የካቲት 12 በኢትዮጵያ ታሪክ ሲታወስ

0
2158

መላ አፍሪካውያን በቅኝ ገዥዎች እጅ በወደቁበት ዘመን ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ሥር ላለመውደቅ ብርቱ ተጋድሎ ያደረገችና ነጻነቷንም አስጠብቃ የዘለቀች ብቸኛ አፍሪካዊት አገር ናት።

በ1888 ከጣሊያን ጋር የተደረገው ጦርነት በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት ከተጠናቀቀ በኋላ፣ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ተመልሶ ቢመጣ ከመጀመሪያው በበለጠ ጀግንነት አሳፍሮ እንደሚመልሰው በሙሉ ልብ ያምን እንደነበር ታሪክ አዋቂዎች ይመሰክራሉ።
ኾኖም ግን፣ የወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የአውሮፓውያንን ዝግጅትና በቂ የጦር መሣሪያ ባለቤት መሆን ያውቁ ስለነበር፣ ከሕዝቡ በተሻለ ቅኝ ገዥዎቹ ድጋሚ ሊመጡ እንደሚችሉና ከመጡም የባሰ ጥፋት እንደሚደርሱ ያስቡ ነበር ይባልላቸዋል።

ለዚህም ነው “ታላቁ ጥቁር” በተሠኘው የንጉሴ አየለ መጽሐፍ ላይ ዳግማዊ ምኒልክ “በማንኛውም ቅጽበት ከአሁን ቀደሙ የበለጠና የከፋ ማጥቃት ሊገጥመኝ ይችላል” ብለው ያስቡ እንደነበር የተገለጸው።
ንጉሠ ነገሥቱ ዳግም ወረራውን ባያዩም፣ ያሠጋቸው የነበረው የዳግም ወረራ ጉዳይ ከ40 ዓመት በኋላ መፈጸሙና ሠፊ ጉዳት ማድረሱ አልቀረም። ጣሊያን ቂም የቋጠረችው በአድዋ ከደረሰባት ሽንፈት ማግስት እንደነበር ይነገራል።

የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም “ሕይወቴና የኢትዮጵያ ዕርምጃ” በሚለው መጽሐፋቸው፣ የጣሊያን መንግሥት ከ14 ዓመት በላይ ሲዘጋጅ መኖሩን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ በ1915 የዓለም መንግሥታት ማኅበር አባል መሆኗና ከጣሊያን ጋርም በ1920 የሠላም ሥምምነት መዋዋሏ የእውነት መስሏቸው እንደነበር ጽፈዋል።

ኾኖም ግን፣ በኅዳር ወር 1927 ጣሊያን በድንገት የወልወልን ግጭት ማስነሳቷ የፈረመችው የሠላም ውል የውሸት እንደነበር እና ለበቀል ስትዘጋጅ የኖረች መሆኑን የሚያመላክትና ጠብ እንዲነሳ መሻቷንም አመላካች እንደነበር ገልጸዋል።
ጣልያን፣ ኢትዮጵያ የዓለም መንግሥታት አባል በመሆኗ በጥንቃቄ የክስ አጀንዳ እያጤነቸና ለ20 ዓመት የሚዘልቀውን የሠላም ሥምምነት ወደ ጎን በመተው ኢትዮጵያን ለመውረርና ቅኝ ለመግዛት በሥውር ትዘጋጅ እንደነበርም ይነገራል።

ሌላኛው የታሪክ ጸሐፊ ሐሪ አትክንስ “የኢትዮጵያ ታሪክ” በሚለው መጽሐፋቸው እንደመዘገቡትም፣ ሞሶሎኒ ኢትዮጵያ በኤርትራና በሶማሊ ጠረፎች በኩል ጦር በመክፈት ውሉን አፍርሳለች የሚል ክስ ካቀረበ በኋላ፣ በ1927 የኢትዮጵያን ግዛት 50 ኪሎ ሜትር ጥሶ በመግባት የወልወልን ጦርነት አስነስቷል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ጣልያን በሶማሊና በኤርትራ በኩል ብዙ ቁጥር ያለው ወታደርና የጦር መሣሪያ በገፍ ትልክ እንደነበርም ነው ጸሐፊው የሚገልፁት።

