ከመጠፋፋት አዙሪት እንውጣ!

0
863

ኢትዮጵያውያን ነን የምንል በሙሉ እንደየ እምነታችን የፍርድ ቀን እስኪመጣ ድረስ አብረን ለመቆየት ብንስማማ ይበጀናል። እገሌ ከእገሌ እያልን መለያየቱንና መፈራረጁን በመተው፣ በፈጣሪ ሥራ እየገባን አንዱን ተኮናኝ አንዱን ፃድቅ አድርገን በጅምላ ከመጠፋፋት መቆጠብ እንዳለብን አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

ኹሉን የፈጠረ አምላክ የፈለገውን ማድረግ አቅቶታል የምንል ካልሆንን በቀር፣ እሱ ያላጠፋውን እኛ በሥሙ ለማጥፋት የምንነሳሳ መሆን እንደማይገባን መገንዘብ ይኖርብናል። በሐሳብ ደረጃ ጠላትህን እንደራስህ ውደድ የሚልን አስተሳሰብ እያደር በተግባር ለማዋል ስንቸገር እየታየን ነው።

ፈጣሪ የፈጠረውን ማጥፋት የሚያፀድቅ አለመሆኑን ለማወቅ የመጀመሪያው የሰው ልጅ ገዳይ ቃየን፣ በሌሎች የሟች ልጆች እንዳይገደል የተደረገበት ታሪክ አስተማሪያችን ሊሆን በተገባ ነበር። መግደል የሚያዋጣ ቢሆን ማንም ዘር አሁን ባልነበረ ብለን የምናስብ ትውልዶች መሆን ይጠበቅብናል።

አንድ ፈጣሪ/አምላክ አለ ብሎ የማያምን የዓለም ሕዝብ ከሌላው እምነት ተከታይ በቁጥር በሚበዛባት በዚህች ምድር ላይ ተቀምጠን፣ አማኞች ነን የምንል እርስ በእርስ ካልተጠፋፋን ያልንበት አስከፊው ጊዜ ላይ ደርሰናል። “የሚፈራ ካልሆነ አያስፈራራም” እንደሚባለው አንዱ ወገን የሌላውን እያጥላላ የራሱን ሲያጀግን ማየትም እየተለመደ ይመስላል። ይህን የመሰለ የማያዛልቅ አስተሳሰብ ይዘው እንደጀግና መሪም የሚቆጠሩ እየበዙ መጥተዋል።

በብዛት ተመክቶ ባህር ነን ብሎ ሌላን ደሴት አድርጎ ንቆ ከሚያስፈራራ ጀምሮ፣ ብዛቱን ተመክቶ ለጥቃትም ሆነ ለበቀል የሚወጣ፣ እንዲሁም በተቃውሞ ሰልፍ ድጋፉን የሚያሳይ ሃይማኖተኛ ነኝ የሚልም በዝቷል። ሁሉም ሃይማኖቶች ከትንሽ ተነስተው እንደበዙ የማያስተውል ትውልድ ሆነና ማነሱንም ሆነ መብዛቱን ማስፈራሪያ አልያም ለቅስቀሳ መሣሪያ ሲያደርገው እየተስተዋለ ነው።

ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ግጭት ሲከሰት አሁን የመጀመሪያ አይደለም። ከጥንት ጀምሮ አንዱ አንዱን ሊያጠፋው ሲሞክር እንደነበር በታሪክ ተመዝግቧል። ይህ ቢሆንም ግን ከሌላው ወጥ ከሆነው የዓለማችን አካባቢ በተለየ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አንዱ አንዱን ሳያሳድድ አሁን ድረስ በዝቶ እንዲኖር ያስቻለ አንፃራዊ ፍትህ እንደነበረ ከመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ተሰደው የመጡ የሦስቱም ሃይማኖት (የአይሁድ፣ የክርስትናና፣ የእስልምና) ተከታዮች ታሪክ ያመላክታል።

በቀደመው ዘመን አንድ ነብይ ነኝ የሚል አልያም ከፈጣሪ ዘንድ ተልኬያለሁ የሚል መልዕክተኛ እንደሆነ የሚናገር ሰው እንደ አሁኑ ማስረጃ አምጣ አይባልም ነበር። ንገር ተብያለሁ ያለውን መልዕክት እንዲያስተላልፍ እድል ይሰጠዋል። ሲያስተምር ግን የንግግሩ ፍሬ ሐሳብ በጭብጥ መልክ ተይዞ ጉዳዩ ይገመገም ነበር።

