በአፋር ክልል ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ለአጃቢ 10 ሺሕ ብር እየተከፈለ ነው ተባለ

0
693

በአፋር ክልል ከያንጉዲ ራሳ እስከ ከሮማ-ገዋኔ ባለው መንገድ የሚንቀሳቀሱ የክልሉ ነዋሪዎች፣ በአካባቢው ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላኛው ቦታ ለመንቀሳቀስ ለአጃቢ 10 ሺሕ ብር እየከፈሉ መሆኑ ተገለጸ።
የክልሉ ነዋሪዎች የተለያዩ ተግባራትን ለማከናወን ከሰመራ ወደ አዲስ አበባ ለመንቀሳቀስ ሲፈልጉ፣ በተለይም ‹‹ሕንድፎ›› ተብሎ የሚጠራውን ቦታ ለማለፍ 10 ሺሕ ብር እየከፈሉ መሆኑን የአፋር ክልል ሕዝብ ፓርቲ ሊቀመንበር ሙሳ አደም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የአፋር ክልል ነዋሪዎችን ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላኛው ቦታ ለማሳለፍ ብር የሚከፈላቸው አጃቢ የተባሉት አካላት እነማን እንደሆኑ አዲስ ማለዳ ለማጣራት የሞከረች ሲሆን፣ ባገኘቸው መረጃ መሠረትም በአካባቢው የሚገኙ “የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና ፌዴራል ፖሊስ” አባላት መሆናቸውን ማወቅ ተችሏል።

በመሆኑም፣ የአካባቢው ነዋሪዎች በጦርነቱ ከሚደርስባቸው ጥቃት በተጨማሪ፣ ለመንቀሳቀስ በሚፈልጉበት ወቅት ለአጃቢ ብር በመክፈል ላልተፈለገ ወጪ እየተዳረጉ መሆኑን ነው መረዳት የተቻለው።
አዲስ ማለዳ ነዋሪዎቹ ብር የሚከፍሏቸው አጃቢዎቹ እነማን ናቸው? ስትል ጥያቄ ያቀረበችላቸው ሙሳ አደም፣ የሚከፈለው “ለፌዴራል ፖሊስና ለመከላከያ ሠራዊት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ከሰመራ ወደ አዲስ አበባ ለማለፍ መንገድ ላይ ለአጃቢ ብር የሚከፈልበት ቦታ አለ የሚሉት ሙሳ፣ ለአጃቢ የሚከፈልበት የቦታው ልዩ ስም ‹‹ሕንድፎ›› ተብሎ እንደሚጠራ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ከአፋር ክልል ሕዝብ ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከተገኘው መረጃ መረዳት የተቻለው፣ “ያንጉዲ ራሳ” ተብሎ ከሚጠራው ቦታ ጀምሮ እስከ “ከሮማ ገዋኔ” ባሉት መንገዶች ማኅበረሰቡ ያለ አጃቢ በነፃነት መንቀሳቀስ እንዳልቻለና ለአጃቢ 10 ሺሕ ብር ድረስ ለመክፈል መገደዱን ነው።

ፓርቲው ባሳለፍነው ጥር አራት 2014 ባወጣው መግለጫም፣ “ከያንጉዲ ራሳ እስከ ከሮማ-ገዋኔ ባለው መንገድ ላይ ሕዝባችን በገዛ መሬቱ ላይ በሠላም አልፎ ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ እንዳይሄድ እየተደረገ ያለበት ኹኔታ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ” መሆኑ ገልጾ፣ “ከአንድ ወረዳ ወደ ሌላ ወረዳ በአጃቢ ካልሆነ መንቀሳቀስ እንደማይቻል እየታወቀ በክልሉም ሆነ በፌዴራል መንግሥት መፍትሔ ባለመበጀቱ ምክንያት ሕዝባችን ለአጃቢ 10 ሺሕ ብር እየከፈለ ለመከራ ተዳርጓል። ይህ ችግር በአስቸኳይ መቀረፍ አለበት” ብሏል።

በኢትዮጵያ ከተቀሰቀሰ ከአንድ ዓመት በላይ ባስቆጠረው ጦርነት ሠለባ ከሆኑት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከሚገኙ አካባቢዎች መካከል የአፋር ክልል አንዱ ሲሆን፣ ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ድረስ የአካባቢው ሕዝብ ባልተቋጨ ጦርነት ውስጥ እንዳለ ከክልሉ ሕዝብ ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከተገኘው መረጃ መረዳት ተችሏል።

በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት በሚሠነዝረው ጦርነት የበርካታ ሰዎች ሕይወት እንዳለፈ፣ ቀላል የማይባል ንብረት እንደወደመ፣ እንዲሁም ለምግብነት የሚውሉ እህሎች በመጋዘን ተሰብስበው ቢገኙም በችግር ላይ ላለው ማኅበረሰብ ወቅቱን ጠብቀው እየተሰጡ እንዳልሆነ እና “በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች” የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ማግኘት እንዳልቻሉ በኮሚቴው መረጃ ተብራርቷል።

አዲስ ማለዳ የአካባቢው ነዋሪዎች ለአጃቢ ስለሚያወጡት አላስፈላጊ ወጪ፣ ስለዜጎች የምግብ ዕጥረት ችግር እና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ምን እየተሠራ እንደሆነ ለማወቅ ለአፋር ክልል የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አህመድ ካሎይታ ስልክ የደወለች ሲሆን፣ ኃላፊውም ሥራ ላይ እንደሆኑ ገልጸው ዝርዝር ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆኑም።

አዲስ ማለዳ የአፋር ክልል ነዋሪዎች ለአጃቢ የሚከፍሉትን ክፍያ በተመለከተ ለኃላፊው ጥያቄ ብታቀርብም፣ ጉዳዩ እንደማይመለከታቸው ገልጸው ስልካቸውን ዘግተዋል።

ተመሳሳይ ርዕሶች 

በአፋር ክልል ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገለጸ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)

የአፋር ክልል ምክር ቤት አወል አርባን የክልሉ ርዕሠ መስተዳድር አድርጎ ሲመርጥ አሲያ ከማልን የምክር ቤቱ አፈጉባኤ አድርጎ ሾሟል – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)

በአፋር ክልል የዳሊኮሞ በተባለ ቦታ ከ10ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በመኖራቸዉ አፋጣኝ እርዳታ ተጠየቀ – ዜና ከምንጩ (addismaleda.com)


ቅጽ 4 ቁጥር 167 ጥር 7 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here