በዚህም፣ በሰሜን በኩል በማርሻል ባዶግሊዮ የሚመራው ጦር ቦምብና መርዝ ጭስ በመጠቀም ኢትዮጵያውያንን ቀስ በቀስ ወደ ኋላ በመግፋት ጎንደርን፣ ማይጨውን፣ ደሴንና ሌሎችን ለመያዝ መብቃቱን አስቀምጠዋል። በደቡብ ኢትዮጵያም እንዲሁ ሶማሊን አቋርጦ የመጣው የፋሽስቱ ጦር ብዙ ቦታዎችን መቆጣጠር ችሎ እንደነበር ነው የሚታወሰው።

በኋላም፣ በ1928 ማርሻል ባዶግሊዮና ጣሊያኖች አዲስ አበባ ሲገቡ ንጉሡን ለመማረክ ጽኑ ፍላጎት እንደነበራቸው ነገር ግን፣ ግርማዊነታቸው አዲስ አበባ ከመያዟ በፊት ወደ ጅቡቲ መሔዳቸው ተቀምጧል።
“የ20ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ” መጽሐፍ ጸሐፊ ጥላሁን ብርሃነሥላሴ በመጽሐፋቸው እንዳሠፈሩትም፣ ሚያዚያ 27 ቀን 1928 ባዶግሊዮ በነጭ ፈረስ ተቀምጦ ጦሩን እየመራ አዲስ አበባ በገባ ዕለት በጣሊያን በኩል የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሥልጣን በኢትዮጵያ ላይ ተቋረጠ።

ንጉሠ ነገሥቱም በተቻኮለ መልኩ ሚያዚያ 23 ሌሊቱን በባቡር ሲጓዙ አድረው ሚያዚያ 25 ጅቡቲ ከገቡ በኋላ ወደ እስራኤል፣ ከዚያም ወደ እንግሊዝ ማቅናታቸው ተመዝግቧል። ግንቦት 26 እንግሊዝ አገር ቢደርሱም፣ በእንግሊዝ መንግሥት በኩል አቀባበል አልተደረገላቸውም። እንግሊዝ የደረሱት ንጉሠ ነገሥቱ ባዝ በሚባል ከተማ ፌርፊልድ መንገድ ዳር ቤት ገዝተው መኖር መጀመራቸውን ጸሐፊው ያነሳሉ።

ይህ የንጉሠ ነገሥቱ ወደ አውሮፓ መሔድ፣ በደጋፊዎቻቸው ዘንድ ለዓለም መንግሥታት አቤቱታ ለማቅረብ የተከናወነ ጉዞ ተደርጎ ቢወሰድም፣ በተቃዋሚዎቻቸው ዘንድ ደግሞ እንደሽሽት መቆጠሩ ነው የሚገለጸው። ኹነቱ ብዙ ባላባቶችና የጦር አበጋዞች ለጠላት እጅ እየሠጡ ወደ መደበኛ ኑሯቸው እንዲመለሱ በር ከፍቷል ይላሉ።

በዚህም፣ የንጉሡን ከአገር መውጣት እና የጣሊያን የተደራጀ አወቃቀርን ተከትሎ የአርበኝነት ትግሉ የተዳከመና ጣሊያንም አገሪቱን መሉ ለሙሉ በመቆጣጠር የራሷን መንግሥት መሥርታ ትኖራለች የሚል ሥጋት በብዙው ሕዝብ ዘንድ አድሮ የነበረ ቢሆንም፣ ከዚህ በተቃራኒ የአርበኞች እንቅስቃሴ እያየለ መሔዱን ታሪክ የመዘገበው ጉዳይ ነው።

በዚህም፣ ኢትዮጵያውያን በዱር በገደሉ እየተቧደኑ በኢትዮጵያ የሞሶሎኒን ወኪል ሠላም ያሳጡትና እንደልቡ እንዳይንቀሳቀስም እንቅፋት ይሆኑበት ነበር። የአርበኝነት ትግሉም በከተማ እና በገጠር እያቆጠቆጠ መሔዱ አልቀረም።

የካቲት 12/1929 ሲታወስ
በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ የታሪክ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ብርሃኑ ለሜሶ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ግራዚያኒ በሶማሊያ በኩል ኢትዮጵያ ወረራ ልትፈጽም ትችላለችና ጠብቅ ተባለ እንጂ፣ ወረራ እንዲፈጽም አልተፈቀደለትም ነበር። ሆኖም ሞሶሎኒን ጨቅጭቆ በሦስት አቅጣጫ ወረራ በመፈጸም አዲስ አበባ ድረስ ዘልቆ እንደገባ አንስተዋል።

