የሕውሓት ቡድን ጉዳት ካደረሰባቸው ኢንዱስትሪዎች ውስጥ 27ቱ ወደ ሥራ ተመልሰዋል

0
600

የሕውሓት ቡድን በአማራ እና አፋር ክልል ጉዳት ካደረሰባቸው 82 አምራች ኢንዱስትሪዎች ውስጥ 27ቱ ወደ ሥራ መመለሳቸው ተገለጸ።
ቡድኑ በወረራ የያዛቸውን ቦታዎች በለቀቀ ማግስት በኢንዱስትሪዎች ላይ ያደረሰውን ጉዳት የሚያጠና ቡድን ወደ ቦታው በመላክ የጉዳቱን መጠንና ዓይነት፣ የሚያስፈልገውን ድጋፍ በመለየት መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከባለድርሻዎች ጋር በመቀናጀት በሠራቸው ሥራዎች ጉዳት ከደረሰባቸው 82 በማምረት ላይ ከነበሩና 5 በፕሮጀክት ደረጃ ከነበሩ አምራች ድርጅቶች ውስጥ፣ 27ቱ በከፊል ምርት ማምረት ጀምረዋል ያለው ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነው።
ኾኖም፣ ሙሉ በሙሉ ማምረት እንዲችሉ እና ሌሎች ወደ ሥራ ያልገቡ ኢንዱስትሪዎችንም ወደ ቀድሞ ሥራቸው ለመመለስ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ዝርዝር ጥናት አካሂዶ የዶላር፣ የፋይናንስ፣የጥሬ ዕቃ፣ የመለዋወጫና ሌሎችም አምራች ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችሉ ድጋፎችን በመለየት ለሚመለከታቸው አካላት አቅርቧል ነው የተባለው።
ሌሎች ጉዳት የደረሰባቸው ኢንዱስትሪዎችንም ወደ ሥራ ለማስገባት ባለቤቶች ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር በመሆን ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው ተብሏል።
እንዲሁም በኢንዱስትሪዎቹ ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎች ፋብሪካዎቹን በመጠገን ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ተጠቅሷል።
የሕውሓት ቡድን በወረራ በያዛቸው የአማራና የአፋር ክልል አካባቢዎች የነበሩ ኢንዱስትሪዎችን የቻለውን ነቃቅሎ በመውሰድ ያልቻለውን አገልግሎት እንዳይሰጡ በማድረግ ማውደሙ ይታወቃል።


ቅጽ 4 ቁጥር 170 ጥር 28 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here