የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በቅርቡ ለሚገነቡ አምስት አዳዲስ የውሃ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ቅድመ ጥናት ለማካሄድ የአማካሪዎች ጨረታ ማውጣቱ ታወቀ። ጨረታውም ተገንብተው ሲያለቁ እስከ 1848 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ይችላሉ ተብሎ ለታሰቡት አምስት የኃይል ማመንጫዎች ወደ ግንባታ ከመግባታቸው በፊት ጥናት እንዲካሄድ በማስፈለጉ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። የኃይል ማመንጫዎቹ በኦሮሚያና አማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የሚገነቡ ሲሆን፤ የሚገነቡትም በግል የዓለም ዐቀፍ የኃይል አመንጪ ኩባንያዎች እንደሆነ በኢትዮጵያ ኤልክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ፕላኒንግ ሥራ አስፈፃሚ ተስፋዬ ባቱ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
ሥራ አስፈፃሚው ጨምረው እንደገለፁት “ኩባንያዎቹ ያመነጫሉ ኮርፖሬሽኑ ደግሞ ይገዛል” ያሉ ሲሆን፤ ከዋጋ ጋር በተያያዘ ተስፋዬ ሲናገሩ ኩባንያዎች የሚጠቀሙት ቴክኖሎጂ ዘመናዊ በሆነ ቁጥር የሚያቀርቡት ዋጋ ዝቅ እንደሚልና ይህም በትንሽ ግብዓት ብዙ ኃይል ማመንጨት መቻላቸው ምክንያት እንደሆነ ገልፃሉ። እስካሁን ባለው ደረጃ ከአምስቱ ኩባንያዎች ሦስቱ ሲፀድቁ ቀሪ ኹለት ኩባንያዎች ላይ ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልጋቸው እና በተንጠልጠል ላይ መሆናቸውን አክለዋል። ግንባታቸው 3 ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንደሚገፈጅ የሚገመተው የኃይል ማመንጫዎች ከዚህ በፊት ቁጥር አራት ድረስ የተገነባውን የገናሌ ዳዋ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ወደ ቁጥር ስድስት በማሳደግ እንዲሁም በአማራ ክልል የጨሞጋ የዳ አንድና ኹለት የኃይል ማመንጫ በዋናነት የሚጠቀሱ እንደሆኑ ተጠቅሷል። ይሁን እንጂ አሁንም ድረስ የገናሌ ዳዋ ቁጥር 5 እና የዳቡስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጄክቶች ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልጋቸው አቅጣጫ ተቀምጦላቸዋል።
ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት 45 ሽሕ ሜጋ ዋት ሊያመነጭ የሚችል እምቅ የውሃ ሀብት እንዳላት ለመረዳት የተቻለ ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ የፀሐይ፣ የንፋስና የእንፋሎት ኃይል ሲታከልበት ማመንጨት የሚቻለውን ኃይል ከፍ እንደሚያደርገውና ይህም ለወደፊቱ ኢትዮጵያ ላቀደችው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ታውቋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በቅርቡ በ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚገነቡ ስምንት የፀሐይ ኃይል በመታገዝ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ፀድቀው ወደ ሥራ እየተገባ እንደሆነ ተስፋዬ ባቱ አስታውቀዋል። በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች የሚገነቡት የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች ሲጠናቀቁ 1 ሺሕ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጩ ይጠበቃል። ኮርፖሬሽኑ ባለፈው በጀት ዓመት በእንፋሎት ኃይልን በመጠቀም ኤሌክትሪክ ኃይል ከሚያመርት ሬክጃቪክ ከተባለ የአሜሪካ ኩባንያ ጋር የ25 ዓመት የግዢ ስምምነት መፈራረሙ የሚታወስ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያ ወደ ጎረቤት አገራት ኃይል በመላክ ከምታገኘው የ90 ሚሊዮን ዶላር የዓመት ገቢ በሠላሳ በመቶ ከፍ እንደሚያደርገው ይጠበቃል።
ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011