የጣሊያን ንግሥት መውለዷን አስመልክቶ የካቲት 12/1929 አዲስ አበባ በቀድሞው ገነተ ልዑል ቤተ- መንግሥት የማርትሬዛ ገንዘብ እንደሚሠጥ በመግለጽ ኢትዮጵያውያን እንዲሰበሰቡ ተደርጎ ነበር ይላሉ የታሪክ መምህሩ።
ይህን አጋጣሚ በመጠቀምም ከአርበኞች መካከል አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስግዶም፣ ከተባባሪያቸው የታክሲ ሹፌር ከሆነው ስምዖን አደፍርስ ጋር ወደ ውስጥ በመግባት ፈንጅ በመጣል ጥቂቶችን ገድለው ግራዚያኒን እንዳቆሰሉት ነው ያብራሩት።
የአርበኞች ድርጊት ጣሊያኖችን እንደአውሬ ስላደረጋቸው፣ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በርካታ ኢትዮጵያውያንን ጨፍጭፈዋል። ወደ ፍቼ በማቅናትም በደብረ ሊባኖስ የነበሩ መነኮሳትንም በገፍ ጨፍጭፈዋል።

በወቅቱ በአዲስ አበባ በውል ያልታወቀ ሕዝብ ከጨረሱ በኋላም፣ ብዙዎችን ወደ ሶማሊያ ወስደው በእርሻ ቦታ ውስጥ አሥረዋቸዋል። ወደ ጣሊያን በማጋዝ በሲሲሊ ደሴት ያሠሯቸው ኢትዮጵያውያንም ነበሩ በማለት የታሪክ መምህሩ ይናገራሉ።
ኮሎኔል አብዲሳ አጋም ወደ ጣሊያን ከተወሰዱት ሰዎች አንዱ ሲሆኑ፣ ከአንድ ዩጎዝላቪያዊ ጋር በመሆን ከዕሥር አምልጦ ጀብድ በመሥራት የአገሩን ሠንደቅ ዓላማ ከፍ ያደረገ እንደነበረም ነው በታሪክ የሚነገረው።

በሶማሊያና በሌሎች ዕሥር ቤቶች ያሉ በርካታ ዕሥረኞችም በሚደርስባቸው ድብደባ፣ ረሀብና በበሽታ በየቀኑ ይሞቱ እንደነበር ታሪክ ይመሰክራል። በርካታ ኢትዮጵያውያንም ወደ ተለያዩ ቦታዎች መወሰዳቸውን ተከትሎ ሶማሊያዊ እና ኤርትራዊ ሆነው የቀሩ እንዳሉም ነው የሚነገረው።

ጳውሎስ ኞኞ “የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት” በሚለው መጽሐፋቸውም፣ የኔፕልስ ልዕልት በመውለዷ ግራዚያኒ የደስታ መግለጫ ገንዘብ እሠጣለሁ ብሎ ከዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከድሮው ቤተ-መንግሥት ድሆች እንዲሰበሰቡ ማዘዙን ጽፈዋል። እኩለ ቀን ገደማም 3 ሺሕ የሚሆኑ ድሆች መግባታቸውን እና ጓደኛማቾቹ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስግዶም በዓሉ ከሚደረግበት ቦታ ቀደም ብለው ደርሰው የያዙትን ቦንብ ማርሻል ግራዚያኒ ለተሰበሰበው ሕዝብ ንግግር ሲያደርግ እንደወረወሩበት ያወሳሉ።
ለሦስተኛ ጊዜ የተጣለው ቦንብ የኢጣሊያ መኳንቶች ባሉበት ቦታ ከፈነዳ በኋላም፣ ባለጥቁር ሸሚዞቹ የኢጣሊያ ወታደሮችና የቅኝ ግዛት ወታደሮች በአዲስ አበባ ከተማ እየዞሩ ሕዝቡን እንደፈጁት ጽፈዋል።
የካቲት 12 የጀመረው እልቂትም ለሦስት ቀን ቀጥሎ 30 ሺሕ ገደማ ኢትዮጵያውያን በገፍ እንዳለቁ እና ሌሎችም እየታፈሱ ወደ ማጎሪያ ቤቶች እንደተወሰዱ ነው የገለጹት።

