ጀግንነት ምን ይመስላል? ማንንስ ይመስላል? ሁሉም ሰው በተለይም ኢትዮጵያዊ ይህ ከምናቡ የማይጠፋና ከቃሉ ጥሪ እኩል ምስል የሚከስት ጉዳይ ነው። ይህን በምናብ የሚከሰት ምስል አውጥተው፣ ቀለም አዋህደው በሸራ ላይ ማኖርን የታደሉ የስዕል ጥበብ ባለሞያዎች ታድያ ጥቂት አይደሉም። እንደ ዕይታቸው፣ ጊዜና ሁኔታውም በፈቀደላቸውና በገለጠላቸው መጠን ሳይሰስቱ በምልሰት ታሪክን ስለዋል፤ ጀግንነትን በምስል አኑረዋል። ሥራዎቻቸው ከተረት ወይም ከምኞት ሳይሆን ከሕያው ክስተት የመነጩ በመሆናቸው በየትውልዱ እንደ አዲስ የሚነሱ ነጻነትን የሚገዳደሩ ፈተናዎችን ምን መስለን መሻገር እንችላለን የሚለውን ያመላከታሉ፣ ተስፋና ጽናትን አልፎም ኩራትን ያጋባሉ። እንጠይቅ፣ በቀለማት የተሳለው ጀግንነት ምን ይመስላል? የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ይህን አሰናድታለች፤
ደስታ ተክለወልድ በ‹ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት› ላይ ጀግና የሚለውን ቃል ሲተረጉሙ፣ ‹ዠግና፣ ኃይለኛ፣ ጎበዝ፣ ብርቱ፣ ጦረኛ፣ ሐርበኛ፣ አሳዳጅ፣ አባራሪ፣ አሸናፊ፣ ሞት አይፈሬ የጦር ገበሬ› ይሉታል። ይህ ቃል ነጻነቷን አስጠብቃ ለኖረች አፍሪቃዊቷ ኢትዮጵያ የየእለት መዝሙር፣ የክብር ሚዛን፣ ሕያው ሆኖ በገቢር የተገለጠ ነው።
ጀግንነት ተዘምሮለታል። ስንኞች ተዋድደው ዜማ ተቀምሮ ተዘፍኖለታል፤ ቃላት ተቀምመው ቅኔ ተዘርፎለታል፤ በድርሰት በትረካ ተሰምቷል፤ የጀግና ገጸ ሰብእ በመድረክ ተተውኗል፤ በአደባባይ ተፈክሯል። ጥበብ ኢትዮጵያን ጉዳይ ባደረገችባቸው አውዶች ሁሉ ስለ ጀግንነት እና ስለ አርበኝነት ሳትሰለች ተናግራለች።
የስዕል ጥበብም ጀግንነትና አርበኝነት በቀለም አትሞታል። ከነፍስና ከመንፈስ የሚነጋገሩ ከሚመስሉት ከእጅጋየው ሽባባው (ጂጂ) ‹አድዋ› ሙዚቃ፣ ከባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን ‹ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት!› ግጥም፣ ከጌትነት እንየው ‹የቴዎድሮስ ራዕይ› ቴአትር ሥራዎች ባልተናነሰ፣ ቀለማት ተዋህደው በኅብረታቸው ጀግንነትን በምስል አትመዋል። ሰዓሊያንና ሰዓሊያትም በምናባቸው ያለውን የጀግንነት እንዲሁም የአርበኝነት ምስል ሳይሰስቱ በሸራ ላይ አኑረው ለተመልካች አጋርተዋል።
ይህን ጉዳይ ያነሳነው ምን ዐይተን ነው ቢባል እነሆ! አዲስ ማለዳ ባለፈው ሳምንት በኹለት የስዕል አውደ ርዕይ መሰናዶዎች ላይ ታድማለች። አንደኛው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የተዘጋጀና በአዲስ አበባ ሙዝየም ለዕይታ የተከፈተ አውደ ርዕይ ሲሆን፣ ሌላው በአለ ፈለገ የሥነጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ተዘጋጅቶ በዛው ጊቢ የቀረበ ነው።
