የወሸባ ውጤታማነት

0
1149

ወሸባ በመባል የሚታወቀው ታማሚዎችን ለቀናት ለይቶ የማቆየት ተግባር ኮሮና ቫይረስ ከተከሠተ ወዲህ ይበልጥ የታወቀ ክሥተት ነው። በአውሮፓ በ16ተኛው ክፍለ ዘመን የተከሠተን ወረርሽኝ ለመከላከል ተብሎ፣ የንግድ መናኸሪያ ወደነበረችው ቬነስ ከተማ የሚገቡ ነጋዴዎች ሳይወርዱ መርከባቸው ላይ ለ40 ቀናት ተገለው እንዲቆዩ ይደረግ ከነበረው ሒደት ተወስዶ፣ ”ኳረንቲን” ወይም የ14 ቀናት ለይቶ የማቆየት ተግባር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደ ተዋኅስያኑ የሠውነት የቆይታ ጊዜ ተግባራዊ ማድረግ ተለምዷል።

ይህ የወሸባ ጊዜ ሲጀመር በተለምዶ የተወሰነና ምንም ዓይነት ሳይንሳዊ መርኅ ባይኖረውም፣ አሁን ግን በጥናት ላይ የተመረኮዘ ሆኖ በተመሳሳይ ቀኑ እየተቀያየረ ሥራ ላይ ውሏል። ኮሮና ቫይረስ በቻይናዋ ዉሐን ከተማ ከተገኘ ወዲህ፣ ላለፉት ኹለት ዓመታት ያህል ታማሚዎች ቢያንስ ለ14 ቀናት ተለይተው እንዲቆዩ ሲደረግ ነበር። ቫይረሱ ያለባቸው እንደሌለባቸው እስኪረጋገጥ ድረስ ከለይቶ ማቆያ እንዳይወጡ ሲደረግ የነበረው ሒደት አሁን ድረስ አልዘለቀም። ኮቪድ እንዳለባቸው ከተነገራቸው ከ14 ቀናት በፊትም ሕብረተሰቡን እንዲቀላቀሉ ማድረግ እየተለመደ መጥቷል።

ኦሚክሮን የሚባለው አዲሱ ዝርያ ተከስቶ ዓለምን በከፍተኛ ፍጥነት እያዳረሰ ባለበት በዚህ ወቅት፣ እንደመጀመሪያዎቹ ዝርያዎች አደገኛ አይደለም መባሉን ተከትሎ ጥንቃቄውም በዛው መጠን ቀንሶ ይታያል። በበሽታው የተጠቃ ሰው እንኳን ከማኅበረሠቡ ተለይቶ እንዲቆይ ማድረግ ይቅርና፣ ከሥራ ገበታው እንዳይቀርና ደንበኛን ጭምር የታፈነ ቦታ ውስጥ ሁኖ እንዲያገለግል እየተደረገ መሆኑን መታዘብ ይቻላል። የመንግሥት አገልግሎት ሰጪዎችን ጨምሮ የተለያዩ ባንኮች በኮቪድ ምክንያት ለሠራተኞቻቸው ፈቃድ አንሠጥም ሲሉ የተሠማበት ወቅት ላይም ደርሠናል።

ለይቶ ማቆየት አንድ ሰው በሽታውን ወደሌላ እንዳያስተላልፈው ሥርጭቱን ለመገደብ የሚያገለግል ቢሆንም፣ ውጤታማ እንዳልሆነ የወረርሽኙን ሒደት በማስረጃነት በማቅረብ የሚሞግቱ አሉ። ሰውን ሙሉ በሙሉ ለይቶ ለማቆየት ከማስቸገሩም በላይ፣ ቫይረሱ በቀላሉ የሚተላለፍ ዝርያ በመሆኑ፣ እንዲሁም አንድ ሰው ስለመያዙ ከማወቁ በፊት በቀላሉ ሊያስተላልፈው ስለሚችል ውጤታማነቱ ሙሉ በሙሉ በጎ እንደማይሆን የሚናገሩ በርካቶች ናቸው። ይህ ቢሆንም ግን፣ ከሞላ ጎደል ለይቶ ማቆየቱ ሰውየው በበሽታው መያዙ ከተረጋገጠ በኋላ እንዳያስተላልፈው በማድረግ ሥርጭቱን እንደሚቀንሰውና አላስፈላጊ የሕክምና ጫናን እንደሚያስወግድ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

