የማይወላውል አቋም ይኑረን!

0
1152

መወላወል ለግለሰብም ሆነ ለመንግሥት የማይጠቅም አቋም የለሽነት ነው። ማንም ቢሆን የሚኖርበትና ራሱንም ሆነ ሌላውን የሚያስተዳድርበት በመርኅ የተደገፈ አቋም ከሌለው የሌሎች ሐሳብ ተሸካሚ መሆኑ አይቀርም።

ኹሉም ሠው አቋም የሚኖረው በራሱ ተነሳሽነትና ኃላፊነት እንጂ ሌላው ሲሠጠው ወይንም የሌላውን ሲከተል አይደለም። በተለይ ሕዝብን አስተዳድራለሁ የሚል አካል ወላዋይ ከሆነና የራሱ አቋም ከሌለው የሌላ ጥገኛ መሆኑ እንደማይቀር አዲስ ማለዳ ታምናለች። መንግሥት በሕዝብ ዘንድ የሚኖረው አመኔታ የሚለካው በአቋሙ እንደመሆኑ፣ መርኁን የማይከተል ወይም አንዱ መጥቶ ሌላ በተተካ ቁጥር የሚቀያይር ከሆነ፣ የነበረው ድጋፍ ይቀንሳል ብቻ ሳይሆን ደጋፊው ጠላት ኹነው እንዲነሱበትና ይበልጥም እንዲናቅ ያደርገዋል።

“ቃል ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” በሚባልበት አገር አቋም የለሽ ኹኖ መዝለቅ እንደማይቻል ግልጽ ነው። አንድ ሠው ቃሉን ጠበቀ የሚባለው ለሌላው አቋሜ ይህ ነው ብሎ እንደማይቀይረው በይፋ ግልጽ አድርጎ ሲናገርና ለመፈጸም ሳይወላውል ነው። አንድ ጊዜ የተናገረውን መጠበቁ እንዳለ ኹኖ፣ በጉዳዮች ላይ አቋም የማይዝና ከመጣው ጋር አብሮ ለመንፈስም ሆነ በኹሉም ለመወደድ የሚጥር ደግሞ ከኹሉም የባሰ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል።

“ግትር መሆን ተገቢ አይደለም” በሚል ብሒል፣ “ዘመኑ ሠጥቶ መቀበል ነው” በሚል አጉል ፍልስፍና አገራዊ ጉዳዮች ላይ መልፈስፈስም ከተጠያቂነት እንደማያድን ሊታወቅ ይገባል። አንድ መንግሥትም ሆነ ግለሰብ የሚነጋገርባቸውንና የማይወያይባቸውን ጉዳዮች ለባለጋራው ብቻ ሳይሆን፣ ለተከታዩም ሆነ ለሕዝብ ጭምር በግልጽ ማሳወቅ እንዳለበት አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።

አንድ ሠው የሚታወቅበት መለያው መልኩ የሚሆነው ገጽታው ለሚያስፈልግበት መታወቂያን ለመሳሰሉ ጉዳዮች ነው። መልክ ውጫዊ እንደመሆኑ የሠውን ባህሪ ለማወቅ ፊቱ ያን ያህል አስፈላጊ የሚሆንበት አጋጣሚ ዝቅተኛ ነው። ከሌላው ለመለየት የሚያግዝ አንድ ገጽታን የያዘ ሠው፣ ምን ዓይነት ሠው ነው የሚለውን ከሌሎች ለመለየትም ሆነ ማንነቱን ለማወቅ ሰብዕናውን መረዳት ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግ ደግሞ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያለውን አቋም ሕዝብ እንዲያውቀው ማድረግ ግድ ይላል። ይህ የሚታወቀው ደግሞ በመመልከት ሳይሆን የሚናገረውን በማድመጥና ከሚሠራው ጋር በማነጻጸር ነው።

በዴሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ ምርጫ የሚካሄደውና ዕጩ የሆነ ሠው ተለይቶ የሚመረጠው የኑሮም ሆነ የሕይወት ፍልስፍናው ሲታወቅ ነው። በብዙ ዓይነት መንገድ ሰዎችም ሆኑ ቡድኖች አቋማቸውን ለሕዝብ አሳውቀው ምረጡኝ ማለት ሲችሉ ነው ሥርዓቱ መቆም የሚችለው። አንድ ሠውም ሆነ ቡድን ከሌሎች ተለይቶ ሊመረጥም ሆነ ተከታይ ሊኖረው የሚችለው የተናገረውን አቋም እንደማቀይርና ቃሉንም እንደማያጥፍ፣ እንዲሁም እንደማይክድ ሲታወቅ ነው። ይህ ካልሆነ ግን፣ ደግሞ አይመረጥም ብቻ ሳይሆን በወላዋይነቱ ስለሚታወቅ፣ ቃሉን የሚያምነውም ስለማይኖር የበታቾቹም ጭምር ከድተውት ቃል የተገባለትን የሥልጣን ጊዜንም መቆየት ይሳነዋል።

ፖለቲከኞች እስኪመረጡ በውብ ቃላት ሕዝብን ማማለላቸው የጊዘው ፋሽን መሆኑ ቢታወቅም፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ባህሪ በመነሳት እንደማያዋጣ ሊታወቅ ይገባል። “እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር” ብሎ ልጁን የሚያስተምር ማኅበረሰብ ለውሸታምና አጭበርባሪ ልቡን ሊከፍት እንደማይችል ፖለቲከኞችነን የሚሉ ሊረዱት ያስፈልጋል።

ውሸት መናገርና ማሳመንን እንደብቃት እየወሰዱ የሚደናነቁ ባለሥልጣናት በሞሉባት ዓለማችን፣ የኛዎቹም ጀማሪዎች አንጋፋዎቹን ሊያስደንቁ ሽቅብ መንደርደር ከጀመሩ ጥቂት ዐሥርት ዓመታት ተቆጥረዋል። ተኩላ መጣብኝ ብሎ በተደጋጋሚ ዋሽቶ የእውነት ሲመጣበት የሚደርስለት ካጣው እረኛ ታሪክ፣ ፍጥጥ ያለ ውሸትን ተናግረው ሲነቃባቸው ማስተባበል የለመዱ ፖለቲከኞቻችን ሊማሩ ግድ ይላቸዋል።

የሕዝብ አካል ነን እያሉ ራሱን ሕዝቡን ለማወናበድም ሆነ ለማደናገር የሚጥሩ አቋማቸው ሥልጣን ይዞ መቀጠል እንጂ፣ ሕዝብን በእኩል ፍትሐዊ ኾኖ ማስተዳደር እንዳልሆነ ሕብረተሰቡ የሚረዳበት ጊዜ ሩቅ ስለማሆን ለራሳቸው ሲሉ ካሁኑ ቢያስቡበት መልካም ነው። ለአገር ጉዳት ያለውን ነገር ለራስ ጥቅም ሲሉ ቁርጥ አቋም የማይወስዱ፣ እንዲሁም ውሳኔያቸውን ለማሳወቅ የሚወላውሉ ብዙ መዘዝ ያለው ችግር ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትፈልጋለች።

ይህን ኹሉ ስለአቋምና መወላወል ያልነው ከሠሞኑ የሚሰሙ አቋም የለሽ ድርጊቶችና መወላወሎች ስለተበራከቱ ነው። በሰሜኑ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተገናኘ “አንደራደርም” ሲባል የነበረ አቋም ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ሲሻርና ሲለወጥ እየተመለከትን እንገኛለን። ድርድር ይኑር አይኑር የማለቱ ብቃት ባይኖረንም፣ መንግሥት ግን በእንዲህ ዓይነት አገራዊ ጉዳዮች ላይ ግልጽ የማያወላውል አቋም ሊኖረው ይገባል። ሕዝብ በተለያየ ፍንጭ እንዲረዳውና ከውጭ የመረጃ ምንጮች እንዲያውቀው ከማድረግ ይልቅ፣ የመንግሥትን እንቅስቃሴ ቢደግፍም ባይደግፍም፣ እንደዜጋ የማይለወጥ የመንግሥትን አቋም ሊያውቅ ይገባል።

እጅ ጠምዛዥ በዝቶ መንግሥት መቋቋም አቅቶት ይሁን አይሁን ግምት ውስጥ ከመግባት፣ ወዳጅም ጠላትም እንዲያውቀው፣ ሕዝቡም ከመላምት እንዲርቅ፣ መንግሥት ነገሮችን አፍረጥርጦ ማሳወቅ ይገባዋል። በእንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ ምስጢር የሚያበዛ ከሆነ ለተቀናቃኙ ምቹ ኹኔታን አንደሚፈጥርም ሊገነዘብ ግድ ይለዋል።