ኹለቱም ክዋኔዎች ጭብጣቸው ጀግንነትና አርበኝነት ነው። ነገር ግን ለዕይታ የቀረቡባቸው ሥራዎች የተሰባሰቡበት መንገድ ለየቅል ነው። የከተማ አስተዳደሩ የባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ከዚህ መሰናዶ አስቀድሞ በተለያየ ዘርፍ ከፋፍሎ ጥበበኞች ጀግንነትና አርበኝነትን የተመለከተ ሥዕል እንዲያቀርቡና እንዲወዳደሩ አድርጓል። ያንን ተከትሎም የተመረጡ ስዕሎች ናቸው በአዲስ አበባ ሙዝየም ለዕይታ የቀረቡት። የአለ ፈለገ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት የተዘጋጀው ደግሞ ከ60 ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠሩ፣ በኢትዮጵያ የድልና የተጋድሎ ታሪክ ላይ ያተኮሩ፣ ጀግንነትና አርበኝነትን የሚያወሱ ስዕላት ካሉበት ተሰባስበው የቀረቡበት ነው።
የዕይታ ጥበብ ብርታት
‹‹ሁላችን ተሰባስበን በቃል፣ በተግባር፣ በሥነጽሑፍና በትወና የምንጥረው በሰዎች ሕሊና ምስል ለመከሰት ነው። ስዕል ደግሞ ሌላ ቃል ወይም ንግግር ሳያስፈልገው በቀጥታ ምስል የሚፈጥር የጥበብ ዘርፍ ነው።›› አሉ፤ በአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሰርፀ ፍሬስብሐት። ታድያ ጀግንነት እና አርበኝነት እንዲሁም ጀግኖችና አርበኞች በቴአትርና በሙዚቃ ብቻ ሳይሆን በዕይታዊ ጥበባትም በተለያየ መንገድ እንደሚዘከሩና እንደሚተረኩ አንስተዋል።
ምንም እንኳ የክውን ጥበባትን ያህል የዕይታ ጥበባት ከማኅበረሰቡ በቂ ትኩረት የተሰጣቸው ባይሆንና ሁሉም በተገባ መጠን ባይገነዘባቸውም፣ ለአገር ብዙ ጥበባዊ ሐሳቦችን ማቅረባቸውን ሰርፀ አመላክተዋል። በዚህ መሠረት ከድኅረ አድዋ ጀምሮ የስዕል ጥበብ ባለሞያዎች የሠሯቸው የስዕል ሥራዎች ተደርድረው ቢቀመጡ የኢትዮጵያን ታሪክ የመናገርና ያለፈውን የጀግንነት መልክ ማሳየት የመቻል አቅም እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአለ ፈለገ የሥነጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ዳይሬክተር አገኘሁ አዳነ ይህን ነጥብ ያጠነክራሉ። ‹‹የዕይታ ጥበብ ከሰው ልጅ ሰው መሆን ጋር አብሮ የሆነ፤ ከ እስከ የምንለው የሌለው ነው።›› ይላሉ። ሰው በቋንቋ ተናግሮ መግባባት፣ በቋንቋው ጽፎ መልእክት ማስተላለፍና ታሪክ መሰነድ ከመጀመሩ በፊት ይግባባ የነበረው በዕይታ ጥበባት እንደነበር ያወሳሉ።
ከዛም ባሻገር የዕይታ ጥበብ ከራሱ ሙያዊ ጠባይ በመነሳት ማለትም ከያኒው በሚመርጠው መንገድ (በቀለም ቅብ፣ በእንጨት ወይም በድንጋይ ሐውልት በመቅረጽ ወዘተ) ክስተቶችን ሰንዶ ሲያስቀምጥ ቆይቷል፤ እያስቀመጠም ነው። የዕይታ ጥበባት ታሪክን መዘከርና መሰነድ ብቻ አይደለ፣ አገኘሁ እንደሚሉት በዕይታ ጥበባት ታሪክና ክስተቶች በአዲስ መልክ ይተረጎማሉ።
