በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ከችግር ይገላግሉን ይሆን?

1
1023

በየወቅቱ እየተሻሻለና እየተራቀቀ የሚመጣውን ቴክኖሎጂ ተከትሎ በዘመናችን የተለያዩ ምርቶች እየተበራከቱ ይገኛሉ።
የቴክኖሎጅውን መሻሻል ስንመለከት እንኳን በድሮና ዘንድሮ መካከል ይቅርና በትናንት እና በዛሬ መካከል ብዙ ፈጠራዎች የሚስተዋሉበት ዘመን ላይ መድረሳችን የሚታይ ሐቅ ነው።

አሁን ላይ በዓለም ላይ ያለው የተወሠነ የማኅበረሠብ ክፍል ከዘመኑ ጋር የሚሄዱ ጉልበትን፣ ገንዘብን፣ እንዲሁም ጊዜን የሚቆጥቡ አገልግሎቶችን የመጠቀም ደረጃ ላይ ይገኛል። ከእነዚህ አገልግሎቶች መካከል በነዳጅ ኃይል መንቀሳቀሳቸው ቀርቶ በአዲስና በዘመነ መልኩ የኤሌክትሪክ ኃይልን የሚጠቀሙ መጓጓዣዎች ይጠቀሳሉ። ባትሪ የሚሞሉበት (ቻርጅ ማድረጊያ) ተገንብቶላቸው በተለይ በተወሱ የአደጉ አገራት ውስጥ አገልግሎት ላይ ውለዋል የተባለላቸው ተሸከርካሪዎች ቀስ በቀስ የዓለማችንን ጎዳናዎች ይቆጣጠራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የትራንስፖርት አገልግሎትን ጅማሮ መለስ ብለን ስናስታውስ፣ በመጀመሪያ አጭርም ሆነ ረጅም ርቀትን ለመጓጓዝ ሠዎች የሚጠቀሙት እግራቸውን ነበር። ነገሥታት እና መኳንንት ካልሆኑ በስተቀር ሌሎች የማኅበረሠብ ክፍሎች የእንስሳት ትራንስፖርትን የማግኘት ዕድላቸው አነስተኛ እንደነበረ ይነገራል።

ጊዜን ጊዜ እየተካው ሲመጣ የትራንስፖርት ሽግግሩ ከእግር ወደ እንስሳት፣ጋሪና መርከብ፣ እንዲሁምወደ መኪና፣ ባቡርና አውሮፕላን እየተራቀቀ መጥቷል። አሁንም ቢሆን በትራንስፖርት በኩል ያለው ለውጥና መሻሻል እንደቀጠለ ነው።
ሠሞኑን በተለያዩ የሚዲያ ተቋማትና በሞተር ኢንጅነሪነግ ባለሙያዎች በኩል እየተወሳ ያለው ጉዳይ በኤሌክትሪክና በፀሐይ ብርሃን የሚሠሩ መኪናዎች ወደ አገራችን ብቅ ማለታቸውን የተመለከተ ነው።
በዚህም፣ ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን ለማስገባት እየተንቀሳቀሰች መሆኑ እየተገለጸ ነው።

የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ በብዛት ሊመጡ መሆናቸውን ተከትሎ በአዲስ አበባ ውስጥ ያሉ በዘርፉ የተሠማሩ ድርጅቶች እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ። ለአብነትም ባለፈው ታኅሣሥ 19/2014 ማራቶን ሞተር ኢንጂነሪንግም “20 በታዳሽ ኃይል የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችንና ቻርጅ የሚደረጉበትን ማዕከል” ማስመረቁ ይታወሳል።

የማራቶን ሞተር ኢንጅነሪንግ ድርጅት በኹለት ሞዴሎች ማለትም፣ የመጀመርያው ሞዴል “ሐዩንዳይ ኮና” እንዲሁም ኹለተኛውን ደግሞ “ሐዩንዳይ ኮኒክ” የኤሌክትሪክ መኪናዎች መገጣጠሚያ እንዳጠናቀቀ ሲገለጽ ሠንብቷል።
ድርጅቱ በተጨማሪም ከመኪኖቹ መገጣጠም እኩል አስፈላጊ የሆነውን መሠረተ ልማት ወይም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ ማድረጊያ ማዕከልን በ30 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ ባረፈው ፋብሪካው ውስጥ ገንብቷል ነው የተባለው።
የድርጅቱ ዓላማ በኤሌክትሪክ የሚሠራ ተሽከርካሪን ማስተዋወቅ ብቻ አይደለም ያሉት አቶ መልካሙ፣ ለዚያ የሚሆነውን መሠረተ ልማት መገንባትም ሌላው ዕቅዱ ነው ብለዋል።

