“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።
ሰርግ ጠርተው ለሕጻናት ቦታ የለንም የሚሉ ሰርግ ደጋሾች ዘመን ተሻግሯቸው መረሳታቸውን ተከትሎ፤ ሆቴል ከፍተው ‹ለሴቶች ቦታ የለንም› የሚሉ መገኘታቸውን እየሰማን ነው።
ነገሩን ሰምተን በመገረም አልፈነው ይሆናል እንጂ ለብዙዎች አዲስ አይመስለኝም። ሰሞኑን ታድያ ‹አትገቢም!› ተብላ በአንድ ሆቴል (ቦሌ አምባሳደር ሆቴል እንደሆነ ተጠቅሷል) ጥበቃ ሠራተኞች የተከለከለች ሴት፣ ነገሩን በቴሌግራም በተከፈቱ የተለያዩ ቡድኖች ገጽ ላይ አጋራችው። ጉዳዩ እንደወትሮው ‹ኧረ!?› ተብሎለት በመደነቅ አልታለፈም። ይልቁንም ብዙዎች እንዲቆጡና ‹ምን እናድርግ?› እንዲሉ ቀሰቀሰ።
ነገሩ ወዴት ደረሰና ምን ውጤት አስገኘ የሚለው ይቆየን። ግን አስቡት! አንዲት ሴት ወደ አንድ ሆቴል ስታቀና፣ የሆቴሉ ጥበቃዎች ወዴት እንደምትሄድ ይጠይቋታል። ወደ ውስጥ ልትገባ መሆኑን ስትነግራቸው፤ ‹የለም! ሴት ብቻዋን አትገባም።› ይሏታል። የተባለችውን እሺ ብላ የምትቀበል ሳትሆን ‹ለምን?› ብላ የምትሞግት ሴት ነበረችና፤ ‹ለምን?› ስትል ትጠይቃለች።
‹ዝሙት አዳሪዎች ደንበኞቻችንን እያስቸገሩ ስለሆነ!› ብለው ይመልሱላታል። ብቻዋን ወደ ሆቴሉ የምትገባ ሴት እንደ ዝሙት አዳሪ (በተለመደው አባባል ሴተኛ አዳሪ) ትቆጠራለች እንደማለት ነው። ያለወንድ አጃቢነት ሴት ልጅ ብቻዋን ወደዚያ ሆቴል አትገባም እየተባለች ነው።
ክስተቱ ብዙ ጥያቄን ፈጠረብኝ። ‹ገላዋን ሸጣ የምትኖር ሴት ወደ ሆቴሉ መግባትና አገልግሎት ማግኘት አትችልም ማለት ነው? ወደ ሆቴሉ ብቻዋን የምትገባ ሴት ሁሉ ዝሙት አዳሪ ናት ተብሎ እየታሰበ ነው ማለት ነው? ወንድ የሆቴሉ ደንበኞች እንዳይረበሹ ለማድረግ ይህን ‘ሕግ’ ካወጡ፣ ለሴት ደንበኞቻቸውም ወንዶች ለብቻቸው ወደ ሆቴሉ እንዳይገቡ በማድረግ ይጠብቋቸዋል ማለት ነው? በሆቴሉ የሚስተናገዱ ደንበኞች (ወንዶቹ) ለአቅመ አዳም ያልደረሱ፣ ልዩ ክብካቤና ጥንቃቄ የሚሹ ‘ልጆች’ ናቸው ማለት ነው? እንደው ምክንያታቸው ምንም ሆነ ምን፣ ሌላ የተሻለ መንገድ የለም ማለት ነው? እሺ! ምን ማለት ነው?›
የተረዳሁት ይህን ነው፤ አብዛኛው ነጋዴ ትርፉን እንጂ ደንበኛውን አያከብርም። ዘይትና ዳቦ ነጋዴ ብቻ ይመስለናል እንጂ፣ ትልቅ ሥም ይዘው የሚሠሩና በተሰጣቸው ክብር የተነሳ ሥራቸው እንከን የለሽ ተደርጎ የሚቆጠርላቸው፣ ስህተታቸውም የምክንያት ካባ የሚደረብለት ‘ድርጅቶች’ ለደንበኛቸው ብቻ ሳይሆን ለሰውም አክብሮት የላቸውም። ሁሉንም በራሳቸው የትርፍ መነጽር ብቻ ይቃኛሉ።
እንዲህ ያሉ ነጋዴዎችም ሆኑ ሌሎች ማናቸውም፤ ‘ቀለል’ ወይም ‘ቀላል’ አድርገው የሚወስኗቸው ውሳኔዎች ምን ያህል ዋጋ ሊያስከፍሏቸው እንደሚችሉ ማወቅ አለባቸው። ካልሆነ ግን ሌሎች ሁሉ እንዲማሩ አንዳቸው ማስተማሪያ መሆናቸው አይቀርም።
ቅጽ 4 ቁጥር 182 ሚያዝያ 22 2014