እርግጥ ነው! ይህን ጽሑፍ ለማዘጋጀት መነሻ የሆነው የአውደ ርዕይ መሰናዶም ይህን ያሳያል። እንደምን ቢሉ ኢትዮጵያ በትላንት ያሳለፈቻቸውንና በሕልውናዋ ላይ የተጋረጡ ፈተናዎች በምልሰት አስቃኝቶ የዛሬን ጉዞ በተስፋ ጥርጊያ የሚመራ ሆኖ ስለሚገኝ ነው። ከዛም ባሻገር ስዕላቱ ትላንትን ዛሬ እንዳሳዩ ሁሉ ዛሬም ራሱን በነገ መስታወት እንዲመለከት የሚያስችሉ፣ የቀደመውን የጀግንነትና የአርበኝነት ታሪክ አእማድ አድርገው አገርን በዛ አጽንቶ የማቆየት ዋጋን የሚያመላክቱ ናቸው።
ሰርፀ ፍሬስብሐት በንግግራቸው ይህን ነጥብ እንዲህ ሲሉ አንስተዉታል፤ ‹‹ኢትዮጵያን በተለያየ ጊዜ የሚያጋጥሟት ተደጋጋሚ ፈተናዎች እንዲህ ያሉ [የጀግንነትና አርበኝነት] ገጽታዎችን የግድ በሕሊናችን መሳል የሚጠይቁ ናቸው፤ ስዕሎቹም በየልቦናችን ጀግንነትን ይስላሉ።››
ጀግንነት በየትውልዱ እንዴት ተሳለ?
በአለ ፈለገ የሥነጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ‹ኢትዮጵያዊ አርበኝነት› በሚል ርዕስ ለዕይታ የቀረቡ ሥራዎች ስድሳ ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ ናቸው። እነዚህ ተመሳሳይ ጭብጥን የያዙ ስዕላት የተሳሉበት መንገድና ተመሳሳይ ክስተትን የተረኩበት መንገድ ግን የተለያየ ነው። ለትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር አገኘሁ ያነሳንላቸው አንዱ ጥያቄ ይህ ነበር፤ በትዝብታችሁ ጀግንነት በየትውልዱ እንዴት ተሳለ?
ከስዕል ስብስቦቹ መካከል በዘመነ ኃይለሥላሴ የተሳሉ አውዳቸው ጀግንነትና አርበኝነት፣ መቼታቸው ደግሞ የድል ሜዳ የሆኑ ስዕላት ጠቅለል ባለ መንገድ ለቀደመው ኢትዮጵያዊ አሳሳል ጠባይ የቀረቡ መሆናቸውን አገኘሁ ያስረዳሉ። ይህም ከተጠቀሙት የአሳሳል መንገድ ወይም ከቴክኒክ አንጻር ሲሆን፣ በይዘት ረገድ ደግሞ ‹በአርበኞች ተጋድሎ ብቻ ድል አይገኝም፣ የመለኮት ተራዳኢነት ወሳኝ ነው።› የሚል መልዕክትን የያዙ ናቸው።
‹‹በስዕላቱ በአርበኞች ተጋድሎና በእግዚአብሔር ተራዳኢነት መካከል ተዋረዳዊ ወይም ቅደም ተከተላዊ ግንኙነትና ትስስር አለ።›› ሲሉ ይገልጹታል። በዚህም ዓለማዊ (Secular) ምሰላ እንዲሁም ሃይማኖታዊ ውክልናን በአንድ ላይ ማየት ይቻላል ማለት ነው።
በደርግ ዘመነ መንግሥት ወቅት የተሠሩ የስዕል ሥራዎች በአንጻሩ የመለኮትን፣ የሰማዕታት ወይም የቅዱሳንን ረዳትነት በማውጣት የሰው ልጅ በራሱ ጠንካራና ራሱን የቻለ፣ በመስዋዕትነትና በሞቱ አገር ማስቀጠል የሚችል ራስ – በቅ ነው የሚል መልዕክት ያላቸው ሆነው ይገኛሉ። በዚህ ዘመን ሥራዎች ውስጥ ‹ሰው ደካማ ነው እየተባለ የሌላ ‹ኃይል› ድጋፍ የሚያስፈልገው መሆን የለበትም!› የሚል ሐሳብና ሙሉ ለሙሉ ዓለማዊ መልክ ይታያል።