ማራቶን ሞተር ኢንጅነሪንግ 10 ሺሕ መኪኖችን በዓመት የሚገጣጥም ሲሆን፣ 50 ኪሎ ቮልት የተላበሱ ቻርጀሮች እንዳሉት እና መኪኖቹ እስከ 300 ኪሎ ሜትር የሚንቀሳቀሱት በ15 ደቂቃ ውስጥ ብቻ ቻርጅ ተደርገው እንደሆነ መነገሩን የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ሲዘግቡ ቆይተዋል።

ትራንስፖርትና ኢትዮጵያውያን
ለመጓጓዣነት የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ከመምጣታቸው በፊት ኢትዮጵያዊያን ሠውንም ሆነ ዕቃን ከቦታ ቦታ ለማጓጓዝ ይጠቀሙ የነበረው የትራንስፖርት ዓይነት በቅሎ፣ ፈረስና አህያ የመሳሰሉትን እንሰሳተን መሆነ በተደጋጋሚ ይነገራል።
የቀደሙት የኢትዮጵያ ነገሥታትና ሠራዊታቸው ጭምር አገራቸውን ከጥላት ለመታደግና ዳር ድንበሯን ለመጠበቅ ወደ ጦር ሜዳ ሲያቀኑ ፈረስና በቅሎን ለመጓጓዣነት ይጠቀሙ እንደነበር የአድዋን ጦርነት ማስታወሱ ብቻ በቂ ነው።

ታዲያ ነገሮች በዘመን መሻሻላቸው አይቀሬ ነውና፣ ኢትዮጵያዊያን እንስሳትን ለመጓጓዣነት ከመጠቀም አልፈው ከዘመናት በኋላ በሠው እጅ ወደተፈበረኩ ተሸከርካሪዎች መሸጋገራቸው አልቀረም።
‹‹ሲድሌ›› ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያን ምድር የረገጠች መኪና እንደሆነች በርሔ አርጋው የብሔር ብሔረሰቦች የታሪክ አመጣጥ በሚል ርዕስ በ2005 ለንባብ ባበቁት መጽሐፋቸው አስቀምጠዋል።
እንደ መጽሐፉ ገለጻ ከሆነ፣ የኢትዮጵያን ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የረገጠችውን መኪና ለመጀመሪያ ጊዜ ያሽከርከሯት አፄ ምኒልክ ሲሆኑ፣ ያቀረቧት መካኒክ ደግሞ ጣሊያናዊው ሲኞር አልዋትዬ ናቸው።

ፈጣሪ ለሠው ልጅ ጥበብን የሠጠው እንደመሆኑ መጠን በየጊዜው የተለያዩ ፈጠራዎችን የማበርከቱ ሥራ እስካለንበት ዘመን ድረስ ከመቀጠሉም በላይ፣ ከዘመኑ ጋር ፈጠራው እየዘመነ መምጣቱን ምድር ላይ የሚስተዋሉት ኹነቶች ያስረዳሉ።
ታዲያ በየወቅቱ የሠው ልጅ የሚያመርታቸው የፈጠራ ሥራዎቹ ከአንዱ አገር ወደ ሌላኛው አገር፣ ከአንዱ ወደ ሌላኛው የማኅበረሠብ ክፍል በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ይስፋፋሉ። ሲድሌ የተሰኘችው የመጀመሪያዋ መኪና በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ወደ አገራችን ኢትዮጵያ ብቅ በማለቷ በዘመኑ ለነበሩ ሰዎች የዐይን ብሌን ነበረች።