የኤርትራ ክፍለ አገር ተወላጅ ደጃዝማች ሪሳሪዮ ጊላ የተባሉም በገነተ-ልዑል በነበሩበት ወቅት ስለተመለከቱት ኹኔታ የምስክር ቃላቸውን እንደሚከተለው ሠጥተዋል፤ “ከፋሽስት ዋና ጸሐፊ ከጉይዶ ኮርቴሲ ጋር ተገኛኘን። ዙሪያውንም ብዙ የፋሽስት ሹማምት አሉ። ኮርቴሲም ለነኛ የፋሽስት መኮንኖች፣ ወንድሞች ሆይ ዛሬ ድል የማድረጋችንን እና የበላይነታችንን የማሳወቂያ ቀናችን ነው። በዚህ ሦስት ቀን ውስጥ ኢትዮጵያውያንን ኹሉ አጥፉ። ለዚህ ለሦስት ቀን የሚሆን የነጭ ሽብር (ካርታ ቢያንካ) ፈቃድ እሰጣችዋለሁ። ይህም ፈቃድ ለማጥፋት፣ ለመግደል፣ በኢትዮጵያውያኖች ላይ የፈለጋችሁትን ለማድረግ የሚያስችላችሁ ነው አላቸው።”

አንጄሎ ዴል የተባለ ጸሐፊ የካቲት 12/1929 ስለተፈጸመው ክስተት ሲጽፍም “በአዲስ አበባ የሚኖር አንድ ጣሊያናዊ ወዳጄ ስሜን አትጥቀስ ብሎ እንዲህ ሲል አጫዎተኝ። አየህ የዚያን ዕለት ጣሊያኖች ብዙ ሥራ ሠርተዋል። ወደማታ ገደማ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ስንገናኝ ቦንብ ስጥል የዋልኩበት እጄ ዝሏል አለኝ። አንዱ ኢጣሊያዊ ሲያጫውተኝ በአንዲት ትንሽ ጣሳ በያስኳት ቤንዚን አስር ቤቶች አቃጠልኩባት አለኝ” ሲል ከትቧል።

በወቅቱ በአዲስ አበባ ይኖር የነበረ ላድስላስ ሳቫ የተባለ የሐንጋሪ ተወላጅ ሐኪም ያየውን ሲገልጽም፣ “ደም እንደ ውኃ ሲፈስ በየመንገዱ ላይ ያዩሁት የዚያን ጊዜ ነው። የወንዶች፣ የሴቶች፣ የልጆች ሬሳ በያለበት ተኝቷል። ወዲያውም ከባድ የቃጠሎ ጭስ ተነስቶ ከተማዋን አጨለማት። የሕዝቡ ቤት ከተፈተሸ በኋላ ሰዎቹ በውስጡ እንዳሉ ቤቱ በእሳት ይቃጠላል። ቃጠሎው ቶሎ እንዲያያዝም ቤንዚንና ዘይት ይጠቀሙ ነበር። ሰው እሳቱን እየሸሸ ከቤቱ ሲወጣ በመትረየስ ይገድሉታል። ሌሊቱንም ሲገድሉና ሲያቃጥሉ አደሩ። የማልረሳው ነገር በዚያ ሌሊት የኢጣሊያ መኮንኖች በሚያምር አውቶሞቢላቸው ከሚስቶቻቸው ጋር ሆነው፣ ብዙ ሬሳ ከተከመረበትና ብዙ ቃጠሎ ከሚታይበት ቦታ በሰው ደም ላይ እየቆሙ ያን እልቂት እየተመለከቱ ይስቁ የነበረበት ሁኔታ ነው” ብሎ ጽፏል።

ጸሐፊው ጥላሁን ብርሀነሥላሴ እንዳተተውም፣ ፈንጅ ወርዋሪዎቹን አብርሀ ደቦጭና ሞገስ አስግዶም ፈንጅ የሠጧቸውና ወደ ገነተ ልዑል ግቢ እንዲገቡ የረዷቸውም ደጃዝማች ለጥይበሉ ገብሬ መሆናቸው ነው። ግራዚያኒን ካቆሰሉት በኋላም ወደ ደብረ ሊባኖስ መሔዳቸው ተደርሶበት የግራዚያኒ ወታደሮች ደብረ ሊባኖስ ድረስ በመሔድ በርካታ መነኮሳትን በግፍ ገድለዋል።

