በድሬደዋ በከባድ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ላይ የሰዓት ገደብ ተጣለ

0
820

በድሬዳዋ ከተማ የሚፈጠረውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቀነስ በከባድ የጭነት ተሸከርካሪዎች ላይ የሰዓት ገደብ መጣሉን የከተማ አስተዳደሩ የትራንፖርት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀ።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ የህዝብ እና የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት አደረጃጀት ስምሪት ዳይሬክተር ተፈራ ነጋ እንደገለጹት፤ ከባድ ተሸከርካሪዎች ጠዋት ከአንድ ሰዓት እስከ ሦስት ሰዓት እንዲሁም አምስት ሰዓት ከሰላሳ እስከ ስምንት ሰዓት ከሰላሳ የሚፈጠረውን የትራፊክ መጨናቅ ለመቅረፍ እንዳይዘዋወሩ ገደብ መጣሉን አስታውቋል።

ይህ ውሳኔ ማሻሻያ ተደርጎበት ነው እንጂ በመጀመሪያ ሕዳር 14 /2013 ከባድ ተሽከርካሪዎች ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ባለው ጊዜ መንቀሳቀስ እንዳይችሉ የሚል እንደነበር እና ይህም የምጣኔ ኃብት እንቅስቃሴውን ይጎዳዋል በሚል ወዲያው ማሻሻያ ተደርጎበት ሠራተኛ ወደ ሥራ የሚገባበት እና የሚወጣበት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱበት ሰዓት ላይ የትራፊክ መጨናነቅ እና አደጋን ለማስቀረት እገዳው መቀመጡን ጠቁመዋል።

ድሬዳዋ የጭነት መኪኖች በብዛት የሚዘዋወሩባት ከተማ ከመሆን አልፋ ወደ ተርሚናልነት የተቀየረች በሚመስል ደረጃ የትራፊክ መጨናነቆች እንዳሉ የገለጹት ተፈራ ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት ትራንስፖርት ቢሮ እና የከተማዋ አስተዳደር በጋራ በመሆን ይህንን የሰዓት እገዳ ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግ ስለታመነበት እገዳው መቀመጡን ኃላፊው ተናግረዋል።

ይህ እገዳ የማይመለከታቸው ከባድ ተሸከርካሪዎች እንዳሉ ለአብነትም ነዳጅ የያዙ ቦቴዎች፣ በቀላሉ ሊበላሽ የሚችል እንደ ፍራፍሬ እና አትክልት የመሳሰሉ ምርቶችን የጫኑ መኪኖችም ማለፍ እንደሚችሉ ተመላክቷል።በቀጣይም ከባድ የጭነት ተሸከርካሪዎች የሚያቆሙበት ቦታ ለማዘጋጀት እቅድ ተይዞ ሲሊሌ አካባቢ 12 ሄክታር ቦታ ወስደን ለጭነት ተርሚናል እና ለትራፊክ ኮምፕሌክስ ደረጃውን የጠበቀ ማቆሚያ ለመሥራት ከመንግሥት 14 ሚሊየን ብር በጀት ተጠይቆ እስኪለቀቅልን እየጠበቅን ነው ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በድሬደዋ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ ዳይሬክቶሬት የግንዛቤ ማስጨበጥና ማስፋፋት ማስተባበሪያ ኃላፊ ኢንስፔክተር ጌትነት ዳባ እንዳሉት በድሬደዋ ያለው መንገድ እና የተሽከርካሪው ቁጥር እየተመጣጠነ አይደለም ለዚህም ገደቡ መጣሉ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
አሁን ያሉት የመንገድ መሰረተ ልማቶች እና የትራንስፖርት አገልግሎቶች በሚፈለገው ልክ መሸከም የሚችሉ ስላልሆኑ መሰረተ ልማቶቹ እስኪስተካከሉ ድረስ እገዳው መቆየት እንዳለበት ያለውን እምነት ጌትነት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ያቀዳቸው እቅዶች እንዳሉ በተለይም ከባድ ተሸከርካሪዎች ከተማው ውስጥ ሳይገቡ ዳር ዳሩን እንደ ቀለበት መንገድ ተሰርቶ ከባድ መኪኖች በዛ መንገድ ብቻ እንዲጠቀሙ የሚያስችል ሥራዎች እንደታቀዱና ይህ ተግባራዊ ሲሆን ደግሞ ለከባድ ተሽከርካሪዎችም ጥሩ እንደሆነና ለከተማዋም ጥሩ እንደሚሆንና መፍትሄ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ድሬደዋ ሦስት ዋና ዋና የሆኑ መግቢያ በሮች እንዳሏት የጠቀሱት ኢንስፔክተሩ የትራፊክ መጨናነቁንም ሆነ የትራፊክ ፍሰቱን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንደሆነ በሌሎች ከተሞች ላይ በብዛት የከባድ ተሽከርካሪ ገደቦች እንዳሉ እና በድሬደዋም ይህ ገደብ መጣሉ ተገቢና የትራፊክ ፍሰቱንም የሚያቃልል ነው ብለዋል።
ይህ እገዳ ተግባራዊ ሲደረግ ለኅብረተሰቡ ደህንነት እና ሰላም ለማረጋገጥ ተብሎ ታስቦ የሚደረግ መሆኑን ተገንዝቦ ሁሉም ተባባሪ በመሆን ከተማችን ድሬደዋን ከትራፊክ አደጋ የፀዳች ለዜጎቿ አስተማማኝ ደህንነት ያላት ከተማ እንድናደርግ ብለዋል።

ገደቡን ተላልፎ የተገኘ በደንብ ማስከበር ሥርዓት አንድ ጊዜ ያጠፋ 1 ሺሕ ብር በድጋሚ ጥፋት ያጠፋ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ አንድ ሺሕ500 ብር ቅጣት ይጣልበታል ያሉት ጌትነት በትራፊክ መቅጫ ቢቀጣ ቅጣቱ አነስተኛ ስለሚሆን ለጥፋት እንዳያበረታታ በሚል እንደሆነ ተናገረዋል።
በድሬደዋ በአጠቃላይ 24 ሺሕ አምስት መቶ አስር ተሸከርካዎች እንዳሉ አዲስ ማለዳ ከፌደራል ትራንስፖርት ሚንስቴር ለማወቅ ችላለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 108 ኅዳር 19 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here