በዘመኑ እንደቀደመው ሁሉ የአድዋ፣ የማይጨው እና የመቅደላ መሰል ታሪኮች ተስለዋል። ታድያ ከቀደመው አንጻር ሲታይ በአሳሳል ረገድ የስዕል ሥራዎቹ ዘመናዊ የሚባለውን የእውነታዊነት/ተጨባጭነት ወይም ‹ሪያሊዝም› አሳሳል መንገድን የተከተሉ ሆነው ተገኝተዋል። ይህ አንድም በጊዜው የስዕል ምሩቃን የነበሩ ባለሞያዎች በሶሻሊስት አገራት ወደሚገኙ ትልልቅ የሥነጥበብ ተቋማት ሄደው በመማራቸው ምክንያት የመጣ ለውጥ ነው። ይህ የባለሞያዎች ለውጥም የትምህርት ቤቱን ስርዓተ ትምህርትም አብሮ እንደቀየረው ነው አገኘሁ ያወሱት።
ከዛ በኋላ በመጣው የኢሕአዴግ ዘመን ነጻ ገበያ፣ ልማት፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የመሳሰሉት ጉዳዮች አጀንዳ ነበሩ። ማኅበረሰቡም ይህንን ጉዳዬ ብሎ ያዘ። በዚህም የተነሳ የማኅበረሰብ አንድ አካል የሆኑ የስዕል ጥበብ ባለሞያዎችም ሳየቀሩ ትልልቅ ከሚባሉ ገናና የሆኑ ክስተቶች ይልቅ የዘወትር ሕይወት ጉዳይ ያሳስባቸው ጀመር። ከዚህ የተነሳ የሰዎች እለታዊ እንቅስቃሴ ጋር የተገናኙ ስዕላትም በዚህ ወቅት ጎልተው ታይተዋል።
‹‹ነገር ግን በዚህ ወቅት የአርበኝነት ታሪኮች በስዕል አልተሠሩም ማለት አይደለም።›› ይላሉ አገኘሁ። የአገር ደኅንነት እና ሉዓላዊነት እንዲሁም አንድነት ጉዳይ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ሲገባ፣ የስዕል ጥበብ ባለሞያዎችም የማኅበረሰቡ አካል በመሆናቸው ደኅንነት አይሰማቸውም። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የብሔር፣ የሃይማኖትና መሰል ልዩነትን የተከተለ አሉታዊ ንጥጥልና ክርክር፣ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን እየፈለጉ በመቧደን የሚታይ መደራጀት ሲበዛ ስጋት እንደሚገባው ሁሉ፣ የስዕል ጥበብ ባለሞያዎችም ይህን ስጋት ይጋራሉ።
ስለዚህም በዚህ ወቅት የአንድነት መንፈስ አለው የሚባልን ጀግናን ወደኋላ ሄዶ ከመካከለኛው ዘመን መማጣት በስዕል ሥራዎች ውስጥ ማሳየት እንደተስተዋለ አገኘሁ ያስረዳሉ። አፄ ቴዎድሮስ፣ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ፣ አቡነ ጴጥሮስና የመሳሰሉትን ከታሪክ ማኅደር በማውሳት ‹እኛኮ የእነዚህ ጀግኖች ልጆች ነን! እነዚህ ሰዎችን ይህን አገር ለመሥራት ብዙ ዋጋ ከፍለዋልና ትንሽነት ለእኛ የተገባ አይደለም!› የሚል መልዕክትን በሥራዎቻቸው ጎልተው ታይተዋልም ይላሉ።
ታድያ ግን ሁሉም በየዘመኑ ጀግንነትን በየራሱ መንገድ፣ ወቅትና ሁኔታው በፈቀደ መልኩና የየዘመኑን ድባብ በሚያሳይ አዝማሚያ ጀግንነትን በተለያየ መንገድና ይዘት በቀለማቸው አኑረዉታል። ዛሬስ ነገ ላይ የሚታይ የጀግንነት ምስል እንዴት እየተሳለ ይሆን?
ተረካቢ የስዕል ጥበብ ባለሞያዎች ምን ይላሉ?
