ኢትዮጵያ ለኮሮና ቫይረስ ተዘጋጅታ ይሆን?

Views: 964

የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት ይግዛው ተፈሪ ካዛንቺስ አካባቢ ጫማቸውን እያስጠረጉ ሳሉ ነበር አዲስ ማለዳ ያገኘቻቸው። ስለኮሮና ቫይረሱ መስማት ከጀመሩ ኹለት ወር ገደማ እንደሆናቸው የሚገልጹት ይግዛው፣ አሁን ግን በዜና ከመስማት ባሻገር ስለራሳቸው ጤና መጨነቅ መጀመራቸውን ነው የሚናገሩት። በስልሳዎቹ እድሜ መጀመሪያ ላይ እንደሚገኙ ጠቆም አድርገው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመገናኛ ብዙኀን የሚሰሟቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎች መተግበር ጀምሬአለሁ ብለዋል።

‹‹ሰዎችን በመዳፌ መጨበጥ አቁሜአለሁ። ይልቁንም ክንዳቸው ላይ ነው የምጨብጣቸው›› ሲሉም በእጅ መጨባበጥ መቀነሳቸውን የሚያስጠርጉትን ጫማቸውን እየተመለከቱ እና በጉዳዩ ስጋት እንደገባቸው በሚያሳብቅ ሁኔታ በትካዜ ውስጥ ሆነው ይናገራሉ።

በሥራቸው ምክንያት ከሚኖሩበት አፋር ክልል ሰመራ ከተማ ቆይተው የመጡት ይግዛው፣ በሰመራ ከተማ ስለ ቫይረሱ ምንም አይነት እውቀት የለም ይላሉ። ወደ አዲስ አበባ መጋቢት 3/2012 የተመለሱት እኚህ ሰው እንደሚሉት፣ በከተማው ውስጥ በመዘዋወር የአፍ መሸፈኛ ለመግዛት ቢፈልጉም ማግኘት አልቻሉም። ይግዛው ቫይረሱ አዲስ አበባ ገብቶ ይሆናል ብለው እንደሚጠረጥሩ ይናገራሉ። ከጅቡቲ አዲስ አበባ የጭነት መኪና ሹፍርና የሚተዳደሩት እና ቤተሰብ ለመጠየቅ አዲስ አበባ መምጣቸውን አስታውሰው፣ ከመጡ ጀምሮ ግማሽ ቀን አዲስ አበባን እየቃኙ እንደነበርም አንስተዋል።

‹‹አዲስ አበባ ከገባሁ ጀምሮ ሳጠያይቅ የበሽታውን መግባት ወሬ ሰምቻለሁ። በዛ ላይ በቴሌቪዥን እንደምመለከተው ኢትዮጵያ እንደ ሌሎች አገራት በረራ አለማቋረጧ ደግሞ ኮሮና ገበቶ ይሆናል የሚለውን ስጋቴን ከፍ ያደርገዋል›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ያስረዳሉ። ‹‹እኔ በተደጋጋሚ የምንቀሳቀስበት የኢትዮ ጂቡቲ ድንበር ላይ የሚደረገው ቁጥጥር እንብዛም ነው። ካለፈው 15 ቀን ወዲህ የሹፌሮች ሙቀት መለካት የተጀመረ ቢሆንም፣ ቁጥጥሩ ጥብቅ ነው ብሎ መናገር አይቻልም›› ሲሉም ያክላሉ።

የኮሮና መከላከያዎች እና የኢትዮጵያውያን ዝግጀት
የዓለም የጤና ድርጅት በታኅሳስ 21/2012 ነበር በቻይናዋ ዉሃን ከተማ ስለተከሰተው እና እስከ አሁን የሰው ዘርን አጥቅቶ ስለማያውቀው አዲሱ የኮሮና ቫይረስ መኖር የተረዳው። ታዲያ በዉሃን ከተማ ላይ ብቻ ያልተገደበው በሽታው፣ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የ5 ሺሕ 117 ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን፣ 13 ሺሕ 285 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል። 70 ሺሕ 729 ሰዎች ደግሞ በበሽታ ተይዘው አገግመዋል።

