ምዕራፍ ኹለት የጦርነቱ መቋጫ ይሆን?

0
1235

ኢትዮጵያ የገባችበት ጦርነት ከአንድ ዓመት በላይ ቢያስቆጥርም አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ አንድ ዓመት ከኹለት ወራት የዘለቀው ጦርነት ከአንድ ወር በፊት ሕወሓት ወደ ትግራይ መመለሱን ተከትሎ የሳምንታት ፋታ አግኝቷል፡፡ የሕወሓትን ወደ ትግራይ መመለስ ተከትሎ መንግሥት የጦርነቱን ምዕራፍ አንድ አጠናቅቄያለው ብሉ መከላከያ ወደ ትግራይ እንዳይገባ መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡

በዚህም ባለፈው አንድ ወር መንግሥት ሕወሓትን ማሸነፉን በመግለጽ እስረኞችን ከመፈታት እስከ ድኅረ ጦርነት ሰነድ ማዘጋጀትና ስለ ድኅረ ጦርነት ከፌዴራል እስከ ወረዳ መምከሩ ይታወሳል፡፡ ጦርነት ሳይቋጭ ስለ ድኅረ ጦርነት ማውራት ተገቢ አይደለም የሚል ትችትም ሲስተናግድ ሠንብቷል፡፡
መንግሥት የድኅረ ጦርነት ሰነድ አዘጋጅቶ ከመከረ በኋላ እልባት ባላገኘ ጦርነት ላይ ስለ አሸናፊነት ማውራት በመቀጠሉ የሚቀርብበት ትችት ሳያበቃ፣ የአገር መከላከያ ምክትል ኢታማዦር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰ ጦርነቱ አለማለቁን እና ምዕራፍ ኹለት ጦርነት እንደሚቀጥል ለመንግሥት ሚዲያዎች በሰጡት ቃለ መጠይቅ አስታውቀዋል፡፡

መንግሥት ስለ አሸናፊነት እና ድኅረ ጦርነት በተደጋጋሚ ማውራቱ እና ምዕራፍ ኹለት ጦርነት ይቀጥላል መባሉን የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ወታደራዊ እና የፖለቲካ ባለሙያዎችን አነጋግሮ የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል፡፡

ለ15 ወራት የዘለቀው የሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት፣ ከአንድ ወር ፋታ በኋላ በድጋሚ አገርሽቷል። ሕወሓት በአፋር ክልል የተጠናከረ ጥቃት መክፈቱን የአፋር ክልል መንግሥት ገልጿል። ሕወሓትም በበኩሉ በአፋር ክልል ላይ ጥቃት መክፈቱን አስታውቋል።
የሰሜኑ ጦርነት ጉዳይ አሁንም ግልጽ መስመር የያዘ ባለመሆኑ በብዙዎች ዘንድ መደናገር እንደፈጠረ ነው። የጦርነቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንደገና አገርሽቶ ይቀጥል ይሆን ወይስ በሠላማዊ መንገድ ይቋጭ ይሆን? የሚለው ጉዳይ ግልጽ ኹኔታ እየታየበት አይደለም። በአንድ በኩል “ምዕራፍ አንድ” የተባለው ዘመቻ በኢትዮጵያ አሸናፊነት መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ሌሎችም የመንግሥት ሰዎች ሲገልጹ ተደምጠዋል። መንግሥት ስለ ድኅረ ጦርነት ወቅት ሠነድ አዘጋጅቶ በየደረጃው ውይይት ማድረጉ፣ ጦርነቱ እንዳለቀ ተደርጎ የሚወሰድበት ኹኔታን ይፈጥራል በሚል በብዙዎች ዘንድ ትችት እያስተናገደ ነው።

በመንግሥት በኩል ጦርነቱ እንዳለቀ የሚያሳዩ እንቅስቃሴዎች መታየታቸው፣ ውጊያው ያለበትን ነባራዊ ኹኔታ ያገናዘበ አይደለም የሚሉ ሐሳቦች ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ ማኅበረሰቡ ድረስ ሲነገሩ ይሠማል። ይህንኑ የመንግሥት ሁኔታ የሚተቹ አካላት አሁንም በአፋር እና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ሕወሓት ጥቃት እየፈጸመ መሆኑን በማንሳት፣ የመንግሥት ኹኔታ ሕዝቡን እያዘናጋው ነው የሚል ነው።