በመንግሥት ደረጃ የአቋም መወላወል የሚታይባቸው ጉዳዮች በርካታ ናቸው ሊባሉ ቢችሉም፣ ጭራሹኑ አቋሙን ይፋ ሳያደርግ ሕዝብን ጉዳት ላይ ሊጥል የሚችልባቸው ጉዳዮችም አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በሠንደቅ ዓላማ ጉዳይ የበርካታ ሠው ሕይወት እየጠፋ በየጊዜው ችግር ሲከሠት አቋሜ ይህ ነው ብሎ ለመናገር አለመድፈሩ፣ ውስጡ ከሕዝብ በተቃራኒ መሆኑን ያመላክታል ለሚሉ ማረጋገጫ እንዳይሆን ሊታሰብበት ያስፈልጋል። ከዕምነት ጋር በተገናኘም የመስቀል አደባባይን ጉዳይ፣ እንዲሁም የሌሎች የቦታ ውዝግቦችንም ሆኑ ከጣልቃ ገብነት ጋር በተገናኘ የሚነሱ ቅሬታዎች ላይ ውሳኔ ለመስጠት የሚያሳየው ዳተኝነት፣ ቀስ በቀስ “መንግሥት ልፍስፍስ ነው” የሚሉ ብዙዎችን ለማሳመን እንዲችሉ ስለሚያደርግና ሥርዓት አልበኝነት እንዲነግስ በር ስለሚከፍት አፋጣኝ ዕልባት ያግኝ ስትል አዲስ ማለዳ በአጽንኦት ትናገራለች።

ሕዝብ በቅድሚያ የማይፈልጋቸውና አንገብጋቢ ያልሆኑ የማስዋብና የመቀየር ሥራዎች በሚሠሩበት ፍጥነት፣ ሕዝብን ሊያፋጁ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ አቋም ይዞ አለማስፈጸም የሕዝብን ጥፋት ከሚፈልጉ ወገኖች ጎን ሊያሰልፍና የማይጠፋ ሥም ሊያሰጥ ስለሚችል መንግሥት ሊያስብበት ይገባል። ግለሰብም ሆነ መንግሥት ምንም ጥሩ ነገር ቢሠራ፣ ሕብረተሰቡ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ ላይ ከወላወለ ወይም አቋም መያዝ ከፈራ፣ አሊያም ብልጣብልጥ ልሁን ካለ፣ የሠራው በጎ ነገር በርካታ ቢሆንም በአንድ ጀንበር ሊረሳ እንደሚችል ይታወቅ።

የማይታመን ከሚከዳው በላይ ያመኑት ሲከዳ የበለጠ ሊጠላ እንደሚችል ከኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ መረዳት እንደሚገባቸው ባለሥልጣኖቻችንን መምከር ያስፈልጋል። ከፋም ለማም አቋም ሲኖር ነው ወዳጅም ሆነ ጠላት ማፍራት የሚቻለው። መሀል ሠፋሪ ሆኖ መቆየት ለሕዝብ እንጂ ለመንግሥት እንደማይበጅ ከመጨረሻው የአፄ ኃይለሥላሴ የሥልጣን ዘመን መማር ይጠቅማል።

መንገድ ለመሻገር የሚወላውል ራሱን ብቻ ሳይሆን ለአደጋ የሚያጋልጠው አሽከርካሪንም ጭምር ነው። ወንዝን በዋና ለመሻገር የፈለገም የማይጨርሠው ውስጥ ገብቶ አቋርጠዋለሁ ወይስ አልችልም እያለ ከወላወለ አዞ ባይኖር እንኳን ሰምጦ መቅረቱ አይቀሬ ነው። ሌላን ለማሻገር ይቅርና ራሱ ለመሻገርም ጭራሹኑ አቋም መያዝ አቅቶት ባለበት የቀረ ደግሞ ከኹሉም የባሰ ነው። ለጊዜው ምን ሆኖ ይሆን በሚል ሠው እየቀረበ ሊጠይቀው ቢችልም፣ መወሠን አቅቶት እየወላወለ መሆኑ ሲታወቅ እንደፍርሃት ችግሩን እንዳያጋባብን በሚል መገለሉ አይቀርም።


ቅጽ 4 ቁጥር 170 ጥር 28 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here