የኹለት ዓመቱ የኮቪድ-19 ጉዞ

0
1342

ኮቪድ-19 ከተከሰተ ኹለት ዓመት ሊያስቆጥር ቀናት ቀርተውታል። ወረርሽኙ በምዕራባውያንና በቻይና መካከል ያለውን ልዩነት ተጠቅሞ መስፋፋቱ ይነገርለታል። ቻይና መነሻውን ለመደበቅ፣ አሜሪካ ደግሞ ቻይናን ከሌላው ዓለም ለማስገለል በሚል የጀመሩት እሰጥ አገባ በዓለም ጤና ድርጅት ጣልቃ ገብነት ሊበርድ ቢችልም፣ መሪውን ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖምን ከማስተቸት አላለፈም ነበር። ዓለም አስቀድሞ እንዳይጠነቀቅ አዘናግተዋል በሚል ትችት ቢሰነዘርባቸውም፣ ተቃውሞው ከቁብ ሳይቆጠር ወጀቡ ታልፏል።
ውሐን በተሰኘች የቻይና ከተማ ውስጥ በሚገኝ እንስሳት ገበያ የተገኘው የመጀመሪያው ኮሮና ቫይረስ፣ ከቻይና ወጥቶ ዓለምን ለማዳረስ ጊዜ አልፈጀበትም ነበር። እንቅስቃሴ እንደልብ ስለነበር ከአንዱ አገር ወደሌላው በከፍተኛ ፍጥነት በመዛመቱ የሕክምና ባለሙያዎችን ያሳስብ የነበረው ሒደቱ፣ ፖለቲከኞችንም ማስጨነቅ የጀመረው ወዲያው ነበር።

ወረርሽኝ ይሆናል ብሎ የቻይና መንግሥትን አስጠንቅቆ ፊት ተነስቶና ተቀጥቶ የነበረው ሐኪም፣ ራሱ መሞቱን ተከትሎ ብዙ ድንጋጤን ፈጥሮ ነበር። በሕክምና ባለሙያዎችና በፖለቲከኞች መካከል የነበረውን ልዩነት የበሽታው ሥርጭት እያጠበበው በኋላ ላይ ወጥ የሆነ አቋም ሊያዝ ችሏል።

የበሽታው ስምና የሚተላለፍበት መንገድ ከሞላ ጎደል ታውቆ ሕዝብን ለማሸበር የወሰደበትም ጊዜ አጭር ነበር። ከአንድ ሰው ጀምሮ እንደቀልድ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሲይዝ ሥጋቱና የሚወሰደውም ዕርምጃ በዛው ልክ ፈጥኖ ነበር። ቻይና ንግዷ እንዳይስተጓጎል ስታቅማማ የነበረውን ትታ፣ ከተማን ሳይቀር ሙሉ በሙሉ በመዝጋት ፈጣን ዕርምጃ በመውሰድዋ እስከዛሬ ድረስ በሽታውን ከሌላው በተሻለ ለመቆጣጠር አስችሏታል።

ጎረቤቷ ሰሜን ኮሪያ ወዲያው ኹሉንም ግንኙነቷን አቋርጣ እስከዛሬ በመዝለቋ አሁን ምንም የኮሮና ተጠቂ የሌለባት አገር ለመሆን ችላለች። መግባትና መውጣት ከልክላ ባለሥልጣናቷንም ሆኑ ዲፕሎማቶቿን በያሉበት በማቆየቷ ከማንም አገር የተሻለ ሥርጭቱን ለመግታት አስችሏታል።

በኢኮኖሚዋ ላይ ምንም አይነት ጫና ቢያሳድርባትም ዋናው ጤና ነው ብላ በወሰደችው ዕርምጃ የብዙዎች ምሳሌ ሆናለች። ቻይናም በበኩሏ ከተማን ሳይቀር ኹሉን ነገር ዘጋግታ ከተፈቀደለት ውጭ ማንም እንዳይወጣ በማድረግ ከማንም በፊት ተሰራጭቶ የነበረውን ቫይረስ ቀልብሳ የተሻለ ውጤትን በወራት ውስጥ ማሳየት ችላለች።

