ማክሰኞ የካቲት 1 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ኢትዮጵያን ጨምሮ በሦስት የምስራቅ አፍሪካ አገራት ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ውስጥ የልህቀት ማዕከላት እየተገነቡ እንደሚገኝ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ይህ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ትስስር ፕሮጀክት (EASTRIP) ከዓለም ባንክ በተገኘ በተገኝ ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ የገንዘብ ድጋፍ በኢትዮጵያ፣ ኬኒያ እና ታንዛንያ ውስጥ በሚገኙ 16 የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ውስጥ የልህቀት ማዕከላቱን የመገንባትን አላማ ያነገበ ፕሮጀክት ነው፡፡
የፕሮጅክቱ የሁለት ዓመት ተኩል አፈጻጸም በሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል የተመራ ልዑክ፣ እንዲሁም የዓለም ባንክ፣ የኢንተር ዩኒቨርሲቲ ካውንስል፣ የአስራ ስድስት የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሥራ ሀላፊዎች እና የኢንዱስትሪዎች ተወካዮች በተገኙበት በሞምባሳ ኬኒያ ተከናውኗል፡፡
በዚህም የተቋማቱና የ3ቱ አገራት አፈጻጸም፣ የኮሌጆችና ኢንዱስትሪው ትስስር እንዲሁም በሀገራቱ መካከል ስለሚደረገው የአሰልጣኞች ልውውጥ ውይይት ተደርጎ ባጋጠሙ ችግሮች ላይ የመፍትሄ ሀሳቦች መቀመጣቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያም የቴክኒክና ሙያ ተቋማትንና የኢንዱስትሪዎችን ትስስር ማሳያ የሚሆን በኬኒያ ናሽናል ኮስት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅና በሞምባሳ ወደብ ጉብኝት መካሄዱም ታውቋል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n






