል ተብሏል። ፔንሲሊንን የመሳሰሉ መድኃኒቶችን የሚቋቋሙ ዝርያዎች ላይ፣ እንዲሁም ማንኛቸውም በወረርሽኝ መልክ ሊከሠቱና ለመቆጣጠር አዳጋች ሊሆኑ የሚችሉ በሽታ አምጪዎች ላይ ርብርብ እንዲደረግ ኹኔታዎችን ያመቻቻል ሲሉም አሳውቀዋል።

የበሽታዎችን ተለዋዋጭነትን ከግንዛቤ ያስገባ አዳዲስ ዘዴን ዘርፉ መጠቀም ካልቻለ በሕክምናው ሒደትና ውጤታማነት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ስለሚችል አሁን የተጀመረው ጥምረት ትልቅ ዕምርታ ሊታይበት እንደሚችል ተጠቁሟል። እንደበሽታ አምጪ ተዋኅስያኑ ተለዋዋጭነት ፈጣን የሆነ የማወቅ፣ የመከላከልና የመቆጣጠር ሒደት ተግባራዊ እንዲሆን የዘርፉ ምሁራንን አቀራርቦ አቅም ካላቸው ኩባንያዎችም ጋር በማስተሳሰር ዘላቂ መፍትሔ እንዲኖር በቋሚነት እንዲሠራ ጥምረቱ ያመቻቸል ሲሉ መስራቾቹ ተናግረዋል።

ከኮሮና ወረርሽኝ መማር አለብን የሚሉት ተመራማሪዎቹ፣ ባለፉት ኹለት ዓመታት የታየውን ዓይነት ቀውስ ዓለም ላይ ዳግም እንዳታይ የዘርፉ ባለሙያዎችም ሆኑ አንቀሳቃሾች ከፖሊሲ አውጪዎች ጋር አብረው መሥራት እንዳለባቸው አስረድተዋል። ለየብቻ ሲኬድበት የነበረው መንገድ ውጤታማ አለማድረጉ በተግባር ታይቷል የሚሉት መሥራቾቹ፣ ከእንግዲህ መዘናጋት እንዳይኖርና ረጅም ጊዜም እንዳይወስድ የተናጥሉን አካሄድ ማስቀረት መቻል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

አንድ ተመራማሪ የሠው ልጆችን እያጠቃ ያለን ተዋኅስያን በቶሎ እንዲያውቅ ከሕክምና ባለሙያዎች ጋር ተገናኝቶ መረጃ እንዲያገኝ ማድረግ ካልተቻለ፣ በጊዜ መድኃኒትንም ሆነ መከላከያውን ማግኘት እንደማይችል ዕሙን ነው። ተመራማሪው ያገኘውን ውጤት ተግባራዊ የሚያደርግበት መንግድ በራሱ ለማመቻቸት ስለማያስችለው አጭር ጊዜንና ወጪን የሚጠይቅ ፈቃድ ሒደት እንዲኖር ለማስቻልም ከሚመለከታቸው ጋር አብሮ መሥራትን ይጠይቃል። ከዚህም በኋላ በምርምር የተገኘውም የሕክምና ዘዴም ይሁን መድኃኒት የሚያመርት ፋብሪካ መኖር ይጠበቅበታል። ምርቱን አውቆ የሚያዝ የሕክምና ባለሙያ፣ የሚሸጥ መድኃኒት ቤት፣ እንዲሁም በአነስተኛ ወጪ ሕብረተሰቡ እንዲገለገልበት የሚያስችሉ ባለሀብቶችን ማቀናጀት ካልተቻለ የልፋታቸውን ያህል ውጤታማ መሆን ባለመቻሉ ጥምረቱ መመሥረቱ ተነግሯል።


ቅጽ 4 ቁጥር 172 የካቲት 12 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here