ዓለምን ወደ አንድ መንደር እያቀራረቡ ነው ከሚባልላቸው ጉዳዮች አንዱ እና ዋነኛው ቁልፉ ጉዳይ ነው ቴክኖሎጂው መዘመን። ታዲያ በአንድ አገር ከዘመን ጋር አብሮ የሚዘምነው የአኗኗር ሁኔታ እና ዘዬ እና ደረጃ በዛው ልክ በልክ ለሚጠቀሙት ጠቅሞ ልኩን ላላወቁት ደግሞ ገድሎም ሲያልፍ ማየት የተለመደ ሆኗል። በቴክሎጂ ውጤቶች ሱስ ተይዘው በማገገሚያ ማእከላት ወራትን ሲከርሙ ማየት እንዴት ባለ ስቃይ ውስጥ ሲያልፉ መመለከትም የሚከብድ ጉዳይ ነው። በአደጉት አገራት ይህን አይነት ጉዳዮች ሲታዩ እና ሲሰሙ ውለው በሚያድሩባት አለም ለማኅበራዊ ትስስር ገጾች አጠቃቀም ዙሪያም ጠንከር ያለ መቋጫ እና ቆንጠጥ የሚያደርጉ የሕግ ማዕቀፍም ሲያበጁለት ይስተዋላሉ።
ይህን አይነት ጉዳይ ታዲያ የቴክኖሎጂ ዕድገት ነገ ዛሬ ሳይል በአዳጊ አገራትም ላይ መዳረሱ እና ኑሮን ከማቅለሉ በተጨማሪ በርካታ ትሩፋትን ይዞ መምጣቱ እሙን ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ግን ታዲያ የጎንዮሽ ጉዳቱም የዛኑ ያህል ከባድ ዋጋ እያስከፈለንም ይገኛል። በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን አጠቃቀም በተመለከተ ይህን ያህል የጠራ መመሪያ ካለመኖር ጋር ተያይዞ በስፋት ሲሰራጭ ሚውለው አሉባልታ እና ግጭት ቀስቃሽ ነገሮች በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ከባባድ ችግሮችን ፈጥረው ያድራሉ። ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ፤ ከሰሜን እስከ ደቡብ ድረስ አንዱ አንዱን ሲነቅፍ እና ጥላቻውን ሲነዛ ከአለበት ሆኖ ይውላል። ይህ ታዲያ በሌላኛው አካባቢ ለሚኖረው ሰላማዊው እና ለፍቶ አዳሪው ሕዝብ ትልቅ የራስ ምታት ወደ መሆን ይሸጋገራል ይህንንም በየእለቱ ስንመለከተው እንውላለን።
በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃዎችን በተመለከተ የሕግ ማዕቀፉ ያነሳው ጉዳይ በዋናነት የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ጉዳይ ቢሆንም ነገር ግን ለተግባራዊነቱ ግን አሁንም ዳተኝነት ይታያል። ይህ ጉዳይ ታዲያ በአሁኑ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ላይ በእሳት ላይ ነዳጅ እንደማርከፍከፍ የሚቆጠር ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ መንግሥት ይህን ጉዳይ ችላ ሊለው ቀርቶ ለአፍታ ሳያስብ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ ያስፈልጋል። ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚንስትሩም በአንደበታቸው ሲናገሩ እነደተሰማው በጀርመን አገር ስለ ናዚ የሚያወድስ አንድ ጽሑፍ በፌስ ቡክ ወይም በሌላ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ተጽፎ ከተገነ እና ለግማሽ ሰዓት በአየር ላይ ከቆየ የፌስ ቡክ ኩባንያ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ እንደሚቀጣ የሚደርግ ሕግ እንዳለም ይታወቃል። ይህን ጉዳይ ታዲያ በኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግም የፉስ ቡክ ኩባንያ ኢትዮጵያዊያን ጋር አብሮ መስራት ከጀመረ ዋል አደር በሏል። ይሁን እንጂ አሁንም ድረስ ከባባድ ጉዳዮች በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ሲዘዋወሩ እና ሐሰተኛ እና ግጭት ቀስቃሽ ጉዳዮች ሲነበቡ እና ሲሰሙ ይውላሉ። በመሆኑም ይህ ጉዳይ አሁንም ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ እንደሆነ አዲስ ማለዳ በጽኑ ታምናለች።