በሌላ በኩል፣ ከሠሞኑ ስለ ጦርነቱ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዝን እና ለፋና ቴቪ መረጃ የሠጡት የአገር መከላከያ ሠራዊት ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከሚሠጡት የተለየ ሐሳብ አንስተዋል። ጀነራሉ ጦርነቱ አለማለቁን እና ዋናው ግዳጅ ገና መሆኑን አንስተው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጦርነቱ እንዳለቀ አድርጎ መውሰድ እንደሌለበት ገልጸዋል።

ጀነራሉ በሠጡት ማብራሪያ፣ መከላከያ ወደ ትግራይ ያልገባው ወይም ድንበር ላይ የቆመው ጦርነቱ ስላለቀ ሳይሆን፣ የጦርነቱ ምዕራፍ አንድ መጠናቀቁን ተከትሎ ለቀጣይ ግዳጅ ለመዘጋጀት እና እረፍት ለማድረግ ነው ብለዋል። “ምዕራፍ አንድ አለቀ ማለት ቃል በቃል ምዕራፍ ኹለት አለ ማለት ነው” ያሉት ጀነራሉ፣ ሕወሓት አሁንም በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ትልቅ ኃይል እያሰባሰበ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጀነራሉ በማብራሪያቸው “ይሄ ኃይል አልጠፋም፣ የግድ መጥፋት አለበት። ይሄ ኃይል ካልጠፋ ኢትዮጵያ ሠላም አታገንም” ያሉ ሲሆን፣ “ትልቅ ግዳጅ ነው ያለን፤ መጀመሪያ ይሄ በደንብ መሰመር አለበት። ያንን ጀሌ ጨርሰን ነው የተቀመጥነው የሚል አስተሳሰብ እኛ የለንም” ብለዋል።
ስለ ጦርነቱ ማለቅ አለማለቅ ማብራሪያ የሠጡት ጀነራሉ፣ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ጦርነቱ እንዳለቀ አድርጎ አይደለም እራሱ መውሰድ ያለበት፤ አላለቀም” ብለዋል። ሕወሓት ዳግም ለኢትዮጵያ ሥጋት እንዳይሆን በተሠራው ሥራ ላይ ጥያቄ የቀረበላቸው ጀነራሉ፣ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ይዞት የገባውን የታንክ፣ አየር መቃወሚያና ተተኳሽ ወደ ትግራይ ይዞ አለመመለሱን ጠቁመዋል። አክለውም፣ ኢትዮጵያን ማፍረስ እንደማይችል ከልቡ እንደገባው እና የጦር መሪዎቹን እንዳጣ ተናግረዋል።

መከላከያ ትግራይን ለቆ ከመውጣቱ በፊት ለስምንት ወራት በትግራይ ክልል በቆየባቸው ጊዜያት፣ ሕወሓት ከተሞችን ለቆ ወደ ጫካ ገብቶ ሕዝቡን በመከላከያ ላይ መሳመጹን ያስታወሱት ጀነራሉ፣ ኹነቱንም የሰው ኃይል ለማሰባሰብ እና 27 ዓመት የቀበረውን ትጥቅ አውጥቶ እራሱን ለማደራጀት ተጠቅሞበታል ብለዋል። በትጥቅ ደረጃ ሕወሓት ለረዥም ዓመታት የተዘጋጀ እንደነበር የገለጹት ጀነራሉ፣ የትግራይ ጫካዎች በትጥቅ የተሞሉ እንደነበሩ አስታውሰዋል። መከላከያ በመንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ትግራይን ለቆ ሲወጣ፣ ሕወሓት በበረሃ የቀበረውን ትጥቅ አውጥቶ እና ከ 250 ሺሕ በላይ ተዋጊ ይዞ አፋር እና አማራ ክልልን መውረሩን ጠቁመዋል።

ምክትል ኢታማዦር ሹሙ ለጦርነቱ አለማለቅ ማሳያ ይሆን ዘንድ በአማራ እና በአፋር አዋሳኝ አካባቢዎች ከሕወሓት ጋር ውጊያዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል። በመንግሥት እና በመከላከያ ሰዎች ስለ ጦርነቱ የሚንጸባረቁ የሐሳቦች ልዩነት እንደቀጠሉ፣ ሕወሓት ከአንድ ወር ዕረፍት በኋላ በአፋር ክልል ከፍተኛ ጥቃት ከፍቶ የተወሰኑ ወረዳዎችን መቆጣጠር ጀምሯል።

የገዥው ብልጽግና ፓርቲ ሰዎች ስለ ድኅረ ጦርነት አጀንዳ መፍጠራቸውን ተከትሎ በሕዝብ በኩል ቅሬታ መፍጠሩ የሚታወስ ነው። ባላለቀ ጦርነት ላይ ስለ ድኅረ ጦርነት አጀንዳ መፍጠር እና ሕዝብን ማዘናጋት፣ በተለይ ለጦርነቱ ተጋላጭ በሆኑት የአማራ እና አፋር አካባቢዎች ላይ ዳግም ወረራ መፍቀድ እንዳይሆን ብዙዎች ሥጋታቸውን ሲገልጹ ነበር።