ይዘቱ ሠውን ከሠው የሚያቀራርብ ከሆነ እንዲቀጥል ይፈቀድለታል ብቻ ሳይሆን ነገሮችም ሊመቻቹለት ይችላሉ። በተቃራኒው ሕዝብን የሚከፋፍል፣ ወገን አስለይቶ እርስ በርስ እንዲጠፋፉ የሚያደርግ እኩይ መልዕክት የሚያስተላልፍ ሆኖ ከተገኘ ግን ቅጣቱ ከባድ ነው። ሁላችንንም የፈጠረ አምላክ መዓት አምጥቶ በቁጣው መቅሰፍት እንደግብፃውያኑ ለይቶ ወይም እንደሰዶምና ጎሞራ በጅምላ ማጥፋት እየቻለ፣ ለምን ፍጡር በሰላም እንዳይኖር የሚለያይ መልዕክት አስተላለፍክ ተብሎ ተግባሩን የፈፀመ ያሳሳታቸውን ሰዎች በሞቱ መልሶ እንዲያስተምር ዘግናኝ የተባለ ፍርድ ይፈፀምበት ነበር።

ግለሰቡ ማንም ይሁን የምንም እምነት ተከታይ ይሁን፣ ተሰቅሎ በእሳት ተቃጥሎ እንዲሞት የሚደረገው፣ እንዲህ ዓይነት ሕዝብን ከፋፍለው የሚያጋድሉ ሰዎች የሚረጩት መርዝ ማርከሻው ቀላል ስለማይሆንና ከበሽታው ቶሎ ስለማይዳን እንደሆነ በታሪክ ድርሳናት ተፅፎ ይገኛል።
የአንድ ምድራዊ ወላጅ ምሳሌን እንኳን ብናይ፣ አባት ልጆቹ ቢጣሉና ለመገዳደል ቢሞክሩ አንዱን ወገን ደግፎ እንዲተላለቁበት እንደማይፈልግ አእምሯችን ሊገነዘብ ይገባል። ልጅ ያለው፣ የሚጠፋፉበትን ምክንያት ያስወግዳል አልያም እስከ እለተ ሞታቸው ቢያንስ ተቻችለው እንዲቆዩና እንዲዋለዱ በመፈለግ በጎን ለሁሉም መመኘቱ አይቀሬ ነው። ቢያንስ በልጆቹ ትውልድ እንደፈለጋቸው ባይሆኑለት በልጅ ልጆቻቸው ዘመን ተዋደው አንድ ሆነው እየተረዳዱ ሊኖሩ እንደሚችሉ ተስፋ ያደርጋል።

መጪውን የሚያውቅ ኹሉን የፈጠረ አምላክ አለን ብለን የምናምን በተለያየ ሃይማኖት ታጥረን ያለን ማኅበረሰቦች እንደመሆናችን፣ አንደኛችን በሌላኛችን ጫማ ውስጥ ሆነን ነገሮችን መረዳት እንዳለብን አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።

አንድ ሰው ምንም አቅም አንሶት ሌላው ጉልበተኛ ሆኖበት ደብድቦም ሆነ አስገድዶ አንድ ጉዳይን እንዲያምንለት ቢደረግ እንኳን፣ ቢያንስ አስገዳጁ ሁኔታ እስኪቀርለት የውስጡን በውስጡ ይዞ እሺ ሊል ይችላል እንጂ በዘላቂነት ተሸንፌአለው ብሎ እምነቱን ይቅርና ሥሙንም እንደማይቀይር ሁላችንም እንረዳለን። በደካማነታችን ጊዜ የሆነብንን ለመበቀል የምንጥር ሰዎች ሆነን ሳለ፣ ሌላን ወገን ጉልበትንም ሆነ ብዛትን ተመክተን ለማስፈራራትም ወይም ጫና ለማሳደር ስንጥር እንታያለን። ራሳችን የማንቀበለውን ሌላው እንዲቀበለውና ዝም ብሎ ለዘለዓለሙ አንገቱን ደፍቶ እንዲኖር እንጠብቃለን። ይህ አጉል ግብዝነት መሆኑን በቶሎ ልናውቅ ይገባናል።

“ባህር ነንና አትነካኩን፣ ሲነኩን ሁላችንንም እንደነኩን ይወቁ” የሚሉ ጥፋትን መሠረት አድርገው ለጅምላ እልቂት የሚጋብዙ መፈክሮችን ከየትኛውም ወገን መስማት እየተለመደ ነው። አንዳንዱ አንድ ሃይማኖት ለአንድ ዘር ብቻ የተሰጠ አስመስሎ ሃይማኖቱ እንደተነካና የዘር ማጥፋት እንደሆነ በአደባባይ ሲሰብክ ሌላውም ሲያጋራው ይታያል። ይህ ፈር የለቀቀ አስተሳሰብ ወገን ለማብዛትና ደጋፊ ለማፍራት ተብሎ የሚደረግ የመቀስቀሻ ስልት ቢሆንም ማንም ሞትን ቁጭ ብሎ የሚጠብቅ እንደሌለ ካለማወቅ የተነሳ የሚነገር ነው።