በሌላ በኩል፣ የቻይናን ተሞክሮ እንደመብት ረገጣ፣ ወረርሽኙንም እንደውሸትና እነሱን ለማዳከም እንደተካሄደ ሴራ ቆጥረው ሕዝባቸውን ሲያዘናጉ የነበሩ አገራት ነበሩ። በቅድሚያ በእንዲህ አይነት ተግባሯ የሌሎች መጥፎ ምሳሌ ሆና የነበረችው ጣሊያን፣ ሌላውን ለበጎ ማስተማሪያ የሆነችው ወዲያው ነበር። ዓለም እስኪያዝንላቸው ድረስ ዜጎቿ እኛን እያያችሁ ተቀጡ እያሉ ብዙዎችን አስተምረው ነበር።

ገንዘብ ፋይዳ የለውም እየተባለ በየሜዳው ተበትኖ የመጨረሻው ዘመን እስኪመስል ድረስ የተጎዱ አገራትን እየጠቀሱ፣ “በቀን ይህን ያህል ተያዙ፤ ይህን ያህል ሞቱ” የሚለውን ለመስማት ኹሉም የዜና ሰዓትን አሰፍስፎ የሚጠብቅበት ጊዜም ነበረ። መቅበሪያም ሆነ ቀባሪ ጠፋ እየተባለ በቅርብ ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ድንጋጤ በሕዝብ ዘንድ በመከሰቱ፣ ታይቶ በማይታወቅ መልክ ሕዝብ ወደ ዕምነት ተቋማት የተመመበትም ጊዜ ነበር።

አንዳንድ አገራት በወረርሽኙ ሳቢያ ኹሉን ነገር ዘግተው ስለነበር የተወሰነው የሕብረተሰብ ክፍል የሚበላው አጥቶ ነበር። በእኛ አይደርስም አይነት እሳቤ አሜሪካና ብራዚል በኋላ ላይም ሕንዳውን እየተፈራረቁ በመዘናጋታቸው አሁን ድረስ የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ ሆነዋል። በተለይ አሜሪካ አስከፊ የሚባል ጊዜን በማሳለፏ ብዙዎችን ሥራ አጥ አድርጋለች።

የወረርሽኙ ክፉ ጎኑ እንዳለ ሁኖ በጎ ጎንም ነበረው። አልዘለቀም እንጂ የሰው ልጅ የተሻለ እንዲተሳሰብ፣ ልግስናም እንዲለመድ ማድረጉን የሚናገሩ አሉ። አንዳንዶች ለክፉ ጊዜ ብለው ምግብና ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን በገፍ ሲያከማቹ የታዩ ነበሩ። አጋጣሚውን እንጠቀም በሚል በተለያዩ ቁሶችና ምግቦች ላይም ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ በሰው ችግር አላግባብ ለመበልጸግም የሞከሩ ነበሩ።