ታዲያ እንዲህ በአጭር ጊዜ ዓለማችንን ያዳረሰው ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል፣ የዓለም የጤና ድርጅት ዋና መከላከያ ዘዴዎችን አስቀምጧል። ከእነዚህም መካከል የእጅ መጨባበጥን ማቆም፣ እጅን በየግዜው በማፅጃ ኬሚካሎች ማፅዳት፣ የአፍ እና የፍንጫ መሸፈኛን መጠቀም እና በማስነጠስ ወቅት አፍን በማህረብ ሸፍኖ መሸፈኛውን ወደ ቆሻሻ መጣያ መጨመር ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
አዲስ ማለዳ በአዲስ አበባ ባሉ ፋርማሲዎች ባደረገችው ቅኝት፣ በተለይም የአፍ መሸፈኛ ማስክ በአብዛኛው አይገኝም። አንድ ደንበል አካባቢ ያለ የመድኃኒት መሸጫ ባለቤት እንደሚናገሩት፣ ከዚህ ቀደም የአፍ መሸፈኛውን የሚያመጡላቸው አከፋፋዮች ማምጣት አቁመዋል። አክለውም ከዚህ ቀደም አራት ብር የሚሸጠው መሸፈኛ ወደ 15 ብር ከፍ ብሏል ብለዋል። ከዚህ ቀደም ብዙ ፈላጊ ያልነበረው የእጅ ማፅጃ ኬሚካል ደግሞ ከ55 ብር ወደ 160 ብር ከፍ ማለቱንም ይናገራሉ።

ከጠንካራ ወረቀት መሰል ግብአት የሚሠራው የአፍ መሸፈኛ ደግሞ በ100 ብር እየተሸጠ ሲሆን፣ ይህም በአብዛኛው የመድኃኒት መደብሮች ውስጥ አይገኝም።

የሕክምና ተቋማት ዝግጅት እስከ ምን?
የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር መጋቢት 4/2012 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ጃፓናዊ ዜግነት ያለው የ48 ዓመት ጎልማሳ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው በኮሮና ቫይረስ የተጠቃ ሰው መሆኑን ይፋ አድርጓል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መግለጫውን በሰጠበት ጊዜ አዲስ ማለዳ ተገኝታ የሕክምና ተቋማት፣ የሕክምና ባለሙያዎች እና ቫይረሱን ለማከም የሚያስፈልጉ ግብአቶች ምን ያክል ነው ስትል ጥያቄዋን አቅርባለች። በሚኒስትርነት ሹመታቸው ማግስት ከባድ የቤት ሥራ የገጠማቸው የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ለጤና ባለሙያዎች፣ ለአየር መንገድ ሠራተኞች በየጊዜዉ እየተሰጠ ነው›› ከማለት በዘለለ በጤና ሚኒስቴር በኩል ያለውን መረጃ አልዘረዘሩም።

በዚሁ ቫይረስ የተጠረጠሩ ሰዎችን ለይቶ ሕክምና መስጫ እንዲውል ታስቦ የተዘጋጀዉ የየካ ኮተቤ ሆስፒታል ምን ያክል የሕክምና ባለሙያዎች እንደተመደቡለትም በመግለጫው አልተገለጸም። የሆስፒታሉ ታማሚዎችን የማስተናገድ አቅም ከ500 አስከ 600 እንደሆነ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኤባ አባተ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ኤባ አክለውም፣ ሌሎች የሕክምና ማእከላት እየተዘጋጁ ነው ይበሉ እንጂ፣ በክልሎችና ከከተማ ውጭ ለሚኖረው የኅብረተሰብ ክፍል እየተደረገ ያለ የለይቶ ማቆያ ዝግጅትና የባለሙያ ዝግጅት እንዳለ አልተገለፀም።
የጤና ሚኒስትሯ ቫይረሱን ለመቆጣጠርና ለመከላከል 300 ሚሊዮን ብር መበጀቱን ጠቅሰዋል። ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆንም ተጨማሪ በጀት ለማፈላለግ እየተሠራ እንደሆነ ተናግረዋል።

ስለኮሮና ቫይረስ መረጃዎች እንዴት እየተሰራጩ ነው?
የኖቭል ኮሮና ቫይረስን በቻይናዋ ዉሃን ከተማ መከሰቱን ለመጀመሪያ ጊዜ የተናገረው እና ሰዎች እንዲጠነቀቁ በመንገድ ሲመክር የነበረዉ ቻይናዊዉ ዶክተር ሊ ዊንሊንግ፣ በጊዜዉ ከቻይና መንግሥት ፖሊሶች ቤቱ ድረስ በመሄድ ከድርጊቱ እንዲጠነቀቅ ተነግሮት ነበር። ዛሬ በሕይወት የሌለው ሊ ሐሰተኛ ወሬ አሰራጭተሃል ተብሎ በወቅቱ በፖሊስ ክስ ተመስርቶበት፣ የቻይና መንግሥት ቢወነጅለውም፣ ኮሮና የቻይና ከባዱ ፈተና ከመሆን አልተገደበም።