ከአፄ ምኒልክ ዘመን በመቀጠል ወደ ኢትዮጵያ በርካታ መኪናዎች እንዲገቡ የተደረጉት በንገሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት እንደሆነ ይነገራል። ከዚያም በኋላ ራስ ተፈሪ መኮነን ወደ ዙፋን ከመጡ በኋላ በተለይም አውሮፓን ጎብኝተው ከተመለሱበት ከ1916 ጀምሮ በግዥ መልኩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን የመኪና ባለቤቶች ለመሆን እንደበቁ በርሔ በመጽሐፋቸው በሠፊው አብራርተዋል።

ምንም እንኳ የትራንስርት ቴክኖሎው እየተራቀቀ መጥቶ ባለንበት በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከድሮው የተሻሉ የቴክኖሎጅ ውጤቶች ባለቤት የመሆን ዕድላችን ዕየሠፋ ቢመጣም፣ የትራንስፖርትንን ጉዳይ ወደ ኋላችን መለስ ብለን ስንመለከት በተለይም በ1760ዎቹ አውቶሞቢሎች ለመጀመሪያ ጊዜ ሲንቀሳቀሱ የነበረው በእንፋሎት ሞተር፣ በ1806 በናፍጣ፣ እንዲሁም በ1885 በቤንዚን እንደነበር ይነገራል።

“ችግር መፍትሔን ይፈጥራል” እንዲሉ፣ ከእነዚህ ጊዜያት በኋላም የሠው ልጅ ሌላ የተሻለ ፈጠራን በማምጣት ቴክኖሎጀውን እያራቀቀ የተሻሉና ወጭ የሚቀንሱ መኪናዎችን የመፈብረክ ከንውኑን ተያይዞታል።
በአገራችን ውስጥ ሰዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ማግኘት የጀመሩት በእንፋሎት ኃይል ሲንቀሳሰቀሱ በነበሩት መኪናዎች ሲሆን፣ ከዚህም አልፎ በናፍጣ፣ በቤንዚን በሚንቀሳቀሱ ተሸከርካሪዎች ተጠቃሚ ከሆኑ ዘመናት ተቆጥረዋል።

ምንም እንኳ ኢትዮጵያዊያን በድሮ ዘመን ዕቃ ለመጫንም ሆነ ለመጓጓዝ ሲገለገሉባቸው ከነበሩት እንስሳት አልፈው ዘመኑ ባስገኛቸው ቴክኖሎጂዎች የመጠቀም ዕድል ቢያገኙም፣ አዳዲስ ግኝቶች ሲፈጠሩ ይዘውት የሚመጡት መልካም ጎን እንዳለ ኹሉ ጎጅ ጎንም ተከትሏቸው ስለሚመጣ በነዳጅ የሚሠሩ ትራንስፖርቶችም ብዙዎችን ማማረራቸው የተደበቀ አይደለም።

ከሠሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አሽከርካሪዎችን አስተያየት ብንመለከት እንኳ በነዳጅ ዕጥረት ምክንያት በወረፋ ከመንቃቃታቸው በተጨማሪ ጊዜያቸውንም ሆነ ሥራቸውን በአግባቡ ለማስኬድ እንቅፋት እንደሆነባቸው ሲናገሩ ሰንብተዋል።
በትራንስፖርት በኩል በርካቶችን ካማረረው ጉዳይ አንዱና ዋነኛው በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የነዳጅ ዋጋ ሲሆን፣ ስለጉዳዩም የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት በየወቅቱ ሲናገሩ ይሠማል።

ያለፉትን ዓመታት መለስ ብለን ብንመለከት እንኳ፣ በ2003 ኢትዮጵያ ለነዳጅ ምርቶች ወጪ ያደረገችው 22.8 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ የተሸከርካሪዎች ቁጥርና ነዳጅ ተጠቃሚ ተቋማት ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ወጪው በ2012 መገባደጃ ወደ 62 ቢሊዮን ብር ከፍ ማለቱ የሚታወስ ነው።