በእኛ አገርም ጭምር ነጭ ሽንኩርት በሽታውን ያጠፋዋል፤ ፌጦ መድኃኒት ነው፤ ሎሚ ሳይቀር ያባርረዋል የሚል ወሬ ሥር በመስደዱ ዕቃዎች ዋጋቸው እንዲያሻቅብ ሆኖ ነበር። ምንም ሳይንሳዊ ማስረጃ ሳይኖር፣ ማን እንደተናገረውም ሳይታወቅ የሚናፈሰው ወሬ ነጋዴዎቹን እስከማስጠርጠርና እስከማስቀጣት ደርሶ ነበር። “እንዲህ አድርጉ” የሚባል ያልተረጋገጠ ወሬ በኹሉም አገራት የመስፋፋቱን ያህል፣ ቫይረሱ ከምን እንደመጣም የሚሰነዘር መላምት የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። የሌሊት ወፍ፣ አሳማና የመሳሰሉ እንስሳት ናቸው ከሚል ወሬ ጋር፣ ከዓመታት በፊት በተሰራ ፊልም ተመሳሳይ ሒደቱ ታይቷል የሚሉ የሴራ ንግርቶችም ቡና መጠጫ ሆነው ነበር። እገሊት አገር ናት ሆን ብላ በቤተሙከራ ሠርታ ያሰራጨችው በሚልም፣ የቃላቱ ጦርነት ሕዝብ ዘንድ ደርሶ በዐይን በማታይ ጥይት እያለቅን ነው እየተባለም ብዙ ተወርቷል።

ከኮሮና ቫይረስ መንስዔ ጀምሮ ማን እንዳመጣው፣ ለምን በአጭር ጊዜ መቆጣጠር እንዳልተቻለ ጭምር ከሚነዛው ወሬ በተጨማሪ፣ መከላከያ ተብለው የሚነገሩ ቁሶችም ላይ የነበረው ውዥንብር ቀላል አልነበረም። አፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) አስፈላጊ ነው ተብሎ ቢታመንበትም፣ ትንሽ የነበረውን ምርት ሕዝቡ ሸምቶ የሕክምና ባለሙያዎችን እንዳያሳጣቸው በሚል ግዴታው ቢዘገይም እስካሁን የማይቀበሉት አሉ። በአገራችን ክፍላተ-አገራት ብቻ ሳይሆን በዋናዋ ከተማም ጭምር ጥቅሙን የማይቀበሉ ብዙ ናቸው። ግዴታ መሆኑን ፈርተው ላለመቀጣት ወይም አገልግሎት ላለማጣት ብለው የሚጠቀሙትን ያህል፣ ማድረግ የለብንም ብለው የማያደርጉም አሉ። በተለይ በምዕራባውያኑ አገራት የሰብዓዊ መብቴን ይጋፋል በሚል የሚቃወሙት ብዙ ሲሆኑ፣ የግል መብት የብዙኀኑን እስካልጎዳ ድረስ ነው በሚል፣ ቻይናን ይከሱ የነበረበትን ሒደት ራሳቸው ለመድገም ተገደዋል።

የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት ከሚወሰዱ የመከላከያ ዕርምጃዎች መካከል የእጅ ማጽጃ ‹ሳኒታይዘርም› በተወሰነ መልኩ ብዥታ ተፈጥሮበት ነበር። እንደአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሉ ባይሆንም ተቀባይነቱ እየጨመረ ሲመጣ ዋጋውም ሆነ ሥርጭቱ ጨምሮ ነበር። ሰው ለቁሶቹ ያሳየው ቸልተኝነት በቶሎ ተገልብጦ ምርቶቹ ላይ ከፍተኛ ዕጥረት ተከስቶ ነበር። በእኛም አገር ፋርማሲ ታይቶ የማይታወቅ ወረፋ ለ‹ሳኒታይዘርና ማስክ› ለወራት ያህል ቆይቶ ነበር።

ዋጋው ርካሽ የነበረ የመከላከያ ቁስ እያደር በ10 ዕጥፍ ጨምሮ በመታየቱ አምራች ብቻ ሳይሆን ሌላውም በማምረት ሒደቱና በንግዱ እንዲሳተፍበት በማድረጉ፣ አሁን ድረስ ዋጋው ረክሶ እንዲዘልቅ አድርጎታል። አሁን አሁን ዋጋው ረክሶ የወረርሽኙ አስጊነት ባለበት እንዳለ የመከላከያ አጠቃቀሙ ግን እየቀነሰ ይታያል።