ሶሪያውያኑም ሆኑ የመናውያን ሃይማኖታዊ ልዩነትን ይዘው አንዱ የአንዱ የበላይ ሆኖ ለማጥፋት የሞከሩበት ሂደት ሁሉንም እያጠፋ መሆኑን ተመልክተን ልንማርበት በተገባን ነበር። ምንም ሃይማኖታዊ ልዩነት ከሌለባት ከጎረቤት ሱማሊያ እንኳን መማር ተስኖን በዚህ ዘመናዊ በሚባል የቴክኖሎጂ ወቅት የተጀመረ መተላለቅ እንደማያባራ እያወቅን፣ ከማን አንሼ በሚል ሰንካላ አስተሳሰብ በየፊናችን የሚያሳልቀንን አጀንዳ እየቆሰቆስን እንደሆነ መረዳት ይገባናል።

ሠሞኑን በጎንደር በተፈጠረው ክስተት እንደሰው ልጅ ማዘን ሲገባ በሃይማኖት ጎራና በዘር ልዩነት ተመዳድበው ነገሩን ሲያጦዙና ሲያስተባብሉ የሚታዩም ነበሩ። ይህ አይነት ማንነትንም ሆነ ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ግጭትም ሆነ ጥቃት በቅርብ ዓመታት ተደጋግሞ ቢፈፀምም፣ የአሁኑን አጋግሎ መቀስቀሻ ማድረግ ያስፈለገበትን ምክንያት ልቦናችንን ክፍት አድርገን ልንረዳው ግድ ይለናል።

በጎንደር ሃይማኖት ተለይቶ የተደረገው የእርስ በርስ መጠፋፋትም ሆነ የንብረት ውድመት የሚጠቅመው ነዋሪውን ሳይሆን የጋራ ጠላታቸውን መሆኑ እሙን ነው። የአንድ ሃይማኖት ተከታይ አውቆም ይሁን ሳያውቅ ከሌላ ሃይማኖት ተቋም አጥር ላይ ለመቃብር የሚሆን ድንጋይ ለመውሰድ ሞከረ በሚል በጥቂት ሰዎች አለመግባባት ሳቢያ የተነሳው የሠላም መደፍረስ፣ ለሠው ልጅ ክቡር ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል።

በየቀኑ ሊባል በሚቻል መልኩ በታጣቂዎች በርካታ ኢትዮጵያውያን እየተገደሉ ገዳዮችም እየታወቁ መናገር የሚፈራው ኅብረተሰብ፣ ሕዝብ በሕዝብ ላይ እርስ በርሱ ተነሳስቶ ተጨፋጨፈ ለማለትና “አዛኝ ቅቤ አንጓች” እንደሚባለው የራሱን አጀንዳ ለማራገብ ሲሞክር በግልፅ ታይቷል።

አጋጣሚውን ተጠቅመው ከኑግ የተገኘህ እያሉ የቅባት እህሉን ሁሉ ሰሊጥ ብለው እየፈረጁ ለጅምላ ጥፋት ለማመቻቸት ጥላቻን የሚሰብኩም እየተሰሙ ነው። ሃይማኖታዊ ጥቅስንም እያሰሙ ጭፍጨፋውን ከጎረቤትህ ጀምር እያሉ ተሰባጥሮ ለዘመናት የኖረውን ሕዝብ እንደፍላጎታቸው ለመለያየት ሲጮሁም እየተሰማ ነው።

ይህ አይነቱ አካሄድ ለማናችንም የማይጠቅም ከሁሉም የከፋ እልቂት እንደሚያመጣ ማወቅ ይገባል። አንድ ሰው መሞት ካለበት ለእምነቱ መሞትን እንደሚመርጥ በማወቅ የሚያመጣውን አስከፊ መዘዝ መረዳት እንደሚቻል አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።

ጥሩነት የሚለካው ወገኔ ለምንለው ብቻ ወግነን ስንጋደል ሳይሆን የእኛ ለማንለውም ቢሆን ፍትሓዊ ሆነን ስንፈርድ ነው። እነ ማዘር ትሬዛን የመሳሰሉ ዓለም የሚያደንቃቸው በጎ ሠሪዎች፣ ክብርን ያገኙት ለራሳቸው ወገን ለይተው ስለረዱ ሳይሆን፣ ለሌላው አቅም ለሌለው የቅርብ ወገናቸው ላልሆነ ደካማ ጭምር ስለቆሙ መሆኑን መረዳት ይጠበቅብናል።


ቅጽ 4 ቁጥር 182 ሚያዝያ 22 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here