ብዙውን ጊዜ የነዳጅ ዋጋ ከፍ ወይም ዝቅ ማለት የሚስተዋልበት ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ ሠሞኑን የነዳጅ ዕጥረት በመከሠቱ በርካታ ተሸከርካሪዎች በየማደያው ተሠልፈው ተስተውለዋል። ይህም በተሳፋሪዎችና አሽከርካሪዎች ሥራ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደፈጠረ ተገልጿል።
ይህንን ችግር መፍታት የሚያስችሉ፣ ከቴክኖሎጅው መራቀቅ ጋር የተያያዙ በኤሌክትሪክና እና በፀሐይ ብርሃን የሚንቀሳቀሱ ዘመናዊ ተሸከርካሪዎች ወደ አገራችን ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል።
በርካታ ሠዎች በአዲስ መልኩ የመጡት ተሽከርካሪዎች፣ በተለይም በነዳጅ ዕጥረት የተከሠተውን ችግር ይቀርፋሉ የሚል ተስፋ እንደሠነቁባቸው ሲናገሩ ይደመጣል።

በርካቶች ይህን ተስፋ ቢሰንቁም፣ በሌላ በኩል ደግሞ በተለይም በአገሪቱ የተከሠተው ጦርነት የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማቶች በወደሙባትና የኃይል አቅርቦት እንደ ልብ በማይገኝባት አገር ኤሌክትሪክን ለተሸከርካሪዎች ማንቀሳቀሻ ለመጠቀም ማሰብ ሳይቀመጡ እግር እንደመዘርጋት ተደርጎ እየተቆጠረ ነው።

በኤሌክትሪክ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች አመጣጥ
በዓለማችን ውስጥ የመጀመሪያዋ ‹‹ፒ1›› የተሰኘችው የኤሌክትሪክ መኪና የተፈበረከው በ1898 ሲሆን፣ የፈበረከውም የስፖርት መኪና ድርጅት መሥራች ፈርዲናንድ ፖርሼ መሆኑን ‹ኢንዱስትሪ ኢንጅነሪንግ› የተሰኘ ድረ-ገጽ ያጠናው ጥናት ያመላክታል። ቢሆንም ግን በኤሌክትሪክ ኃይል ከሚንቀሳቀሱት ተሽከርካሪዎች ዋጋ ይልቅ በቤንዚን የሚሠሩ መኪናዎች ዋጋ አነስተኛ ሆኖ በመገኘቱ የኤሌክትሪክ መኪናዎቹ መስፋፋት ደብዝዞ ነበር።

ጥናቱ እንደሚያመላክተው ከሆነ፣ በ1908 ሔነሪ ፎርድ ያስተዋወቀው ‹‹ቲ›› ሞዴል በቤንዚን የሚንቀሳቀስ መኪና በመመረቱና በተለይም በ1912 አካባቢ ዋጋው 650 ዶላር ስለነበር ተደራሽነቱ እየሠፋ መጥቷል።
የኤሌክትሪክ መኪናዎች ዋጋ 1ሺሕ 750 ዶላር ስለነበርና በቤንዚን ከሚንቀሳቀሱት ጋር ሲነጻጸር ከዕጥፍ በላይ ብልጫ በማሳየቱ ብቅ ብሎ የነበረው መኪናዎችን በኤሌክትሪክ ኃይል የመጠቀም ተግባር መልሶ ከስሟል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በ1960ዎቹ አሜሪካ ቴክሳስ ግዛት ውስጥ ድፍድፍ ዘይትን በማግኘቷ፣ ዋጋው ርካሽ ከመሆኑም በዘለለ በገጠሩ አካባቢዎች ስለተትረፈረፈ በ1930ዎቹ ቤንዚን ተጠቃሚዎቹ እየበዙ እንደመጡ እና ኹሉም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እንደጠፉ ጥናቱ ላይ በዝርዝር ተቀምጧል።

ሆኖም ግን በ1970ዎቹ የነዳጅ ዕጥረት እያጋጠመ በመምጣቱ፣ በተለይም በ1973 የነበረው የዓረብ የነዳጅ ማዕቀብ የኤሌክትሪክ መኪናዎችን የመጠቀም ፍላጎትን ከፍ ማድረጉና በነዳጅ መትረፍረፍ ተዳክሞ የነበረው ጅማሮ በነዳጅ ዕጥረት መስፋፋት እንደጀመረ ጥናቱ ያብራራል። በ1976 የኤሌክትሪክ አውቶሞቢሎች ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩ ቢሆንም፣ ለ20 ዓመት ያህል ግን አልተስፋፉም ነበር። ይህ በእንዲህ እያለ በአሜሪካ ውስጥ በ1990 የወጣው ‹የንጹሕ አየር ሕግ ማሻሻያ› እና የ1992 ‹የኢነርጅ ፖሊሲ ሕግ› የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች እንዲስፋፉ ምክንያት መሆኑ ተመላክቷል።

