በወቅቱ ካለው የዳቦ ዋጋ ጋር ሲነጻጸር የኹለት ብር ቅናሽ አለው
ከበቆሎና ከስንዴ ዱቄት በአዲስ መልክ ተቀላቅሎ እንዲመረት የተደረገው ዳቦ በሙከራ ተረጋግጦ በመጠናቀቁ ለምግብነት ሊውል መሆኑን የምግብ፣ መጠጥና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ዳቦው ተጋግሮ በሙከራ መረጋገጡንና ለሥርጭት ሊውል መሆኑን የምግብ ፣መጠጥና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዕቅድ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አስራት አያሌው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም፣ ዳቦው ተጋግሮ በሙከራ ከመረጋገጡም በላይ ሠዎች እንዲቀምሱት መሠራጨቱን የተናገሩ ሲሆን፣ ምርቱን ገበያ ላይ ለመዋል በሠፊው የማስተዋወቅ ሥራ እንደቀረ ነው የገለጹት።
የኢንስቲትዩቱ የምግብ ምርቶች ከፍተኛ ባለሙያ መላኩ አገኘ በበኩላቸው፣ ዳቦው በሙከራ ተረጋግጦ አርባ ሰዎች እንዲቀምሱት መደረጉን እና በተገኘው ምላሽ መሠረትም ምርቱ ተቀባይነት እንዳገኘ ጠቁመዋል።
ከስንዴ ዱቄት ጋር በመቀላቀል ለዳቦ ለማምረት የሚያስችለው የበቆሎ ምርት ከአገር ውስጥ የሚገኝ ነው ወይ? ስትል አዲስ ማለዳ ጥያቄ ያቀረበች ሲሆን፣ አገሪቱ ከስንዴ የተሻለ የበቆሎ ምርት ስላላት ከአገር ውስጥ በሚገኘው ምርት ነው የምንጠቀመው ሲሉ አስራት አብራርተዋል።
የበቆሎ ምርት በብዛት አለን የሚሉት መላኩ፣ ባለፈው ዓመት ምርቱ ወደ 9.6 ሚሊዮን ቶን አካባቢ እንደነበር ያስታወሱ ሲሆን፣ በባለፈው ዓመት ከተመረተው 5.8 ሚሊዮን ቶን የስንዴ ምርት እንደሚበልጥ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የምታገኘው የስንዴ ምርት ከበቆሎ ምርት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ በመሆኑ የተዘጉ የዳቦ ፋብሪካዎች አሉ የሚሉት መላኩ፣ የበቆሎ ምርት ከስንዴ ምርቱ የተሻለ በመሆኑ በቆሎውን ከስንዴ ዱቄት ጋር አቀላቅሎ ዳቦ በማምረት የዳቦ ዕጥረቱን መቀነስ እንደሚቻል ነው ያመላከቱት።
ባለሙያው አክለውም፣ ዳቦውን ለማምረት ከስንዴ ዱቄት ላይ 15 በመቶ የበቆሎ ዱቄት መጨመር መታሰቡን የጠቆሙ ሲሆን፣ ይህም ቀላል የማይባል ትርፍ እንዳለው ነው የተናገሩት።
ለአብነትም፣ አንድ የዳቦ ፋብሪካ ስንዴ ዱቄትን ለዳቦ ምርት የሚጠቀም ከነበረ፣ 15 ፐርሰንት የበቆሎ ዱቄት ቢቀላቅልበት በተመጣጣኝ አቅርቦት በርካታ ዳቦ ማምረት እንደሚቻል ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።
ባለሙያው አያይዘውም፣ ባለንበት ወቅት የአንድ ኩንታል በቆሎ ዋጋ ወደ ኹለት ሺሕ 200 ብር፣ እንዲሁም የአንድ ኩንታል ስንዴ ዋጋ ሦስት ሺሕ 300 ብር እንደሚደርስ ጠቁመው፣ ሙሉ ለሙሉ ከስንዴ ዱቄት ብቻ ሲዘጋጅ የነበረው ዳቦ 15 በመቶ የሚሆነውን መጠን የበቆሎ ዱቄት ሲሸፍን የአንድ ሺሕ ብር ልዩነት ይኖረዋል ነው ያሉት።
እንደ መላኩ ገለጻ ከሆነ፣ ይህ የአንድ ሺሕ ብር ልዩነት ደግሞ በርካታ ዳቦ ለማምረትና ለመሸጥ የሚረዳ መሆኑን ነው መረዳት የተቻለው።
በሌላ በኩል፣ በአዲስ መልኩ ለምግብ አገልግሎት ይውላል የተባለው ዳቦ በስንዴ ዕጥረት ምክንያት የሚከሠተውን የዳቦ አቅርቦት ዕጥረት ከመቅረፉም ባሻገር፣ በወቅቱ ካለው የዳቦ ዋጋ በቅናሽ ስለሚቀርብ በተመጣጣኝ ዋጋ በቂ አቅርቦት ማግኘት እንደሚያስችልም ተጠቁሟል።
ባለንበት ወቅት የአንድ መቶ ግራም ዳቦ ዋጋ ስድስት ብር ነው የሚሉት የምግብ ምርት ባለሙያው፣ 15 በመቶ በተጨመረው የበቆሎ ዱቄት መሠረት የአንድ ዳቦ ዋጋ ከስድስት ብር ወደ አራት ብር ዝቅ አንደሚልና የኹለት ብር ትርፍ እንዳለው ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት። ይህም የዋጋ ቅናሹን ወደ 33 በመቶ ያደርሰዋል ሲሉ መላኩ ጨምረው ተናግረዋል።
በአገር ደረጃ ስምንት ሺሕ አነስተኛና መካከለኛ የዳቦ ፋብሪካዎች አሉ የሚሉት ባለሙያው፣ ፋብሪካዎቹ በአጠቃላይ በዓመት ውስጥ ከ1 ቢሊዮን 952 ሺሕ ቶን በላይ የስንዴ ዱቄት እንደሚያስፈልጋቸው የተናገሩ ሲሆን፣ ነገር ግን በስንዴ ዕጥረት ምክንያት የሚሠሩት ፋብሪካዎች 50 በመቶዎቹ ብቻ እንደሆኑ ጠቁመዋል።
በተያያዘም፣ በአገሪቱ ለሚገኙ ስምንት ሺሕ የዳቦ ፋብሪካዎች በዓመት ውስጥ የስንዴ ዱቄት ለማቅረብም ከ82 ቢሊዮን 830 ሚሊዮን ብር በላይ ይጠይቅ እንደነበር መላኩ አመላክተው፣ 15 በመቶ የበቆሎ ዱቄት ሲጨመርበት ወጪው ወደ 75 ቢሊዮን 739 ብር ዝቅ እንደሚልና ይህም ከ7 ቢሊዮን 395 ሺሕ ብር በላይ ትርፍ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 172 የካቲት 12 2014