ኮሮና፣ ዓለም የዲጂታል ዓለምን ከተዋወቀች ወዲህ የተከሰተ የመጀመሪያው ዓለም ዐቀፍ ወረርሽኝ እንደመሆኑ፣ ከተለመደው በተለየ የሰው ልጆች ከፍተኛ ፈተና መሆኑ አልቀረም። ይህም ከበሽታው ውጤት የበለጠ ስጋት እና ሐሰተኛ መረጃዎች ከበሽታው ባልተናነሰ ፍጥነት መዘዋወራቸው፣ ጭንቀትን ፈጥሯል። ሆኖም ያለ ዲጂታሉ ዓለም እገዛ ደግሞ በሽታውን አሁን ለመቆጣጠር በተቻለው ፍጥነት ለመከታተል የሚቻል አይሆንም የሚሉም አሉ።

የይግዛው የቅርብ ወዳጅ የሆኑት ሰለሞን ጉግሳ የ75 ዓመት አዛውንት ናቸው። ከወዳጃቸው በተለየ ስለ ቫይረሱ ፍርሀትና ስጋት እንደሌለባቸው ይናገራሉ። በሽታውን ለመከላከል የሚቻልባቸው ተብለው የሚጠቀሱት መንገዶች በኢትዮጵያ ለመተግበር የማይቻሉ ናቸው ብለው እንደሚያምኑም ይናገራሉ።

‹‹እንደዚህ በታክሲ ታፍገን እየሄድን፣ አውቶቡሱን እና ባቡሩንም እንደምታውቀው ነው። ስለዚህ እንዴት ነው በትንፋሽ የሚተላለፈውን ይህንን በሽታ የምንከላከለው›› ሲሉ ይጠይቃሉ። ‹‹ስለዚህ በከንቱ መጨነቅ አልፈልግም›› ሲሉም ተናግረዋል።

እንደ ሰለሞን ሁሉ በሽታውን መከላከል አልችልም የሚል አቋም ያላቸው ኢትዮጵያውያን ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም። ከዚህ ባሻገርም ቫይረሱ አፍሪካውያንን አይዝም፣ እንደ ነጭ ሽንኩርት ያሉ ምግቦች ኮሮናን ይፈውሳሉ እና መሰል መረጃዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በማኅበረሰቡ እየተስፋፉ ነው።

ሐሰተኛ፣ የተዛቡ ወይም የሚያደናግሩ መረጃዎችን በማጥራት የመገናኛ ብዙኀን በበሽታው ላይ የሰጡት ትኩረት ማነስ እንዳለ ሆኖ፣ የጤና ሚኒስቴር ያዘጋጀው ነፃ የስልክ መስመርም ለሰዓታት ተያዟል ከማለት ውጪ አለመመለሱ ሌላው ተግዳሮት ነው።

ምንም እንኳን ሌሎች ፖለቲካ ነክ የሐሰት መረጃዎች በሚዘዋወሩበት መጠን የኮሮና ሐሰተኛ መረጃዎች ለጊዜው ባይሰራጩም፣ አሁንም አደናጋሪ የሐሰት መረጃዎች ይዘዋወራሉ።
ኮሮና በዓለም ጤና ድርጅት COVID-19 የሚል ሥያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ስዓት ድረስ በ134 የዓለም አገራት ተሰራጭቶ ገዳይነቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል።
በብዛት በቫይረሱ ከተጠቁ አገራት ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጣሊያን፣ ኢራን፣ ጃፓን፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ስፔን፣ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም በቀዳሚነት ተቀምጠዋል። በቻይና እስከ አሁን 3 ሺሕ 120 ሰዎች በቫይረሱ የሞቱ ሲሆን፣ በሞት ብዛት ከቻይና ቀጥላ ጣሊያን 366 ሞት በማስተናገድ በኹለተኛ ደረጃ ተቀምጣለች።