በመቀጠልም፣ በ1997 በጃፓን የተመረተው በኤሌክትሪክ የሚንቀሳቀስ ተሸከርካሪ ቶዮታ ፔሬስ፣ እንዲሁም በ2010 ማብቂያ ሸቪ ቮልት (Chevy Volt) እና ኒሳን ሊአፈ (Nissan LEAF) በአሜሪካ ገበያ እየተስፋፉ መጥተዋል።

የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ፋይዳ?
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹ በትራንስፖርት ዘርፍ ከተጋረጠብን ችግር ይገላግሉን ይሆን የሚለው የብዙኀኑ ጥያቄ ነው። በዘመነ መልኩ የመጡት በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ተሸርካሪዎች፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ኹነቶች ለአገሪቱ ቀላል የማይባል አስተዋጽዖ እንደሚኖራቸው የኢኮኖሚ ምሁራን ሙያዊ አስተያታቸውን ለአዲስ ማላዳ ገልጸዋል።

ተሽከርካሪዎቹ በኢኮኖሚ ደረጃ ቀላል የማይባል ሚና ይጫወታሉ የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው ዳዊት አንተነህ ሲሆኑ፣ ሙያዊ አስተያየታቸውን በአራት ዋና ዋና መንገዶች በሚከተለው መልኩ አስረድተዋል።
ዳዊት በመጀመሪያ ደረጃ ያነሱት በኤሌክትሪክ እና በፀሐይ ብርሃን ኃይል ይሠራሉ የተባሉት ተሸከርካሪዎች አገሪቱ ከውጭ አገራት ነዳጅ ለማስመጣት የምታወጣውን ወጭ ለመቀነስ የሚረዳ መሆኑን ነው።

ሠሞኑን በተለያዩ የሚዲያ ተቋማትና በዘርፉ ምሁራን በኩል እየተገለጸ የሠነበተው የኤሌክትሪክ ኃይል ተገጥሞላቸው ከነዳጅ ወጪ ያላቅቃሉ የተባሉት መኪናዎች ናቸው።
አዲስ አበባ ውስጥ ከ3 መቶ ሺሕ በላይ የግል አውቶሞቢሎች መኖራቸውን የገለጹት የኢኮኖሚ ባለሙያው ዳዊት፣ ከፍተኛ ነዳጅን የሚጠቀሙት አውቶሞቢሎቹ በመሆናቸው አብዛኞቹን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ ከተቻለ ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ ወጪ ለመቀነስ ማስቻሉ ዕሙን እንደሆነ አብራርተዋል።

ምንም እንኳ አሁን አሁን በአዳዲስ መልክና ቅርፅ ብቅ ብቅ እያሉ ቢሆንም፣ በአገራችን ያሉት አብዛኛዎቹ አውቶሞቢሎች አሮጌ ከመሆናቸው አንጻር የመለዋወጫ ዕቃ (ስፔር ፓርት) ሲያሰፈልግ ኢትዮጵያ ምርቱን ስለማታመርት ከውጭ አገር እንደምታስመጣ ይታወቃል።
የኤሌክትሪክ ኃይል ለተሽከርካሪዎች አገልግሎት እንዲውል መደረጉ አገሪቱ በእያንዳንዱ ዓመት ለነዳጅ የምታወጣውን ከኹለት ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጭ ከመቀነ በተጨማሪ፣ ስፔር ፓርት ከውጭ አገር ለማስመጣት የሚወጣውን ውጭም ለማስቀረትም እንደሚረዳ ዳዊት ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የኢኮኖሚስት ባለሙያው በኹለተኛ ደረጃ ያነሱት ነጥብ የአካባቢ ብሎም የዓለም የአየር ብክለትን በመቀነስ ለጤንነት ያለውን አስተዋጽዕ ይመለከታል።