አንድ ሠው ለ14 ቀናት ተለይቶ ይቆይ ሲባል እሱን ማግለል ሳይሆን የሌላውን ደኅንነት ማስጠበቅ እንደሆነ ቢታመንበትም፣ ውጤታማነቱ ግን አጠያያቂ ነው። ሠውነት ውስጥ ከገባ በኋላ ቫይረሱ በጥቂት ቀናት ውስጥ መጥፋት ካልቻለ ለኹለት ሳምንት ብቻ ለይቶ የማቆየት ሥርዓቱን ለሟሟላት ካልሆነ በስተቀር ጠቃሚ አይሆንም የሚሉ አሉ። ያም ተባለ ይህ፣ የቆይታ ጊዜው ውጤታማነት በጥናት መረጋገጥ እንዳለበት ዕሙን ነው።

ስለወሸባ አስፈላጊነት ጥናት አድርገው ግኝታቸውን ሠሞኑን ይፋ ያደረጉ ሳይንቲስቶች እንደሚሉት፣ ለ14 ቀናት ብቻ ለይቶ ማቆየቱ ሙሉ በሙሉ ውጤታማ እንደማያደርግ ነው። ቫይረሱ በሠውነታችን ውስጥ ከወር በላይ ሊቆይ የሚችልበት ኹኔታ ስላለ ለኹለት ሳምንት ብቻ መወሸቡ ያን ያህል ወረርሽኙን ለመቆጣጠር አያስችልም ብለዋል። በሠውነት ውስጥ እንዳለ ምንም ዓይነት ምልክት ሳያሳይ ሊቆይ የሚችልበት አጋጣሚም ሠፊ ስለሆነ፣ የለይቶ ማቆያ ጊዜው እንደታሰበው ውጤታማ አያደርግም ሲሉ ግኝታቸውን ይፋ አድርገዋል።

‹ፍሮንቲርስ ኢን ሜዲሲን› የተሰኘው መጽሔት ላይ ወጣ ብሎ ‹ሚንት› ድረ-ገጽ ይፋ እንዳደረገው፣ የምርምሩ ግኝት የሚያሳየው አንድ ሠው በቫይረሱ ከተያዘ ከ14 ቀናት በኋላ ቫይረሱን ለሌላ ሠው ሊያስተላልፈው እንደሚችል ነው። በሠውነቱ ውስጥም ለወራት ሊቆይ ስለሚችል በተለምዶ የሚወሠነው የወሸባ ጊዜ ትክክል ላይሆን እንደሚችል ያመላከተ ነው። በ38 ብራዚላውያን ታማሚዎች ላይ ያለማቋረጥ ለሳምንታት በተካሄደ ምርመራ፣ አንድ ጊዜ ሠውነታቸው ውስጥ ቫይረሱ ከተገኘ በኋላ በአማካኝ ለአንድ ወር ውስጥ ምንም ዓይነት ምልክት ሳያሳይ ሊቆይ ይችላል። በጥናቱ ውስጥ ከተካተቱት ውስጥ ኹለቱ ከ70 ቀናት በላይ ሠውነታቸው ውስጥ በመቆየቱ ከዚህ ቀደም የነበረን ግምት ያስቀረ ነው ተብሏል።

በጥናቱ ላይ ተካተው ያልተጠበቀ ውጤት ያሳዩት እነዚህ እንደናሙና የተወሰዱ ሕመምተኞች ቀላል የሚባል ሕመም ያጋጠማቸውና በሽታው እንዳለባቸው በቀላሉ የማይታወቅባቸው እንደሆኑ ተጠቁሟል። ከኹሉም ግኝት ያስደነቃቸው አንድ ሕመሙ እንዳለበት የማይገመት ሠው ለ232 ቀናት የቫይረሱ ተጠቂ (ፖዘቲቭ) ሆኖ ከነቫይረሱ የመቆየቱ ጉዳይ ነው። ሠውየው እንዲህ የሆነው 3 ጊዜ የለብህም ከተባለ በኋላ ነው። ያስገረማቸው ይህ ብቻ ሳይሆን ግለሰቡ ከ4 ዓመታት ወዲህ በደሙ ውስጥ ኤች አይ ቪ ያለበት መሆኑ ነው። በአጠቃላይ፣ በጥናቱ መሠረት 8 በመቶ የሚሆኑት ተሳታፊዎች ከኹለት ወር በኋላም ቫይረሱን ወደ ሌላ ሰው ለማስተላለፍ እንደሚችሉ ነው።