መከላከያ በተናጠል ተኩስ አቁም ሰኔ መጨረሻ ሳምንት 2013 ከትግራይ መውጣቱን ተከትሎ፣ ሕወሓት ከአንድ ወር በኋላ ወደ አማራ እና አፋር ክልል ዘልቆ በመግባት ከአምስት ወራት በላይ በኹለቱ ክልሎች ጦርነት መካሔዱ የሚታወስ ነው። ሕወሓት ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች በመግባትና ከጊዜ ወደ ጊዜ በርካታ አካባቢዎችን በመቆጣጠር ሰሜን ሽዋ ዞን መድረሱን ተከትሎ፣ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በሕዝብ ትብብር ከኹለቱ ክልሎች ሙሉ በሙሉ ባይባልም ከአብዛኛዎቹ ቦታዎች እንዲወጣ ተደርጎም ነበር።

ሕወሓት ከክልሎች ተገፍቶ መውጣቱንና መከላከያ ወደ ትግራይ እንዳይገባ በመንግሥት ትዕዛዝ መሰጠቱን ተከትሎ፣ ለአንድ ወር ያህል በአዋሳኝ አካባቢዎች አልፎ አልፎ ውጊያ ቢኖርም ወደ ዳግም ጦርነት አልተገባም ነበር። ይሁን እንጂ፣ ከሠሞኑ ሕወሓት በአፋር ክልል ዞን ኹለት በከባድ መሣሪያ የታገዘ ጦርነት መክፈቱን የክልሉ መንግሥት አስታውቋል።

የክልሉ መንግሥት ባወጣው መግለጫ፣ ሕወሓት በወራራ ይዟቸው ከነበሩ አካባቢዎች እንዲወጣ ቢደረግም፣ ከታኅሣሥ 10/2014 ጀምሮ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች የደረሰበትን ኪሳራ ለማካካስ እና ለመበቀል በኪልበቲ ረሱ፣ በአብዓላ እና በተለያዩ ወረዳዎች በኩል ጥቃቶችን እየሠነዘረ ነው ብሏል።
የአፋር ክልል መንግሥት ሕወሓት በወረራ የያዛቸውን አካባቢዎች ለቆ እንዲወጣ እና የሚደርሰው ጥቃት እንዲቆም ቢጠይቅም ጥቃቱ አልቆመም። የክልሉ መንግሥት፣ ሕወሓት ዳግም በጀመረው ጦርነት ከባድ መሣሪያ ወደ ንጹኃን ዜጎች በመተኮስ ሕይወት እየቀጠፈ እና ሆስፒታሎች፣ የጤና ተቋማት እና ትምህርት ቤቶችን ዒላማ ያደረገ የከባድ መሣሪያ ድብደባ እያካሄደ መሆኑን ነው ያስታወቀው። ከሠሞኑ ደግሞ በተደራጀ መልኩ አብዓላ፣ መጋሌና ኤረብቲ ወረዳዎችን በመቆጣጠር እና በራህሌ ወረዳ ላይም ከፊል ቀበሌዎች ድረስ ዘልቆ በመግባት ከባድ ጥቃት ከፍቶ ንጹኃንን በመግደልና በማሳደድ ወረዳዎቹን እያወደመ እንደሚገኝ እና ከ220 ሺሕ በላይ ንጹኃን ከቤት ንብረታቸው እንዳፈናቀለ የአፋር ክልል አስታውቋል።

“ኹሌም ከትንኮሳ አርፎ የማያውቀው የሽብር ቡድኑ ለዘመናት የቆየውን በድንበር የሚዋሰኑ የአፋር እና የትግራይ ሕዝቦችን ግንኙነት ከምንም ሳይቆጥረው፣ ኹለቱን ሕዝቦች በማጋጨት የማይረባ ትርፍ ለማግኘት ሌት ተቀን እየጣረ ይገኛል። እያደረሰ ባለው ጥቃትም የአፋር ንጹኃንን ዒላማ በማድረግ የሽብር ተግባሩን በማስፋት ላይ ነው” ያለው የክልሉ መንግሥት፣ ጥር 16/2014 ባወጣው መግለጫ፣ “አሸባሪው ሕወሓት በአራት ዞኖች ውስጥ በ21 ወረዳዎች ወረራ በማካሄድ የአፋር ሕዝብን በአሰቃቂ ሁኔታ ቢጨፈጭፍም፣ በብዙ ቢሊየኖች የሚገመት ሀብት ንበረት ቢያወድምም፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ እንዲሰደድ ቢያደርግም፣ ለጎረቤት ትግራይ ሕዝብ ሰብዓዊነት ሲባል ዕርዳታ በአፋር አብዓላ በኩል እንዲያልፍ እየተደረገ ነበር። ነገር ግን፣ ጁንታው ለትግራይ ሕዝብ እንኳን ምንም አይነት ርህራሄ እና ዕዝነት የሌለው በመሆኑ በዚሁ ቀጠና ግጭት በመፍጠር አካባቢው የግጭት ቀጠና እንዲሆን እና ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዳያልፍ አድርጓል” ብሏል።