አፍሪካ ከየትኛውም አኅጉር በተሻለ ከቫይረሱ ጫና ዝቅተኛውን ብታስተናግድም፣ እስከ አሁን ኮሮና ቫይረስ ከተከሰተባቸው የአፍሪካ አገራት ግብፅ፣ ሴኔጋል፣ ደቡብ ሱዳን፣ ናይጄሪያ ኬኒያ እና ኢትዮጵያ ይገኙበታል። ጎረቤት አገር ኬኒያም በሳምንቱ መጨረሻ የመጀመሪያውን የኮሮና ተጠቂ መለየቷን አስታውቃለች።

ከዚህ ቀደም ኮሮና ያሰጋቸዉ የጎረቤት አገር ኬኒያ ዜጎች ‹‹ከኬኒያ ወደ ቻይና የሚደረገው በረራ ይቁም” ሲሉ በአደባባይ ሲቃወሙ መሰንበታቸው ይታወሳል።
ኮሮናን ለመቆጣጠር የሚሠሩ ሥራዎች በኢትዮጵያ ቢኖሩም፣ ኅብረተሰቡ ለቫይረሱ ትኩረት እንዳልሰጠውና በቂ ግንዛቤ እንደሌለዉ፣ ግንዛቤ ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎችም መሠረታዊ የሆኑ የቫይረሱ መከላከያ ግብአቶችን ማግኘት አለመቻላቸውን አዲስ ማለዳ በተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍሎች ተንቀሳቅሳ ባደረገችው ቅኝት አረጋግጣለች።

በየካቲት 12 ሆስፒታል የአራተኛ ዓመት የሕክምና ተማሪ ዋለልኝ መለሰ፣ የቫይረሱን አሳሳቢነትና የተሰጠውን የጥንቃቄ ትኩረት የቫይረሱን መተላለፊያ መንገድ በራሱ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ያደርገዋል ይላሉ። ከዚህም ባሻገር ኅብረተሰቡ ለበሽታው ትኩረት እየሰጠው አለመሆኑ ከባድ እንደሆነ ማስተዋላቸውን ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ ኮሮና ቫይረስ ቢከሰት የዓለም ኃያላን አገራት መቋቋም ያቃታቸውን፣ በዓለም ጤና ድርጅት ወረርሽኝ መሆኑ የታወጀለት ይህንን በሽታ፣ መቋቋም መቸገሯ አይቀሬ ነው። ኮሮና ቫይረስ ዓለማችንን በኢኮኖሚው ትሪሊዮኖችን አሳጥቷታል። ከኢኮኖሚው ባሻገር በፖለቲካዊ መጠራጠሮች ውስጥ ከትቶ ማኅበራዊ ግንኙነቶችን ስጋት ውስጥ ከትቷል።

የመከላከልና የዝግጁነት ሥራዎች
ቫይረሱ በዓለም አገራት ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም የካቲት 21/2012 ባካሄደዉ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ፣ ቫይረሱን ለመከላከል በጤና ሚኒስቴር የሚመራ ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራውን እያከናወነ ይገኛል። ኮሚቴው ለጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እየሠራ ያለውን ሥራ የካቲት 30/2012 ሪፖርት ያቀረበ ሲሆን፣ ሪፖርቱን ያቀረቡት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣ ኢትዮጵያ ቫይረሱ እንዳይገባ ከምትሠራቸዉ የመከላከል ሥራዎች ባሻገር ቫይረሱ በአገሪቱ ቢከሰት መቋቋም የሚያስችላትን ቅድመ ዝግጅት ማድረጓን ገልጸው ነበር።

ብሔራዊ ኮሚቴውን የሰበሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቫይረሱ ላይ የሚደረገውን መዘናጋት ትተን መዘጋጀት አስፈላጊ ነው ሲሉ አሳስበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ በቫይረሱ ምክንያት በአዲስ አበባ ሊደረጉ የታሰቡ ዓለም ዐቀፍ ጉባኤዎች ተሰርዘዋል፣ ይህም ኢትዮጵያ ልታገኝ የምትችለውን ገቢ እንዳስቀረባትና የአገሪቱን የቱሪዝም እድገት ከባለፈዉ ዓመት እንዲቀንስ እንዳደረገው አስታውቀዋል። ቫይረሱ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ከማስከተሉም ባሻገር ለዓለም ስጋት መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ እስከ አሁን የኖብል ኮረና ቫይረስ የላብራቶሪ ምርመራ ማረጋገጫ ባለመኖሩ፣ የማረጋገጫ ምርመራ ወደ ሌላ አገር ተልኮ ይደረግ ነበር። ይህ አሠራር ግን ከየካቲት 28/2012 ጀምሮ ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር የምርመራ መሣሪያው ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ በኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አማካኝነት ምርመራው በአዲስ አበባ መሰጠት ተጀምሯል።
ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስን በተመለከተ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን እና መረጃዎችን ለማስጠንቀቅ የሚያስችል ነፃ የስልክ መስመር አገልግሎት ለሕዝብ ይፋ አድርጋለች። ነገር ግን አዲስ ማለዳ በተደጋገሚ ባደረገችው የስልክ ጥሪ ሙከራ የነፃ ስልክ መስመሩ ‹‹ተይዟል›› ከማለት ውጪ ምላሽ አልሰጠም።

