ወንዶች ማጀት ዋሉ!

0
1162

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

“ባሌ ኹልጊዜ ደካማ እንደሆነኩ ይነግረኛል፤የትንሽነት ስሜት እንዲሰማኝ ማድረግ የዕለት ተዕለት ሥራዉ ነዉ፤ ለ 11 ዓመት የምሰማዉ ድምጽ ይህ ስለሆነ ደካማንቴን ተቀብዬ ፣ከሰዉ ኹሉ በማነስ ኑሮዬን በመግፋት ላይ ነኝ” አንዲት እናት አሁን በማላስታዉሰዉ የሬዲዮ ጣቢያ ላይ የተናገሩት ነዉ።
ከኹሉ የሚገርመዉ እኚህ ሚስት ባላቸው በተደጋጋሚ የሚሏቸውን በመስማት መጥፎ ሰብዕና ተጋብቶባቸው ደካማ ነኝ ብለው መቀበላቸውን ያምናሉ። በ 11 ዓመት የትዳር ዘመናቸዉ 3 ልጆች አፍርተዋል። ባልየዉ ገንዘብ ከማምጣት ዉጭ ምንም እንደማይሠሩ ተናግረው ነበር። ቤታቸውንና ልጆችን በመንክባከብ የአንበሳዉን ድርሻ የሚወስዱት እሳቸው ቢሆኑም፣ ሽልማታቸው ስድብ ነዉ።
ከባላቸው የሚጠይቁት አንድ ነገር አለ፣ ለአንድ ቀን ቤት ዉለው እሳቸው የሚሠሩትን ሥራ እንዲከውኑ ነዉ። ለልጆች ወጥ ሥራ፤ እንጀራ ጋግር፤ ምግብ አስረህ ልጆችህን ትምህርት ቤት ላክ፤ ቤት አጽዳ፤ ልብስ እጠብ፤ አልጋ አንጥፍ፤ ጊቢ ጠራረ፤ ቡና አፍላ፤ ከትምህርት ቤት ልጆችህ ሲመጡ የትምህርት ቤታቸዉን ልብስ እጠብ፤ አንድ ነገር ደሞ እንዳትረሳ፣ ሊጥ ማቡካትህን፣ ምክንያቱም እንጀራዉ ከማለቁ በፊት ሊጡ ቦክቶ መዘጋጀት ስላለበት ብለው ማዘዝ ይፈልጋሉ።
ከዚያ በኋላ ሚስትህ ደካማ ሳትሆን፣ ሥራዉ ብቻ ምን ያህል እንደሚያደክማት፣ እንዲሁም ጥንካሬዋን እንጂ ደካማ መሆኗን እንደማያሳይ ትረዳዋለህ ብለዋል።
የኚህ ሴት ታሪክ የስንቶቻችን ታሪክ ይሆን? ቤቱ ይቁጠረዉ።አዚህ ላይ አንድ ነገር ልብ ማለት ያሻል፣ ለአእምሮ ሕመም ከሚዳርጉ ምክንያቶች አንዱ፣ ለራስ ዝቅተኛ አመለካከት መኖር ነዉ። “እኔ ደካማ ነኝ፤ እኔ አልጠቅምም” ማለት ለእብደት የሚዳርግ አደገኛ ሐሳብ መሆኑን። ዶ/ር ዮናስ ላቀዉም ይህንን በ“አማኑኤል ሆስፒታል ታሪኮች” መጽሐፉ ውስጥ አስቀምጦታል።ወንድሞች ሆይ፣ እያወቃችሁም ሆነ ባለማወቅ ሚስቶቻችሁን ለአእምሮ ሕመም እየዳረጋችኋቸዉ ነዉና እባካችሁ ባታደንቋቸዉ እንኳን አትተቿቸዉ።
በነገራችን ላይ በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ፣ በኹሉም የሕይወት መንገድ ሴት ናት ወይስ ወንድ ነው ጫና የሚበዛበት? መልሱን ለሕሊናችሁ ትቼዋለሁ።
ሴት በተፈጥሮ በየወሩ የወር አበባ ስታይ የሆርሞን ለዉጥ ስለሚመጣባት ለጤና መዛባት ትዳረጋለች። ሌላዉ በዓለም በሕመሙ በኹለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠዉን ምጥ በወሊድ ጊዜ ታስተናግዳለች። በወሊድ ጊዜ የሚያጋጥመዉ ሞት፣ ሌላዉ የእናትነት ፈተና ነዉ። ከወለደች በኋላ፣ ጡት የማጥባት እና ልጇን የመንከባከብ ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ የዚችዉ እናት ነዉ። ትንሽ ከወሊድ ጊዜዋ ማግስት ስትጠነክር፣ ቤቷንና ባሏን የመንከባከብ ድርብ ኃላፊነቷ ይቀጥላል። ።
በተያያዘ፣በትዳር አጋር ብቻ ሳይሆን በቤተሰብ ፣በጓደኛ፣በዘመድ፣እና በሥራ ባልደረባ ወይም በአለቃ ዝቅ ተደርጎ መታየትም ይስተዋላል። የሥነ ልቦና ጉዳቱ በቀላሉ የሚነገር አይደለም። አቅምን ያለማወቅና ያለማዉጣት ችግር ያስከትላል። የፈጠራን ክህሎት በእጅጉ ያዳክማል። ሥራን ለመሥራት ተነሳሽነት እንዳይኖር ያደርጋል። ዉጤታማነትን ይቀንሳል። ከሁሉ የሚብሰዉ ግን ለአእምሮ ሕመም መዳረጉ ነዉ። ሰዉን “አትችልም” ማለት፣ ደካማነቱን እንዲያምን ማድረግ ከመግደል የማይተናነስ ወንጀል ነው። ታዲያ የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ ሚስቶቻቸሁን አድንቁ፤ አመስግኑ፤ ዉደዱ።


ቅጽ 3 ቁጥር 156 ጥቅምት 20 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here