በምዕራብ ጎንደር ዞን ተከስቶ የሰነበተውን ግጭት ተከትሎ 37 ሰዎች በነፍስ ግድያ እንዲሁም 101 ግለሰቦች በስርቆትና ሌሎች ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለፀ።
በተያያዘ በመተማ ዮሐንስ ከተማ በተቃጠሉ የግለሰቦች ቤት ውስጥ ለታንክ እና ለከባድ ምሽግ ማጥቂያ የሚያገለግሉ ከባድ መሳሪያዎችም ጭምር መገኘታቸውን የአማራ የብዙኃን መገናኛ ድርጅት ዘገባ ያስረዳል።
መሳሪዎቹ ለአገር መከላከያ ሠራዊት እና ለተፈቀደላቸው የፀጥታ አካላት ብቻ የሚፈቀዱ ቢሆንም በግለሰቦች ቤት ተገኝተዋል ተብሏል።
ከመሳሪያዎቹ ጋር የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት የደንብ አልባሳት እንዲሁም ሐሰተኛ የብር ኖቶችና አደንዛዥ ዕፆች መገኘታቸውም ታውቋል።
የ33ኛ ዓባይ ክፍለ ጦር 1ኛ ብርጌድ 1ኛ ሻለቃ አዛዥ ሌተናል ኮሎኔል አንገሶም አርአያ የተያዙት የቡድን መሳሪያዎች መሆናቸውን ጠቅሰው ሌሎች መሣሪያዎች አሁንም በግለሰቦቹ እጅ እንዳሉ እንደሚታመን ተናግረዋል። ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ መንግሥት በቶሎ ለሕግ አለማቅረቡን እንደገመገሙም አክለዋል።
በተመሳሳይ ዜና በሕገወጥ መንድ ከመተማ ወደ መሀል አገር ሲዘዋወር የነበረ 1997 የብሬን ጥይትና 100 የክላሽ ጥይት ሐሙስ የካቲት 7 ሠራባ ኬላ ላይ በጉምሩክ ፈታሾች መያዙን የገቢዎች ሚንስቴር አሳውቋል። አራት ተጠርጣሪዎች አብረው መያዛቸውም ታውቋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 14 የካቲት 9 ቀን 2011