ከተለያዩ የኢንዱስትሪ ተቋማት፣ ከተሽከርካሪዎች፣ እንዲሁም ከመሰል ፋብሪካዎች የሚለቀቅ ካርቦንዳይ ኦክሳይድ ለአካባቢ አየር ንብረት መበከል ምክንያት ከመሆኑ ባሻገር ጤና ላይ እንከን ማምጣቱ በሳይንስ የተረጋገጠ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል።
ታዲያ በኤሌክትሪክና በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ ተሸከርካሪዎች ወደ አገራችን መምጣታቸው ለነዳጅ የሚወጣውን ዶላር ከመቀነሳቸው በተጨማሪ፣ የአካባቢ አየር ብክለትን ለመቀነስ እንደሚረዳ በበርካቶች ታምኖበታል።

በነዳጅ የሚንቀሳቀሱት ተሸርካሪዎች በኤሌክትሪክ ኃይል መንቀሳቀስ ሲጀምሩ ምንም ዓይነት የተቃጠለ ኦክስጅን ስለማይወጣ፣ የአገሪቱን ቀርቶ የመላ ዓለሙን ሕዝብ በአየር ብክለት ከሚመጣ በሽታ ለመታደግ እንደሚያስችል ዳዊት የግል አስተያታቸውን ሠጥተዋል።
አዳዲስ ፈጠራዎች ሲመጡ በቀጥታ እንዲያበረክቱት ከተፈለገው ዋነኛ ዓላማ ጎን ለጎን የሥራ ዕድልም ይዘው ስለመምጣታቸው በየወቅቱ የመጡ አዳዲስ ኢንቨስተመንቶችን፤ ድርጅቶችን እንዲሁም ሌሎች መሰል ተግባራትን መመልከት ይቻላል።

የግልም ሆኖ የመንግሥት ድርጅቶች ሲመሠረቱ ለበርካታ የማኅበረሠብ ክፍሎች የሥራ ዕድል እንደሚያበረክቱት ኹሉ፣ ተሽከርካሪዎች ከነዳጅ ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል መሸጋገራቸው ለሥራ አጦች የሥራ ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ዳዊት ከላይ ከተዘረዘሩት ኹለት ነጥቦች በተጨማሪ ጠቅሰዋል።

መኪናዎቹ በአገሪቱ ውስጥ እየተበራከቱ ሲመጡ የመኪና መገጣጠሚያ ድርጅቶችም በተመሳሳይ ይጨምራሉ የሚሉት ዳዊት፣ ይህም ዕድል በአገራችን ያሉ ቴክኒሻኖች በሥራው እንዲሳተፉ ይረዳል ሲሉ ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።
የኢኮኖ ምሁሩ አያይዘውም፣ በዚህ አጋጣሚ የመገጣጠሚያ ድርጅቶችን ለማቋቋም ‹ኢንቨስት› የመድረጉም ብዙ ዕድል ስለሚኖር ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት መሻሻልም አስተዋጽዖ ይኖረዋል ሲሉ ነው ሙያዊ ምክራቸውን ያካፈሉን።

ዳዊት በመጨረሻና በአራተኛ ደረጃ ያነሱት ነጥብ፣ በኤሌክትሪክና በፀሐይ ብርሃን የሚሠሩት መኪናዎች መምጣታቸው ከላይ ከተዘረዘሩት ጥቅሞች በተጨማሪ በአገሪቱ ያለውን የውኃ ሀብት ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት ጥቅም ላይ ለማዋል መንግሥትንም ሆነ ማኅበረሠቡን የማነቃቃት ኃይል እንደሚኖረው ነው።

አገራችን የነዳጅ ድሃ እንዳልሆነች በተለያዩ ወቅቶች በሚዲያ ተቋማት ይነገራል እንጅ ከከርሰ ምድር መውጣታቸው አልተሰማም የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፣ በተመሳሳይ አገሪቱ የውኃ ባለሃብት እንደመሆኗ መጠን ያን ያክል በዘርፉ ስላልተሠራበት የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎቹ መምጣት የውኃ ሀብታችንን ይበልጥ ጥቅም ላይ ለማዋል በር ከፋች ምክንያት ሊሆን ይችላል ሲሉ ነው ግምታቸውን የተናገሩት።


ቅጽ 4 ቁጥር 172 የካቲት 12 2014

አስተያየት

Leave a Reply to አንዳምላክ ባዴ ምላሽ ሰርዝ

Please enter your comment!
Please enter your name here