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ከወራት በፊት ነበር ፍላጎት ያላቸውና የስዕል ጥበብን የሚያውቁበት ባለሞያዎች ሥራዎቻቸውን እንዲያቀርቡና እንዲወዳደሩ ጥሪ ያቀረበው። ውድድሩ በአራት ዘርፍ የተከፈለ ነበር። በዚህ መሠረትም ከ18 ዓመት በታች ያሉ አዳጊ ልጆች፣ ከ18 ዓመት ጀምሮና በላይ የሆኑ በሙያው በልምምድ ላይ ያሉ ከያኒያን፣ አሁን በስዕል ትምህርት ቤቶች ያሉ ተማሪዎች እንዲሁም ተመርቀው ወጥተው በግል ስቱዲዮ እየሠሩ ያሉ ባለሞያዎች ተሳትፈውበታል።
ሥራዎቹ ከጀግንነት እና አርበኝነት ጋር የተያያዙ ሲሆን፣ 38 የሚሆኑ ሥራዎች ለዕይታ ቀርበዋል። ቢሮው እነዚህን የተመረጡ ሥራዎች ‹በአዲስ ምዕራፍ በጀግንነት ማለፍ፣ አገርን ማትረፍ፣ ወገንን መደገፍ› በሚል መሪ ሐሳብ አካትቶ ነው በአዲስ አበባ ሙዝየም ለአንድ ሳምንት ለሚቆይ ጊዜ ለዕይታ ያቀረባቸው።
ሰዓሊት ሔርሜላ ንጉሡ በዚህ አውደ ርዕይ ላይ ሥራዎቻቸው ከቀረበ የስዕል ጥበብ ትምህርት ተማሪዎች መካከል ናት። ‹ድል ለአገር› የሚል ርዕስ የሰጠችውን የስዕል ሥራዋን ለተመልካቾች የተወሰነ ማብራሪያ በመስጠት ስታስረዳ አገኘናት።
ሔርሜላ የስዕል ጥበብን መማር የጀመረችው በኹለት ዓመት ገደማ በፊት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ቤት መቀመጥ የግድ ያለበትን ወቅት ተከትላ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ተናግራለች። በጊዜው የ12ኛ ክፍል የመሰናዶ ፈተና ለመውሰድ በዝግጅት ላይ ነበረች። ሆኖም ትምህርት በወረርሽኙ ምክንያት በመታጎሉ፣ ፈተናውም በሚራዘም ጊዜ ባገኘችው አፍታ ለጥቂት ወራት በ‹ኢንላይትመንት› የሥነጥበብ ትምህርት ማእከል ተምራለች።
ለውድድር ያቀረበችውንና በአውደ ርዕዩ ለዕይታ የተመረጠላትን ሥራ በተመለከተ ስታስረዳ፤ ‹‹አሁን ባለንበት በዚህ ወቅት አገርን መደገፍ ወገንን ማትረፍ ወሳኝና መሠረታዊ ጉዳይ ነው። በዚህ ሰዓት ደግሞ ስለእኛ ስለሁላችን እየጣሩልንና እየለፉልን፣ መስዋዕትነት እየከፈሉልን ያሉት ወታደሮች ናቸው።›› አለች።
ስለዚህም የእነርሱን ዓርማ ከፍ አድርጋ ‹‹እነርሱን ከደገፍን አገርን ደገፍን፣ እነርሱ አገርን ሲደግፉ አገርን አተረፉ›› የሚል ጭብጥ ያለው ስዕል እንደሳለች ታስረዳለች። የስዕል ጥበብ ሞያን የሙሉ ጊዜ ሥራዋ የማድረግ ሕልም ያላት ሔርሜላ፣ የስዕል ሥራ የአገር ባለውለታ የሆኑ ጀግኖችን ከፍ በማድረግና በማመስገን፣ አልፎም በዛ ውስጥ አገራዊ ፋይዳ ያለውን መልዕክት በማስተላለፍ ዘመን ተሻጋሪ ማድረግ እንደሚቻል እምነቷን ገልጻለች።
ሌላው ከአዲስ ማለዳ ጋር አጠር ያለ ቆይታ ያደረገው ምንተስኖት ዳዲ ነው። ምንተስኖት የስዕል ጥበብን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተምሯል፤ አሁን ላይ በግሉ የስዕል ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። በአውደ ርእዩ ለዕይታ የተመረጠለትና ያቀረበው የስዕል ሥራ የብዙዎችን ቀልብ መሳብ የቻለ ነው።