በሌላ በኩል ደግሞ በቅርቡ በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የተዘጋጀው እና ለመገናኛ ብዙኃን ተግባራዊ የሚሆነው አዲሱ የሚዲያ ፖሊስ ደግሞ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ጉዳይ ከግምት ውስጥ አለማስገባቱ ደግሞ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት እንዳልሰተው ማሳያ ነው ስትል አዲስ ማለዳ ታምናለች። በመሆኑም መንግሥት ይህን ጉዳይ በአፋጣኝ ክለሳ በማድረግ በሚዲያ ፖሊሲው ውስጥ እንዲካተቱ ማድረግ እንደሚኖርበትም ታሳስባለች። በኢትዮጵያ ውስጥ ከአንዳድ መገናኛ ብዙኃን በላይ ግለሰቦች የማህበራዊ ትስስር ገጾች በስፋት ሰዎች ጋር በሚደርሱበት በዚህ ወቅት በሚዲያ ፖሊሲ ላይ ማኅበራዊ ትስስር ገጾች አለመካተታቸው ከባድ ስህተት ነው ስትል አዲስ ማለዳ ታስባለች።
በአሁኑ ወቅት የፌደራል መንግስቱ በሕወሓት እና አመራሮች ላይ የሕግ ማስከበር እርምጃ መውሰድ በጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እንኳን የሚወጡ እና ወደ ሕዝብ የሚደርሱ መረጃዎች በስህተት ተሞሉ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞም ሕዝብን ውዥንብር ውስጥ የሚከቱ ከመሆናቸውም በላይ ሕዝብ ትክክለኛውን መረጃ ከሚያገኝበት መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚያድርበት አመኔታ ችግርም ሊስተዋል ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ አቋሟን ትገልጻለች። በተደጋጋሚ እና ያልተጣሩ፣ የራሳቸው የሙያ ስነ ምግባር እና ፖሊሲን ባልተከተሉ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሚወጡ ዘገባዎች ከተጠያቂነት ውስጥ የሚገቡ ባለመሆናቸው እና በሚያወጡት ዘገባ የሚደርሰውን ጉዳት ሳይመዝኑ በሚያስራጩት ዘገባ ግዴለሽነታቸው ይታያል። ይህ ደግሞ የሆነው መንግሥት በዚህ ዙሪያ የሚወስደው እርምጃ አናሳ በመሆኑ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች። ስለሆነም እስካሁን ልቅ በነበረው የማኅበራዊ ትስስር ገጽ አጠቃቀም ዙሪያ የጠፋውን የሰው ሕይወት እና ንብረት ከዚህ በኋላ በለዘብተኝነት እንዳይጠፋ ከወዲሁ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች አጠቃቅም ዙሪያ መንግስት እርምጃ ሊጠነክር እንደሚገባ አዲስ ማለዳ አሁንም ትናገራለች። በርካታ ተከታዮች ያሏቸው ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ተካተው ለሚለጥፏቸው ጉዳዮች ኃላፊነታቸውን የሚወስዱበት እና የሚጠየቁበት አግባብ እንዲኖርም ያስፈልጋል ስትል አዲስ ማለዳ ታስረግጣለች። ነገር ግን ይህ ባልሆነበት ሁኔታ በየስፍራው ሚከሰተውን ችግር የጊዜያዊ እሳት የማጥፋት ስራን መስራት ዘላቂ መፍትሔ አይሆንም ስትልም አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።
ምክንያቱም ደግሞ በቴሌቪዥን እና በጋዜጣ መረጃዎችን ከሚያገኘው ወጣት ይልቅ በተንቀሳቃሽ ስልኩ ሚደርሰው መረጃ በእጅጉ ቅርብ ነው እና ለአልተገባ ተግባር እንዲጋለጥ ማድረግ እድላቸው ሰፊ በመሆኑ ይህ ጉዳይ ከወዲሁ ሰፊ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው ስትል አዲስ ማለዳ ሀሳቧን ትደመድማለች።
ቅጽ 2 ቁጥር 108 ኅዳር 19 2013