በምዕራፍ የተከፋፈለው ጦርነት ዕጣ ፈንታ
ጦርነቱ ከተጀመረ ከአንድ ዓመት በላይ ቢሻገርም አልፎ አልፎ በወራት ፋታ ልዩነት አሁንም እንደቀጠለ ነው። የጦርነቱ መቋጫም እስካሁን በግልጽ አልተለየም። በአንድ በኩል ሕወሓትን በኃይል አሸንፎ ጦርነቱን ማጠናቀቀ፣ በሌላ በኩል በሠላማዊ መንገድ ጦርነቱን መቋጨት የሚሉ ሐሳቦች ይንጸባረቃሉ።
የመከላከያ ሰዎች “ሕወሓትን ማጥፋት” ይላሉ፤ የገዥው ፓርቲ ሰዎች ደግሞ የደኅረ ጦርነት ሠንድ አዘጋጅተው ባላለቀ ጦርነት ላይ ስለ ድኅረ ጦርነት አጀንዳ ቀርጸው ይወያሉ።

ጦርነቱ ገና ከጅምሩ የተራዘመ እንዳይሆን በብዙዎች ዘንድ ሐሳብ ሲሰጥ የነበረ ቢሆንም፣ ጦርነቱን ማሳጠር አልተቻለም። ሕወሓትን ከአማራ እና አፋር ክልሎች የማስወጣት ሒደቱ ምዕራፍ አንድ የተባለ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ምዕራፍ ኹለት እንደሚቀጥል ጀነራል አበባው ጠቁመዋል።
ሕወሓት በአፋር ክልል የጀመረው ጥቃት የምዕራፍ ኹለት ጦርነት ማሳያ ነው የሚሉት የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍና የልማት ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ታመነ አባተ፣ ጦርነቱ በምዕራፍ ተከፋፈለ እንጂ አላለቀም ይላሉ። ስለ ጦርነቱ ማለቅ አለማለቅ ከመከላከያ ሰዎች ወጭ ሌሎች ሰዎች የሚሰጡት ሐሳብ ሕዝብን ከማደናገር የዘለለ ሚና እንደሌለው የሚገልጹት ሻለቃው፣ በአፋር ክልል ምዕራፍ ኹለት ጦርነት ተጀምሯል ማለት እንደሚቻል ጠቁመዋል።

መንግሥት ጦርነቱን በምዕራፍ የከፋፈለው ከሕወሓት ወጥመድ ለማምለጥ እና በበቂ ዝግጅት ጦርነቱን ለመፈጸም፣ ብሎም ትግራይን ነጻ አውጥቶ ሕወሓትን ለሕግ ለማቅረብ ይሆናል የሚል ግምት አላቸው። ይሁን እንጂ ጦርነቱ በምዕራፍ እየተከፋፈለ መራዘም የለበትም ይላሉ። ጦርነቱን የተራዘመ እንዳይሆን እና ሌላ ምዕራፍ ሦስት ጦርነት እንዳይኖር መንግሥት በከፍተኛ ጥንቃቄ ጦርነቱን በምዕራፍ ኹለት ማጠናቀቅ አለበት ብለዋል።

