የውሃ አካላት ዳርቻዎችን ርቀት ለመወሰን ረቂቅ አዋጅ እየተዘጋጀ ነው ተባለ

0
1003

በውሃ አካላትና በየብስ መካከል ያለውን ርቀት ለመወሰን ብሎም በተወሰነው ርቀት መካከል ያለው ድንበር በማስከበር የውሃ አካላትን ደኅንነት ለማስጠበቅ፣ የውሃ አካላትን ዳርቻዎች (በፈር ዞን) ለማልማት እና ለመንከባከብ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ቴዎድሮስ መርጊያ፣ የውሃ አካላት በተለያዩ ምክንያቶች አደጋ ላይ የሚወድቁ በመሆናቸው እና ይህን ተከትሎም በደለል እንደሚሞሉ፣ የውሃ መጠናቸው እንደሚቀንስ፣ አላስፈላጊ አረም እንደሚበቅልባቸው፣ በሂደትም ሊደርቁ እንደሚችሉ አንስተዋል። ይህን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ታሳቢ ያደረገ ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ረቂቅ አዋጁ ከዚህ በፊት ያልነበረ አዲስ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም የውሃ አካላትን ደኅንነት መጠበቅ እና መንከባከብ ወሳኝና አስፈላጊ በመሆኑ የተለያዩ የተፋሰስ ሥራዎች (የአፈርና ውሃ እቀባ) ሲሠሩ መቆየታቸውን ሳይሬክተሩ ጠቁመዋል። አያይዘውም አሁንም በተሻለ ሁኔታ ሥራውን ለመከወን አዋጅ ተዘጋጅቶ ኹሉንም የውሃ አካላት ደኅንነት ለመጠበቅ፣ ለመከታተልና ለማልማት እንደታሰበ ነው የገለጹት።

እንደምሳሌ የአዲስ አበባ ወንዞችን በከፍተኛ ሁኔታ መበከል አንስተው፣ ይህም በወንዞች የግርጌ ተፋሰስ አካባቢ ያሉ ማኅበረሰቦች ወንዞችን ለተለያየ አገልግሎት መጠቀም እንደማይችሉ ጠቁመዋል።
በዝግጅት ላይ ባለው ረቂቅ አዋጅ መሠረትም፣ በውሃ አካላትና በየብስ መካከል ባሉ ዳርቻዎች የተፈቀዱና ያልተፈቀዱ ተግባራት እንዲሁም በማን እና እንዴት እንደሚፈጸሙ በዝርዝር ተደንግጓል ተብሏል።

የውሃ አካላት ደኅንነት ጥበቃ ሥራው የውሃ አካላትን ወንዝ፣ ሐይቅ፣ ግድብ በማለት ወንዞችንም ጅረት አንድ፣ ጅረት ኹለት፣ ጅረት ሦስት ብሎ የመከፋፈል ሥራዎች እንደሚሠሩ ነው ዳይሬክተሩ ያከሉት። ስለሆነም በእነዚህ የውሃ አካላት ላይ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የውሃ አካላትን ደኅንነት እንዳይጎዱ ቁጥጥርና ክትትል ይደረጋል ብለዋል።

ስለዚህም የውሃ አካላትን አጠቃላይ ደኅንነት ለመጠበቅና የውሃ አካላቱ የሚያስገኙትን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ለማጉላት ከፍ ያለ ሚና እንዳለው ተመላክቷል።

የውሃ አካላትን ደኅንነት ከማስጠበቅና ከመቆጣጠር በተጨማሪም፣ ከውሃ አካላት የሚቻለውን ያህል ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማግኘት የልማት ሥራዎች ይሠራሉ ነው የተባለው። በዚህም መናፈሻዎች፣ የኃይል ማመንጫዎች እና ሌሎች የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ለመሥራት በረቂቅ አዋጁ የተካተተ መሆኑ ተጠቅሷል።

ረቂቅ አዋጁ ውይይት እየተደረገበት እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፣ በቅርቡ ወደሚመለከተው የሕግ አካል ቀርቦ ከጸደቀ በኋላ ተግባር ላይ ይውላል ተብሏል። አዋጁን ለማስፈጸምም ዝርዝር ደንብና መመሪያዎች እንደሚዘጋጁ ተመላክቷል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ካሏት የውሃ አካላት ቀላል የማይባሉት የደኅንነት ስጋት እንደተጋረጠባቸው ተመላክቷል። በእንቦጭ አረም የተያዙ ሐይቆችን ጨምሮ በደለል የተሞሉ፣ አረም የበቀለባቸው፣ እንዲሁም መርዛማ እና ባዕድ ነገሮችን በያዙ ከፋብሪካዎችና ከከተሞች በሚለቀቁ ፈሳሾች የተበከሉ የውሃ አካላት መኖራቸው ነው የሚነገረው።

ይህም በአሳ ሃብት ልማት፣ ቱሪዝም፣ መስኖ፣ የውሃ አካላት ብዝኀ ሕይወት፣ አየር ንብረት ለውጥና አካባቢ ጥበቃ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ነገሮች ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ የከፋ እንደሆነ ይታመናል።


ቅጽ 4 ቁጥር 182 ሚያዝያ 22 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here