ይህ የምርምር ግኝት አዲሱ የኦሚክሮን ዝርያን ሥርጭት ለመቆጣጠር ከ14 ቀናት ያነሰ የወሸባ ጊዜ ይበቃል ለሚሉ አስተማሪ እንደሚሆን ‹ዘ ቴሌግራፍም› አስነብቧል። አምስትም ሆነ ዐስር ቀን ይበቃል የሚሉ፣ ምንም ዓይነት ሳይንሳዊ መሠረት የላቸውም በማለት ጊዜውን ማራዘም እንጂ ማሳጠሩ አደገኛ ነው ተብሏል። የምርምሩ ውጤት የወሸባውን ጊዜ ለማራዘም ከማስቻሉ በላይ ሕብረተሰቡ መቼም ቢሆን መከላከያ መንገዶችን ከመጠቀም ወደኋላ እንዳይል ያደርጋል ተብሏል። የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልን ማድረግና ርቀትን መጠበቅ፣ እንዲሁም የንጽህና መጠበቂያ መንገዶችን የተያዘም ሆነ ያልተያዘ ያለማቋረጥ እንዲጠቀምባቸው ግኝቱ ያሳስባል ሲሉ ሳይንቲስቶቹ አስረድተዋል።

በሠውነት ውስጥ ቫይረሱ ንቁ ሆኖ የሚቆይበት ጊዜ አማካኙ 30 ቀን ነው የተባለ ሲሆን፣ በሴትና በወንዶች ላይ ግን ይለያያል ተብሏል። ሴቶች ሰውነት ውስጥ በአማካኝ 22 ቀናትን ይቆያል ያሉት ተመራማሪዎች፣ በወንዶች ግን ለ33 ቀናት ሳይለቅ በመቆየት ወደሌላ ሰው ሊተላለፍ ይችላል ብለዋል።

የኦሚክሮን የሥርጭት መጠንና ተደጋጋሚነቱ
ኦሚክሮን የተሰኘው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ከቀደሙት ዝርያዎች በይበልጥ እንደሚተላለፍ ቢነገርም፣ በምን ያህል ፍጥነት ይዛመታል የሚለውን በንጽጽር ያረጋገጠ አልነበረም። ከሠሞኑ ግን አዲሱ ዝርያ ከነባሮቹ በ13 በመቶ የበለጠ ይተላለፋል መባሉን ‹ፋይናንሺያል ሪቪው› ዘግቧል።

የአውስትራሊያ ተመራማሪዎች ስለግኝቱ እንደተናገሩት፣ አዲሱ ዝርያ ያን ያህል ጎጂ ባለመሆኑ በቀላሉ ይጠፋል የሚለውን የብዙዎችን ግምት ውድቅ የሚያደርግ ነው። ከኹሉም የበለጠ ተሥፋፊ በመሆኑ ሥርጭቱን ገድቦ ለማቆም ቢያንስ በርካታ ወራትን ሊጠይቅ እንደሚችል ነው። ከዚህ ቀደም እንዳስነበብናችሁ፣ እነሱም በዚህ ጊዜ ብለው እርግጡን ወረርሽኙ ስለሚያበቃበት ጊዜ መናገር እንደማይችሉ ያሳወቁ ሲሆን፣ በአጭር ጊዜ ወደነበረው የሰው ልጆች ሕይወት መመለስ ይቻላል የሚለው ግን እውን እንደማይሆን አመላክተዋል።

ኮቪድ 19 ዓለማችን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሠተ ሠሞን፣ “አንዴ ከያዘ ደግሞ አይዝም” በሚል ራሱ እንደመከላከያ ይሆናል የሚል ዕምነት ነበር። ቀስ በቀስ ግን ይህ አስተሳሰብ በምርምር ውድቅ የተደረገ ሲሆን፣ የሠውነት የመከላከል አቅምን እስከመጨረሻችን አጎልብቶ እንደማይቆይ ታውቋል። የኮሮና ቫይረስ አንዴ ይዞ ከጠፋ በኋላ፣ ሠውነት ከተመሳሳይ ዝርያ ሊጠበቅ የሚችለው ግፋ ቢል ለሦስት ወር እንደሆነ የሚናገሩ አሉ። ስለመከላከያ ክትባቶቹም የአገልግሎት ዘመን በተመሳሳይ ከወራት እንደማዘልቅ ምልከታቸውን የሚያስቀምጡም ጥቂት አይደሉም። ኹሉም የሚስማሙበት ግን፣ ቫይረሱ ዝርያውን ቀይሮ አሁንም በድጋሚ ሊመጣ የሚችልበት ዕድል ሠፊ መሆኑን ነው። በዚህም ምክንያት ሕብረተሰቡ ሳይዘናጋ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረገ ሥራውን እየሠራ ሕይወቱን እንዲመራ ተመክሯል።


ቅጽ 4 ቁጥር 170 ጥር 28 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here