የካቲት 12/1950 ለንባብ የበቃው አዲስ ዘመን ጋዜጣም፣ “በዕለቱ በየመንገዱና በየመንደሩ የሞት ዕድል ቅርብ መሆኑንና መንገዱ ኹሉ ሬሳና የሠው ጭንቅላት ብቻ ነበር” የሚል ጽሑፍ አስነብቧል።

ቀጥሎም፣ “በዚህም ላይ በየመንደሩ የገቡት በዝባዦች እያንዳንዱን ቤተሰብ በአንድነት እያሠሩ በቤት ውስጥ ካጎሩ በኋላ በእሳት ሲያቃጥሉት የነበረው ዋይታና ለቅሶ ለውጥ የሚገኝለት አይመስልም ነበር። እንደምንም ብሎ ከመሀል ከተማው እልቂት ያመለጠውም፣ ቀደም ብለው በየተራራው ዙሪያ ሆነው እንደጥንታዊው ጌታቸው እንደ ኔሮን ቄሳር በአዲስ አበባ ከተማ ቃጠሎ ይሳለቁ በነበሩት የፋሽስት ወታደሮች ታደነ። በጠቅላላው ከሞት በቀር ምንም ምርጫ አልነበረም” ይላል።

አብርሀ ደቦጭና ሞገስ አስግዶምም አርበኞችን ተቀላቅለው ከቆዩ በኋላ ወደ ሱዳን ለመሸሽ ሲሞክሩ በሽፍታ መገደላቸውና ስሞኦን አደፍርስ መኪናውን እየነዳ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ በባንዳ ጠቋሚነት ተይዞ በሥቃይ እንደተገደለ የታሪክ መዛግብት ያወሳሉ።
በጥላሁን ብርሀነሥላሴ መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸውም፣ ስሞኦን አደፍርስ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በታሪክ ስሙ ተዘንግቶ የኖረ ሲሆን፣ ይህም የሆነው ካሉት ብዙ ታክሲዎች ውስጥ ብዙዎቹን የነጠቁት ባንዳዎች ከነጻነት በኋላ ባለሥልጣን ስለሆኑ ስሙን ማንሳት አይፈለግም ነበር።

የግራዚያኒ ጦር በአዲስ አበባ ሕዝብ ላይ የፈጸመው ከባድ ድርጊት በዓለም የዜና መገናኛዎች ኹሉ ስለተወሳ ለኢትዮጵያ አቤቱታ ተሠሚነት የራሱን አስተዋጾ አበርክቷል ይባላል። ይህንም ሐሳብ አጠናክረው ያቀረቡት ሎሬንሶ ታዕዛዝ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለፋሽስት ተገዥ እንዳልሆነና ጣሊያንም ሠላም እንደሌላት የዓለም ሕዝብ እንዲገነዘብ አድርገዋል።

የግራዚያኒ ጦር የካቲት 12/1929 በአዲስ አበባ ላይ ጭፍጨፋ ባወጀ ጊዜም፣ 35 ሺሕ የኢጣሊያ ሜትሮፖሊታን ወታደር፣ 40 ሺሕ ባለጥቁር ሸሚዝ የኢጣሊያ ሚሊሻ፣ 5 ሺሕ የኤርትራና 3 ሺሕ የሊቢያ ተወላጅ ወታደሮች እንደነበሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ማጠቃለያ
ጣሊያን ብቻ ሳትሆን እንግሊዝና ፈረንሳይም ቢሆኑ፣ ከአድዋ ጦርነት በኋላ የነጭ መንግሥት በጥቁር መሸነፉ ስላስቆጣቸው ለቅኝ ግዛት ውጥናቸው የተለዬ አጀንዳ የሚፈጥር መሆኑን በማሰብ በኢትዮጵያ ላይ ቂም ይዘው መቆየታቸው በታሪክ ተመዝግቧል። የኋለኛው የእንግሊዝ ዕገዛም የመጣው ጣሊያን እንግሊዝን ለመውረር ከሚያስበው የጀርመኑ አዶልፍ ሒትለር ጋር በማበሯ እንደሆነ እንጂ፣ ለኢትዮጵያ ከመቆርቆር የመጣ እንዳልሆነ የሚነሳ ጉዳይ ነው።
ጣሊያን በኢትዮጵያውያን ላይ ይህን ያህል ግፍ ብትፈጽምም አርበኞች የበለጠ እየተጠናከሩና እየተደራጁ መሔዳቸው ይታመናል።