ክትባትን በተመለከተ፣ ከወረርሽኑ መነሻ ጀምሮ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም፣ ሳይሳካ ወራት በማለፋቸው በሽታው እንደኤች አይ ቪ ይሆናል በሚል ብዙዎችን ተስፋ አስቆርጦ ነበር። በዛው ልክ ተመራማሪዎችና መድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ትርፍ ለመዛቅ እንዲመቻቸው ምርምሩን ሌት ተቀን እየተፈራረቁ ሲያካሂዱ ከርመዋል።

“ክትባት ተገኘ” እየተባለ ሙከራው ውድቅ እየተደረገ የብዙዎች ተስፋ እንዲጨልም ከሆነ በኋላ፣ ዘግይቶም ቢሆን በተመሳሳይ ወቅት በርካታ ኩባንያዎች ወደምርት እንደሚገቡ አሳውቀው ነበር። ይህ ከሆነ በኋላ ማን ቀድሞ ይደርሰዋልና ድኃ አገሮች እንዳይበደሉ በሚል ሙግት ዕርዳታ ለጋሹና ተለጋሹ ሲተረማመስ ቆይቷል። በወረርሽኙ ሳቢያ ሥራ አጥተውና ተንኮታኩተው የከረሙት የኢትዮጵያ አየር መንገድን የመሳሰሉ ግዙፍ ኩባንያዎችም ክትባቱን በማመላለስ ጥሩ ገቢ ለማስገባት ችለዋል።

ክትባቱን በተመለከተም እስካሁን ያልጠራ ውዥንብር በሕዝብ ዘንድ እንዳለ ይነገራል። የተወሰኑ ክትባቶችን ለይተው አገራችን እንዳይገቡ ያሉ ስለነበሩ ለሴራ ወሬ ተመችቶ ነበር። ክትባቶቹ የጎንዮሽ ጉዳት ያስከትላሉ፤ የተከተበም በቫይረሱ ይያዛል፤ እንዲሁም አንዳንድ ባለሥልጣናት የውሸት የተከተቡ ለመምሰል ሞክረዋል የሚሉ አሉባልታውች ተናፍሰው ነበር።

በርካቶች በኃይማኖት ሳቢያ ለመከተብ ባይፈልጉም፣ አንዳንዶች ደግሞ ልጅ አጥቢ ነን በሚል ይቃወሙታል። የተለያዩ ማስረጃዎችን በመናገር አንዳንዶች በቫይረሱ ብንሞት ይሻለናል ቢሉም፣ ለራሳችሁ ሳይሆን ለሌላው እንዳታስተላልፉ መከተብ ግዴታችሁ ነው በሚል ሙግቱ እስካሁን አልተቋጨም።

ኮቪድ 19 በዓለማችን ከተከሰተ ኹለት ዓመት ሊሞላው ወር ገደማ የሚቀረው ሲሆን፣ እስካሁን 250 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችን አጥቅቷል። እስካሁን ከ5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ የሞቱ ሲሆን፣ ከ7.13 ቢሊዮን በላይ ክትባት ተሠጥቷል። በወረርሽኙ ከተጠቁ አገራት ቀዳሚዋ አሜሪካ ስትሆን፣ በሟች ቁጥር ብራዚል ትከተላታለች። በተጠቂ ቁጥር ደግሞ ሕንድ ኹለተኛ አገር ስትሆን፣ ብራዚል ሦስተኛ ሁናለች።

ቫይረሱ በአንድ ጃፓናዊ ዜጋ ላይ መጋቢት 4፣ 2012 ኢትዮጵያ ውስጥ ከተገኘ ወዲህ በወረርሽኙ የተያዙ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ከ365 ሺሕ በላይ ነው። በቫይረሱ ተይዘው ሕይወታቸው ያለፈ ታማሚዎችም ከ6 ሺሕ 500 በላይ መሆኑን ወርልዶ ሜትር ይጠቁማል።


ቅጽ 4 ቁጥር 157 ጥቅምት 27 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here