እንብዛ…ጎመኑ ይጠንዛ!

0
696

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ግራ ከሚያጋቡኝና አንዳንዴም በመጠራጠር ከማሰላስላቸው ጉዳዮች አንደኛው ሴቶች እርስ በእርስ አይስማሙም የሚለው ነገር ነው። እውነት ነው አይደለም ብሎ ጥናት የሠራ ሰው መኖሩን እንጃ! ግን ስንት ሰው ይህ ዕይታ ትክክል ነው ብሎ ያምን ይሆን?

ሰው እርስ በእርሱ በብዙ ነገር ይጋጫል። ክፉ ልብና ሐሳብ ያለው ሰው ለማንም ሳይራራ ክፋትን ይሠራል። መልካም ሰው ደግሞ እገሌን ከእገሌ ሳይል ሰውነትን አስቀድሞ መልካሙን ነገር ያደርጋል። ይህ የሰው የግል ምግባሩ ሆኖ ሳለ፣ በጾታ ለምን እንደሚመዘን ግራ ይገባኛል።
ከዛ ደግሞ ይጋጫል። ሴቶች ሰብሰብ ብለው ወሬ ከጀመሩ አይለያዩም ይባላል። እንግዲህ በአንድ በኩል ‹አይስማሙም› ሲሉ፣ ደግሞ በሌላ በኩል ተስማምተው ‹ሲሰበሰቡ ብዙ ያወራሉ›ም ሲባል እንሰማለን። ጉድ ፈላ! ለዛም ነው አሉ ‹ሴት በዛ፣ ጎመን ጠነዛ› የሚለውን ተረት የፈጠሩት።

ልንገራችሁ! እንብዛ። ሰብሰብ እንበል። እህቴ! የምንጋራው ደስታም ሆነ ሐዘን የለምን? ስለትዳር፣ ስለልጆች አስተዳደግ መወያየት የለብንም? ስኬትሽ እንዴት እንደመጣ፣ ምን ያህል እንደለፋሽና ፈተናሽን እንዴት እንዳለፍሽ ለጀማሪዋ ሯጭ ንገሪያት እንጂ! ሲሰበሰቡ ጎመን ያጠነዛሉ ስለተባለ ለምን ዝም ብለሽ ልምድሽን ይዘሽ ትቀመጪያለሽ? ስኬት ሩቅ ነው ብላ ከተስፋዋ ጋር ለምትታገለው አጋሪያት።

ትዳርሽ እንዴት እንደሰመረ፣ ምን መላ ዘይደሽ ጎጆሽን እንዳሞቅሽ ለአዲሷ ሙሽራ ሹክ በያት። አዎን ሕይወት የሚሠራው በቀመር አይደለም፤ ለአንቺ የሠራ ለእርሷ ይሠራል ማለት ላይሆን ይችላል። ግን ጉዞና ጥረትሽ፣ የሕይወት ልምድሽ ጀማሪን ያበረታል። መልካሙን ነገር ለማጽናት የሚያስችለውን ትዕግስትና ብልሃት ታለብሻታለሽ። ይበሉ! አይስማሙምን ትተው ጎመን አጠነዙ ይበሏችሁ!

ትዳርሽ የፈረሰብሽ ሕይወትን እንዴት መግፋት እንዳለብሽ ጨንቆሽ ይሆን? ልክ ባለሽበት ጎዳና ያለፈችውን እህትሽን ለምን አታማክሪያትም? ለምን ሰብሰብ ብለን አናወጋም፣ አንመካከርም? የደረሰብሽ ጥቃት በሕሊናሽ እየተመላለሰ አስጨንቆሻል? አንቺ ብቻ ዓለም ላይ የተጠላሽ መስሎሻል? ጥቃቷን አሸንፋ በፈገግታ መጋረጃ የሸፈነችውን እህትሽን እንዴት በረታሽ በያት።

እህቶቼ! ‹እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ!› እንባባል። እርስ በእርስ አይስማሙምን እናስጥላቸው። የእህትሽን ስህቷትን አትንቀሺ፤ ሙላቷን ተመልከቺ። ድክመቷን አትፈልጊ፣ ብርታቷን አበርቺላት። ዝቅታዋን እንድትበረታባቸው ጠቁሚያት። ደግሞ በቀኝ ጆሮ እንሰማማ፣ ሁሉም ትችት ለክፋት አይደለምና።

ሰብሰብ እንበል! እንማከር፤ እንወያይ። እንብዛ! ጎመኑም ይጠንዛ! የጓሮ አትክልት የሚበረታታበት ጊዜ ላይ ነንኮ! መንግሥትም ለተክሎች ልዩ ትኩረት አለው። ስለዚህ ጎመን ቢጠነዛ ጎመን ይተካል። ከእህትሽ ጋር ጆሮና ሐሳብ መለዋወጡ ከዚህ ጋር ሊነጻጸር እንኳ አይጠጋም።
መቅደስ ቹቹ


ቅጽ 4 ቁጥር 177 መጋቢት 17 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here