‹ምስልሽ አይጉደል› የሚል ርዕስ ያለው ይህ የስዕል ሥራ፣ የኢትዮጵያ ካርታ ምስል እንደ ‹ፐዝል› ተገጣጥሞ ይታይበታል። በካርታው ዙሪያም የኢትዮጵያ መሪዎች የነበሩ ስምንት ሰዎች በተለያየ አንጻርና አኳኋን ሆነው ይገኛሉ። አፄ ዩሐንስ፣ አፄ ቴዎድሮስ፣ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ፣ አፄ ኃይለሥላሴ፣ መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ መለስ ዜናዊ እንዲሁም ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይታያሉ።
በዚህ የስዕል ሥራ ውስጥ ሁሉም መሪዎች በኢትዮጵያ መልክና ገጽታ ላይ የየራሳቸው ድርሻ እንደነበራቸውና እንዳላቸው መናገር እንደፈለገ ምንተስኖት ያስረዳል። ታድያ በዚህ ስዕል ሥራው የኢትዮጵያን ጉዞ በመሪዎች ውስጥ ከማመላከቱ በተጓዳኝ አሁን ላይ ያለው ወጣት የስዕል ጥበብ ባለሞያ ጀግንነትና አርበኝነትን በተለየና በአዲስ መንገድ፣ ከቀለም ቅብ ባለፈ በቅርጻ ቅርጽና በሐውልት ጭምር የመሥራት ምኞት አለው ብሏል።
አክሎም እንዲህ አለ፤ ‹‹በተለይ ተፈሪ መኮንን ተማሪ እያልን እንደማስታውሰው ሁሉም ተማሪ ውስጥ የአርበኝነት ስሜት አለ። የውጊያና የድል ቦታዎች አካባቢ፣ ለምሳሌ አድዋ ላይ ተገኝቶ የሐውልት ሥራዎችን ቢሠራ [ባለሞያው] አይጠግብም። ምክንያቱም ሁሉንም መጀመሪያ ምናቡ ውስጥ ሠርቶታል። ሁላችንም ያንን በምናባችን ያለን ምስል ማውጣትና መግለጽ እንፈልጋለን።››
አርበኝነትና ጀግንነት እንደ አርበኞችና ጀግኖች ሁሉ በስዕል ሸራዎች ላይ መልክ ይዘው በተለያየ ቀለም በነጻነት ተቀብተዋል፤ ተስለዋል። እነዚህ የጀግንነት መልኮች ከምናብ ይፍለቁ እንጂ ጥበበኞቹ ከእውነት የተዋሷቸው ናቸው። ዘመን የቀደሙትን እንደሰነደ ሁሉ የዛሬ ዘመን የጀግንነት መልክም በነባርና በአዲስ ትውልድ እየተሳለ ይገኛል። ጊዜ የመመልከቻ አውድ ሆኖ ሁሉን ማሳየቱ አይቀሬ ነው!
እናብቃ! ባሳለፍነው ቅዳሜ ኅዳር 25/2014 በአዲስ አበባ ሙዝየም ለዕይታ ክፍት የሆነው አውደ ርዕይ እስከ ታኅሳስ 03/2014 ለዕይታ ክፍት ሆኖ ይቆያል። በተጓዳኝ ኅዳር 2/2014 በአለ ፈለገ የሥነጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት የተዘጋጀው አውደ ርዕይ እስከ ታኅሳስ 28/2014 ክፍት ሆኖ የሚሰነብት ነው።
እናም በትውልድና በዘመን መካከል የስዕል ጥበብ ባለሞያዎች ምን እንደሳሉ፣ ጀግንነት በየትውልዱ ምን መልክ እንደነበረው ለማየትና በእርጋታ መንፈሱን ተጋርቶ አዲስ ዕይታን ለመቃረም ሄዳችሁ ጎብኙ ስትል በዚህ አጋጣሚ አዲስ ማለዳ ጥቆማ ልታደርስ ትወዳለች።
ቅጽ 4 ቁጥር 162 ታኅሣሥ 25 2014