ጣሊያን በአድዋ ጦርነት ጊዜ ከተጠቀመችው በላቀ ወታደሮቿን በዘመናዊ የጦር ትጥቅ አደራጀታ ወደ ኢትዮጵያ ስትልክ፣ በአንጻሩ የትኛውም ወራሪ ቢመጣ አይቀጡ ቅጣት ቀጥቼ እመልሰዋለሁ ብሎ የሚያምነው ኢትዮጵያዊ አርበኛ ግን በአድዋ ጦርነት ወቅት የተጠቀመውንና የተረፈውን ያረጀ መሣሪያ ይዞ ነበር የወጣው።

በጣሊያን በኩል በተለይም የአውሮፕላን ግኝትን ተከትሎ ተዋጊ አውሮፕላኖችን መጠቀሙ የኢትዮጵያን ጦር ብዙ ዋጋ ያስከፍል ክስተት ነበር።

ይሁን እንጂ፣ ጣሊያን ይህን ያህል ተደራጅቶና ሠልጥኖ፣ ለአርባ አመትም ቂሙን ሲያስብ ኖሮ ቢመጣም ያደረሰው እልቂት መጠነ ሠፊ መሆኑ እንጂ፣ ኢትዮጵያን የመቆጣጠር ሕልሙ ሳይሳካ እንደተመለሰ በብዙ መዛግብት የተመዘገበ ነው። ኾኖም ጣሊያን በኹለተኛው የአምስት ዓመት ወረራ ያደረሰችው ግፍ እጅግ መጠነ ሠፊ እንደሆነ ይገለጻል።

ኢትዮጵያ በጣሊያን ወረራ ምክንያት በተለይም በየካቲት 12 እና በማይጨው ጦርነት የደረሰባትን ጉዳት ጥላሁን ብርሃነሥላሴ እንደመዘገቡትም፣ 275 ሺሕ ሠራዊትና 75 ሺሕ አርበኞች ተገድለዋል። 30 ሺሕ ሰዎች በየካቲት 12 ክስተት ብቻ አልቀዋል። 2 ሺሕ 400 ሠዎች በፍርድ ቤት በሞት ሲቀጡ፣ 25 ሺሕ ሠዎች በማጎሪያ ቤት ሞተዋል። 30 ሺሕ ገደማ ሠዎችም በችግር እንዲያልቁ ሆኗል። በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ መኖሪያ ቤቶች እና በሺሕዎች የሚቆጠሩ አብያተ-ክርስቲያናትም ፈርሰዋል፤ ተቃጥለዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ በርካታ የቤት እንስሳትም አልቀዋል።

የካቲት 12 የሚገባውን ያህል ክብር ተሠጥቶት እየተከበረ እንዳልሆነ የሚገልጹ አሉ። ለአድዋ በዓል በጣም ቅርብ በመሆኑ ተሸፍኗል የሚሉ ቢኖሩም፣ በተለይ በመንግሥት ትኩረት ተነፍጎት እንደቆየ የሚናገሩም ብዙ ናቸው።
ብርሀኑ ለሜሳም (ዶ/ር) በቀዳማዊ ኃይለሥላሴና በደርግ ዘመን የካቲት 12 በደማቅ ኹኔታ ሲከበር እንደኖረ ነው ያነሱት። ከደርግ በኋላ የተተካው ሥርዓት ለምዕራቡ ዓለም ክስተት እንጂ ለአገር ታሪክ ክብር ያልነበረው ነው ያሉት ብርሃኑ፣ ምናልባት ቢቆይ ኖሮ ለሰማዕታት መታሰቢያ ተብሎ የቆመውን ሐውልትም ሊያስነቅለው ይችል ነበር በማለት፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን በገዛ አገራቸው በግፍ የረገፉበት ዕለት ዝቅ ተደርጎ መታየት እንደሌለበት አመላክተዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 172 የካቲት 12 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here