ሰኞ ጥር 23 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ የተመራ እና ከመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች የተውጣጣ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን በሳዑዲ አረቢያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አድርጓል።
ቡድኑ ባለፉት አራት ቀናት በነበረው ቆይታ በሪያድ ከኢትዮጵያ ኮሙኒቲ አመራሮች እና አባላት፣ ከሀይማኖት መሪዎች እንዲሁም የንግዱ ማህበረሰብ ጋር የተወያየ ሲሆን፣ ከሳዑዲ መንግስት በኩል ከአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል አብዱል አዚዝ ቢን ሳዑድ ቢን ናየፍ፣ ከሳዉዲ ሮያል ፍርድ ቤት አማካሪ እና የንጉስ ሰልማን የሰብዓዊ እርዳታ ማዕከል የበላይ ተቆጣጣሪ ከሆኑት ከዶ/ር ቢን አብዱልአዚዝ አል ራቢህ ጋር መወያየቱ ተገልጿል፡፡
እንዲሁም የልኡካን ቡድኑ ከእስላማዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ዶክተር አልዱልላቲፍ አልዱልአዚዝ አል-ሼይክ፣ ከፋይናንስ ሚስትር ሞሃመድ ቢን አብዱላህ አልጀዳን እንዲሁም ከሳዉዲ የልማት ፈንድ የኦፕሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ከሆኑት ከኢንጂነር ፈይሰል መሀመድ አል-ቃህታኒ ጋር ውይይት አድርጓል።
በውይይቱ ወቅትም እስር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አያያዝ ስለሚሻሻልባቸው፣ የመኖሪያ ፈቃዳቸው የተቃጠለና የተለያዩ ቅጣቶች የሚጠብቋቸው ነገር ግን በራሳቸው ገንዘብ ተሳፍረው አገራቸው መግባት ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ቅጣት ተነስቶላቸውና ምህረት ተደርጎላቸው ወደ አገራቸው መመለስ በሚችሉባቸው አግባቦች መነሳታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
እንዲሁም ፈቃድ እያላቸው የተለያየ ወከባ ይደርስብናል የሚል ስጋት ያላቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን መኖራቸው ስለሚሰማ ይኸው ሁኔታ ስለሚሻሻልበት፣ እስር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በተቻለ ፍጥነት ዝግጅት ተደርጎ ወደ አገራቸው በሚመለሱበት እና ይህንን ችግር በመፍታት የሁለቱን አገሮች ስትራቴጂካዊ ትብብርና ግንኙነት ወደላቀ አጋርነት ማሸጋገር በሚቻልባቸው አግባቦች ዙሪያ ከፍተኛ ልዑካን ቡድኑ ተወያይቷል።
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n






