በወለጋ ንብረታቸው የታገተባቸው ለማስመለስ 40 ሺሕ ብር ጉቦ እየተጠየቁ ነው

0
644

በአንገር ጉትን ከተማ የመከላከያ ሠራዊት ገብቷል

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች፣ በሽብርተኝነት የተፈረጀውን የኦነግ ሸኔን ጥቃት ሸሽተው ሠላም ወዳለበት አካባቢ በመሔዱ ላይ ሳሉ፣ በኃይል ተይዞባቸው የነበረወን ንብረት ለማስመለስ 40 ሺሕ ብር ጉቦ ክፈሉ እየተባሉ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት፣ ከአንድ ዓመት በላይ በኦነግ ሸኔ እየተሠነዘረባቸው ያለውን ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት ተከትሎ ንብረታቸውን በመጫን ቤታቸውን ለመልቀቅ ሙከራ አድርገው እንደነበር ነው።

ነገር ግን፣ በአካባቢው የሚገኙ ፖሊሶች “የእናንተ ንብረት አይደለም” በሚል ሠበብ ንብረታቸውን ያገቱባቸው ሲሆን፣ ወደሚመለከተው አካል በመሔድ ንብረታቸውን እንዲመልሱላቸው ሲጠይቁ “40 ሺሕ ብር ጉቦ ክፈሉ” መባላቸውን ነው የተናገሩት።
ከዚህ ቀደም አዲስ ማለዳ በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ አንገር ጉትን ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች፣ በተለያዩ ወቅቶች ንብረታቸው ጭነው ሲወጡ በከተማው አስተዳደር ጽ/ቤት ታግቶባቸው እንደሚገኝ መናገራቸውን ስትዘግብ መቆየቷ የሚታወስ ነው።

አሁን ላይ ንብረታችንን ለማግኘት ጉቦ ክፈሉ ተብለናል የሚሉት የአንገር ጉትን ከተማ ነዋሪዎች ናቸው። ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ካቀረቡት ሰዎች መካከል ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ አንድ ግለሰብ፣ ከ500 ሺሕ ብር በላይ የሚገመት የስምንት አርሶ አደሮች 135 ኩንታል እህል እንደታገተባቸው ነው የገለጹት።

በጊዳ አያና ወረዳ በምትገኘው አንገር ጉትን ከተማ ሸኔዎች ጥቃት መሠንዘራቸውን ተከትሎ ግንቦት 1/2013 ሠላም ወዳለበት አካባቢ እህላቸውን ጭነው ለመውጣት ሙከራ ያደረጉ መሆኑን የሚናገሩት ግለሰቡ፣ ግንቦት 2/2013 ፖሊስች ንብረታቸውን በጉትን ከተማ እንዳገቱባቸውና በመጨረሻም ወደ ሊሙ ወረዳ አርቁምቢ መንደር ኹለት ቀበሌ እንዳስተላለፉባቸው ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል።

ግለሰቡ ንብረታቸው እንዲመለስላቸው ሠሞኑን ወደ ወረዳው ሔደው ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ንብረታቸውን ለማስመለስ ጉቦ መክፈል እንዳለባቸው መነገራቸውን ነው የተናገሩት።

ግለሰቡ አያይዘውም፣ የታገተው የእህል ዓይነት በዋነኝነት ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ እንዲሁም በርበሬ መሆኑን ጠቁመው፣ 170 ሺሕ ብር የሚገመተው ሰሊጥ የግል ንብረታቸው እንደሆነም ጨምረው ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በሊሙ ወረዳ ውስጥ አርቁምቢ መንደር አንድ ቀበሌ፣ ጥር 26/2014 ከረፋዱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ በተነሳ እሳት ብዛታቸው በውል ያልታወቁ በርካታ ቤቶች እየተቃጠሉ መሆኑን አዲስ ማለዳ ሠምታለች።

ስሜ እንዳይጠቀስ ያሉት የሊሙ ወረዳ አርቁምቢ መንደር አንድ ነዋሪ፣ ሐሙስ ጥር 26/2014 ከጧቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ ቤቶች እየተቃጠሉ ነው ያሉ ሲሆን፣ ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ወረዳውም ሆነ የመከላከያ ኃይል አደጋውን ለመከላከል እንዳልሞከረ ተናግረዋል።
ግለሰቡ አክለውም፣ “ከዚህ ክልል መኖራችን አስፈላጊ ካልሆነ የተዘጉት መንገዶች ተከፍተውልን ሠላም ወዳለበት አካባቢ እንድንሔድ መንግሥት ሊረዳን ይገባል” ሲሉ መፍትሔ ይሆናል ያሉትን ሐሳብ ሠጥተዋል።

በተያያዘ፣ ከጥር 24/2014 ጀምሮ በአንገር ጉትን ከተማ መከላከያ መግባቱን የከተማዋ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ የገለጹ ሲሆን፣ ሆኖም ግን ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ለችግራቸው መፍትሔ እንዳላገኙ ነው ያብራሩት።

ስሜ እንዳይጠቀስ ያሉ አንድ የጊዳ አያና ወረዳ ታጣቂ ከ60 ሺሕ በላይ የሚሆኑ የአንገር ጉትን ከተማ ነዋሪዎች ከቤታቸው ተፈናቅለዋል ያሉ ሲሆን፣ የገባው የመከላከያ ኃይል የተዘረፈባቸውን ንብረት እንዲያስመልስላቸውና ተፈናቀዮቹንም ወደየቄያቸው እንዲመለሱ እንዲረዳቸው ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ግለሰቡ አክለውም፣ ከ60 ሺሕ በላይ የሚሆኑ በደለሳ መካኒሳ፣ ሊት በቆ፣ ለሊ ማርያም እንዲሁም፣ አንዶዴ ዲቾ የነበሩ የጊዳ አያና አባውራዎች በአንገር ጉትን ከተማ ተፈናቅለው ነው ያሉት ብለዋል።

አዲስ ማለዳ ወደ ሊሙ ወረዳ አስተዳዳሪ ስልክ በመደወል ለተነሳው ቅሬታ ምላሻቸው ምን እንደሆነ ጥያቄ ያቀረበች ሲሆን፣ አስተዳዳሪውም “ስብሰባ ይዠ ነው፤ በኋላ ምሳ ሰዓት ላይ ደውል” የሚል ቀጠሮ ሰጥተው የነበረ ቢሆንም፣ በቀጠሮው ሰዓት ግን ስልካቸውን ሊያነሱ ፈቃደኛ አልሆኑም።

ከዚህም በተጨማሪ፣ አዲስ ማለዳ ወደ አንገር ጉትን ከተማ ከንቲባ ስልክ የደወለች ሲሆን፣ ከንቲባው ጥያቄውን ከሠሙ በኋላ ስልኩን በመዝጋታቸውና በድጋሚ ሲደወል ለማንሳት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ለቀረበው ቅሬታ ምላሻቸውን ለማግኘት ሳይቻላት ቀርቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 170 ጥር 28 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here