ኢትዮጵያስ ኮሮና ቫይረስ ቢከሰት የመቋቋም አቅሟ ምን ያክል ነዉ?
እስካሁን በኮሮና ቫይረስ የተጠቃ ሰው ባይኖርም በሽታው ወደ ሀገር ቢገባ ከሚደረጉ ቅድመ ጥንቃቄዎች መካከል የተለያዩ ማእከላትን ግብዓት በማሟላት አስፈላጊ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑንም የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ኤባ አባተ ተናግረዋል።

እስከ አሁን የቫይረሱ ምልክት ታይቶባቸው በማቆያ ማእከላት ውስጥ አምስት ግለሰቦች የሚገኙ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም በማእከሉ ክትትል ሲደረግባቸው የነበሩ ከ900 በላይ ሰዎች ክትትላቸውን ጨርሰው መውጣታቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቤጂንግ፣ ሆንግ ኮንግ፣ ሻንጋይ፣ ቸንዱ እና ጓንዡ እንደሚበር ይታወቃል። ይህ ቫይረስ ከተሰራጨባቸው ከተሞች መካከል ደግሞ ቤጂንግ እና ሆንግ ኮንግ ተጠቃሽ ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪም ቦሌ ዓለም አቀፍ አየርማረፊያ በርካታ መንገደኞች አቋርጠውት የሚያልፉ ሲሆኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቫይረሱ መነሻ ወደ ሆችዉ ቻይና የሚደርገዉን በረራ ጨምሮ መደበኛ ስራውን ቀጥሏል።

የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በዓለም ጤና ድርጅት ምክረ ሀሳብ መሠረት ለሁሉም መንገደኞች የሰውነት ሙቀት የመለካት ሥራ እየሰራ መሆኑን የሚታወቅ ቢሆንም በክልሎችና በድንበር አካባቢዎች ስፊ ስራዎች በትኩረት አለመሰራታቸዉ እንደሚሰጋቸዉ ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸዉን የሰጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ስጋታቸዉን ገልፀዋል።
የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ የቅድመ መከላከል እና ጥንቃቄ እንዲሁም የድንገተኛ አደጋ ምላሽ ሥራዎች እየተሠሩ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥም በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የሚደረግ የሙቀት ልየታ ሥራ (thermal screening) እና ጊዜያዊ የለይቶ መከታተያ ክፍል ይገኙታል።

በቅድመ ጥንቃቄ ዝግጅት ተግባር የለይቶ ማከሚያ የሕክምና ማእከላት መዘጋጀታቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።

የአለም አገራትን እየፈተነ የሚገኘዉ ኖቭል ኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ቢከሰት ለቫይረሱ ብቻ ለተጠቁ ሰዎች ህክምና እንድሰጥ የየካ ኮተቤ ሆሰፒታል መዘጋጀቱን የጤና ሚኒስቴር ሚኒስቴር ዴኤታ ሊያ ታደሰ(ደ/ር) ተናግረዋል። ሆስፒታሉ አስፈላጊ መሳሪያዎችን በማሟላት እና የጤና ባለሙያዎችን በማሰልጠን መዘጋቱን እንድሁም ሆሰፒታሉ አሁን ባለዉበት ደረጃ 300 ስዎችን ማስተናገድ መቻሉን እና በጥቅሉ 600 ስዎችን ማስተናገድ እንደሚችል አስረድተዋል። ከየካ ኮተቤ ሆስፒታል በተጨማሪ ቢሾፍቱ መከላከያ ሆሰፒታል መዘጋጀቱን ሊያ ሪፖረቱን ባቀረቡበት ወቅት ገልጸዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 71 መጋቢት 5 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com