ጦርነቱ በምዕራፍ ኹለት ሳይጠናቀቅ ከቀረ እና ለሦስተኛ ምዕራፍ የሚሸጋገር ከሆነ፣ መንግሥት በተራዘመ ጦርነት ኪሳራ ውስጥ ሊገባ ይችላል ይላሉ። ጦርነቱ በምዕራፍ ኹለት የማይጠናቀቅ ከሆነ የወታደሩ እና የማኅበረሰቡ ሞራል እንደሚቀዛቀዝና የመሰላቸት ስሜት እንደሚፈጥር ጠቁመዋል። በተጨማሪም የጦርነቱ የኋላ ደጀን ድጋፍ እና ኢኮኖሚው እየቀዘቀዘ ስለሚሄድ ጦርነቱ በምዕራፍ ኹለቱ ዘመቻ ዕልባት ማግኘት እንዳለበት ሻለቃው ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከሰሜኑ ጦርነት በተጨማሪ በሌሎች አካባቢዎች የጸጥታ ችግሮች እንዳሉባት የሚገልጹት ሻለቃ ታመነ፣ በሌሎች አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ችግር በራሱ የሰሜኑ ጦርነት በተራዘመ ቁጥር እየተባባሰ እንደሚሄድ ጠቁመዋል። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ክልል የሚታየው የጸጥታ ችግር ከሕወሓት ጋር የተገናኘ በመሆኑ የጸጥታ ችግሩ መባባሰ ለሕወሓት መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርለት በመግለጽ ነው።

መንግሥት ጦርነቱን በምዕራፍ የከፋፈለው በምክንያት ነው የሚሉት ሻለቃው፣ የሕወሓትን ዝግጅት እና ከዚህ በፊት ከነበረው ጦርነት ልምድ በመውሰድ የጦርነቱን መጨረሻ ማፋጠን አለበት ብለዋል። ጦርነቱ አለቀ ሊባል የሚችለው ዓላማውን ሲያሳካ ነው የሚሉት ሻለቃው፣ የጦርነቱ መጠናቀቅ የሚረጋገጠው መንግሥት ትግራይን ከሕወሓት ነጻ አውጥቶ የሕወሓት መሪዎችን ለሕግ ሲያቀርብ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል።

ለመሆኑ ኢትዮጵያ የገባችበት ጦርነት ወዴት ያመራ ይሆን? በምንስ ይቋጭ ይሆን? የሚለው ጉዳይ አሁንም በተጨባጭ ለመገመት አስቻይ ኹኔታዎች አለመኖራቸውን ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ጠቁመዋል።
እንደ ፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ገለጻ፣ የጦርነቱን መቋጫ ለመገመት አደጋች የሚሆነው መንግሥት ተገማች ያልሆኑ እና በአብዛኛው የማኅበረሰብ ከፍል ያልተጠበቁ ውሳኔዎችን በየጊዜው በመወሰኑ ነው ይላሉ። ከዚህ በፊት እንደታዩት ያልተገመቱ ውሳኔዎች የሚኖሩ ከሆነ አሁንም ጦርነቱ በድርድርም ይሁን በኃይል ወዴት እንደሚያመራ ለመገምት አዳጋች ነው ብለዋል።

መምህሩ እንደሚመክሩት፣ ለኢትዮጵያ የሚበጃት መንግሥት በጦርነቱ እና ከጦርነቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ የሕዝቡን ፍላጎት ባገናዘበ ኹኔታ ከሕዝብ ጋር የሚያለያዩትን ጉዳዮች ማጥበብ ነው ብለዋል። መንግሥት ከሠሞኑ የሚወስናቸው ያልተጠበቁ ውሳኔዎች ከሕዝብ ጋር የሚያራርቁት መሆኑን በመገንዘብ፣ ጦርነቱን በሠላማዊ መንገድ ይሁን በኃይል ለማጠናቀቅ ሕዝብን ያማከለ ሥራ መሥራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

ጦርነቱ በምዕራፍ እየተከፋፈለ በተራዘመ ቁጥር በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል ጥርጣሬ እና ተስፋ መቁረጥ እንደሚፈጠር የሚገልጹት መምህሩ፣ መንግሥት በተቻለ መጠን አወዛጋቢ ውሳኔዎችን በየጊዜው ከመወሰን ተቆጥቦ ጦርነቱን ባጠረ ጊዜ ማጠናቀቅ አለበት ብለዋል። የተራዘመ ጦርነት መንግሥት በሕዝብ ዘንድ ያለውን አመኔታን እንደሚያሳጣ የሚገልጹት መምህሩ፣ የተራዘመ ጦርነት በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በፖለቲካ ጉዳዮች አክሳሪ መሆኑን መገንዘብ እና ጦርነቱን በተጨባጭ መፍትሔ መስጠት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀው ጦርነት ከዚህ በፊት በነበረው ኹኔታ የሚቀጥል ከሆነ፣ ከዋናው ጦርነት በተጨማሪ በሌሎች አካባቢዎች ታጣቂ ኃይሎች ከፈጠሩት የጸጥታ ችግር ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያን የማያባራ የጦርነት አዙሪት ውስጥ እንዳይከታት መጠንቀቅ እንደሚገባ ምሁራኑ ጠቁመዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 169 ጥር 21 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here