በአዲስ አበባ የታክሲዎችን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠር መተግበሪያ ወደ ሥራ ሊገባ ነው

Views: 575

በአዲስ አበባ ከተማ የሚንቀሳቀሱ የከተማ ታክሲዎችን እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር የሚረዳ ‹አዲስ ጉዞ› የተሰኘ አዲስ መተግበርያ በሥራ ላይ ለማዋል በሂደት ላይ እንደሆነ ተገለጸ።

አዲሱ የታክሲዎች መቆጣጠሪያ መተግበሪያ የትራንስፖርት አመራር ስርዓት (TMS) አገልግሎትን የሚያሳልጥ ሲሆን፣ ከ15 ቀን በኋላ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን መተግበሪያውን የሠሩት ተመስገን ገብረሕይወት (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አዲስ ጉዞ የተሰኘው የTMS መተግበሪያ አሁን በታክሲዎች ላይ እየተፈጠረ ያለውን እና ከመንገድ ትረፊክ አደጋ ጋር በተያያዘ ሊገጥም የሚችለውን ችግር በቀላሉ ለመቅረፍ እንዲቻል ጉልህ ሚና ይጫወታል ሲሉ ተመስገን ጨምረው ጠቅሰዋል።

አዲስ ጉዞ የተሰኘው መተግበሪያ የታክሲዎቹን ታርጋ በመመዝገብ ወደ ትራፊክ ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ተጠቃሚዎች መረጃ የሚልኩበት መተግበሪያ ሲሆን፤ መረጃ አላላኩም ታክሲዎች ትርፍ ሲጭኑ፣ ካለ አግባብ (ከታሪፍ በላይ) ተሳፋሪን ሲያስከፍሉና የመሳሰሉትን ለቁጥጥር ከባድ የሆኑትን ጨምሮ መረጃ በመላክ የሚያግዝ መተግበርያ እንደሆነም ተገልጿል።

ይህ አዲሱ መተግበርያ ከዚህ ቀደም ተሞክሮ የማያውቅ እና ወደ ትግበራ ሲገባም እንቅስቃሴውን ለማቅለል ብሎም የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ጠቃሚም ነው በማለት የሚገልጹት ተመስገን፣ ይህን መተግበርያ ማኅበረሰባዊ ግልጋሎት ኃላፊነትን ለመወጣት ታስቦ የተደረገ ነው ብለዋል። ለመተግበሪያውም ኤታ ሶሉሽንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በነጻ ለአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የሰጠው እንደሆነ ታውቋል።

በዓይነቱ አዲስ የሆነውን መተግበርያ ሠርቶ ለማጠናቀቅ የአንድ ዓመት ጊዜ የወሰደ ሲሆን፣ በተያያዘም የመጨረሻ አጠቃላይ ሙከራ ተካሂዶ በተገቢው ሁኔታ ውጤት ታይቶበት መጠናቀቁንም ተመስገን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አዲስ ጉዞ የተሰኘው አዲሱ መተግበርያ ከአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ጋር አንድ ላይ በመሥራት ውጤታማ የሆነ ለውጥ እንዲመጣ እና ሥራውን ቀልጣፋ ለማደረግ እየተሠራ መሆኑንም ተመስገን ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

በተለይ ደግሞ በአሁኑ ሰዓት የተከሰተውን የኮሮና ወረርሽኝ ተከትሎ በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን መሠረት በማድረግ፣ ጠቃሚ መረጃዎችን እና ምልክቱ የታየባቸውን ሰዎች ጥቆማ ለማስተላለፍም ተጨማሪ ማሻሻያ እንደሚደረግበትም ተመስገን አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ መአረ መኮንን (ኢ/ር)፣ አዲስ ጉዞ የተሰኘው መተግበርያ አዲስ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል። የመጨረሻው ሙከራ ተካሂዶበት ውጤታማነቱንም ማረጋገጥ እንደተቻለ ጠቅሰዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ 4 ሺሕ 500 የሚጠጉ ታክሲዎች እንዳሉ የጠቆሙት ምክትል ሥራ አስኪያጁ፣ ትርፍ የተጫኑ ሰዎች በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ላይ መተግበርያው ካለ የመኪናውን ሰሌዳ በመላክ ቅሬታቸውን ማሳወቅ እንዲችሉ በማድረግ ለመቆጣጠር ይረዳል ብለዋል።

ለማኅበራዊ አገልግሎት እርዳታ ለማድረግ በማሰብ ኤታ የተባለ ድርጅት በነጻ ሠርቶ እንደሰጣቸው የተናገሩት መአረ፤ በትክክል ግን መተግበሪያው በሥራ ላይ የሚውልበት ቀን እንዳልተወሰነ አስታውቀዋል።

መተግበሪያው ስማርት ስልክ ያላቸው ብቻ የሚገለገሉበት ሲሆን፣ የሌላቸው ግን እንዲጠቀሙ እድል ላይኖራቸው ይችላል በማለት ተናግረዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ውጤታማነቱ የሚወሰነው የስማርት ስልክ ተጠቃሚ ጋር ያለው መስተጋብር ታይቶ እንደሚሆን ምክትል ሥራ አስኪያጁ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 73 መጋቢት 19 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com