በኢትዮጵያ ከ80 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ። ሆኖም የቁጥራቸውን ያክል የርዕዮት ዓለም ልዩነት የላቸውም በማለት ይታማሉ። እንደዚያም ሆኖ በሰው ኃይል፣ በገንዘብም ይሁን በሕዝባዊ መሠረት ጠንካራ ባይሆኑም የፓርቲዎቹ ቁጥር መጨመሩን አላቆመም። በሕዝብ ግፊት ለመተባበር የሞከሩት ድርጅቶችም ኅብረታቸው ብዙ ጊዜ አይፀናም። አንድ ተለቅ ያለ ፓርቲ ሆነው የጀመሩትም ተሰነጣጥቀው ብዙ ትንንሽ ሆነው ይቋጫሉ። ለዚህ የመንግሥት አፈና አንዱ ምክንያት ቢሆንም የፓርቲዎቹ እና መሪዎቻቸው ድክመትም ሌላኛው ችግር ነው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚኖራቸው የቅቡልነት ደረጃ ፍላጎቶችን በማስታረቅና በማመቻመች ችሎታቸው፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመቀነስ አቅማቸው፣ የፖለቲካ አጀንዳ በመቅረፅና ተፈፃሚ ለማድረግ የሚያስችል ተፅዕኖ የመፍጠር አቅማቸው ላይ የተመሠረተ ነው። በተለምዶ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያራምዱት ርዕዮተ ዓለም ላይ ተመሥርተው በሚነድፉት የፖለቲካ መርሐ ግብር ላይ የሚወክሉትን የማኅበረሰብ ክፍል ፍላጎቶች ማንፀባረቅም ይጠበቅባቸዋል።
በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን በብሔር ላይ የተመሠረቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደመብዛታቸው፣ በፖለቲካ መርሐ ግብራቸው የሚፎካከሩበት ወይም የሚተባበሩበት መንገድ የለም ማለት ይቻላል። የሚያንፀባርቋቸው ፍላጎቶች በአንድ የተወሰነ ብሔር/ቡድን ውሱን ፍላጎት የተገደበና ማኅበራዊ መሠረታቸውም እንወክለዋለን የሚሉት ብሔር/ቡድን አባላት ብቻ ነው። ኅብረ ብሔራዊ የሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቢሆኑ በግልጽ ማኅበራዊ መሠረታቸውን ያልለዩና በፖለቲካ መርሐ ግብሮቻቸው ያስቀመጧቸው ፍላጎቶች ምናባዊነትን የተላበሰና በአገሪቱ ካሉ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮች የመነጩ አይደሉም እየተባሉ ይተቻሉ።
የፖለቲካ ድርጅቶቹ በሰው ኃይል አመዳደባቸው፣ አደረጃጀትና አሠራራቸው ከጥቅም ጋር የተሳሰሰረ በመሆኑ፣ በፓርቲዎች መካከል ያሉ ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው አብዛኞቹ ፓርቲዎች ማኅበራዊ መሠታቸው እየጠበበ ሔዶ በፓርቲዎች ውስጥ የሚሳተፉት የልኂቃን የግል ንብረት ሆኗል ማለት ይቻላል። ለዚህም ነው ፓርቲዎቹ የልኂቃን ናቸው የማባሉት። ማኅበራዊ መሠረታቸው የጠበበ መሆኑ ደግሞ ፈተና በገጠማቸው ወቅት ኅልውናቸውን የማስጠበቅ አቅማቸው ደካማ እንዲሆን አስገድዷቸዋል። በዚህም ሳቢያ እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች ቆመንለታል የሚሉትን ርዕዮት ወይም ሕዝብ ወክለው የመደራደር አቅማቸውን እጅግ በጣም የወረደ ሆኗል።
ማኅበረሰባዊ ፍላጎቶችን ማስታረቅና ልዩነቶችን ማቻቻል የፖለቲካ ፓርቲዎች ተግባራት አንዱ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ይህን ተግባር የመከወን ልምድ ሊዳብር አልቻለም። ይልቁንም እጅግ በጣም ጠባብ በሆኑ የፖለቲካዊ ልዩነቶች ሳቢያ ግዙፍ ብጥብጦች እና መከፋፈሎች እየተከሰቱ ነው። ይህ ጥቃቅን ችግሮችን በውይይት እና ማመቻመች ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ወደ መከፋፈል እና መለያየት መሔድ ድርጅቶቹ አገር የመምራት ዕድል ቢያገኙ ሊያስከትሉ የሚችሉትን አደጋ አስፈሪ አድርጎታል።
የሴራና የመጠፋፋት ታሪክ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ደካማ ከማድረጉም በላይ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ቅቡልነት በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳው ይገኛል። በዚህ የፖለቲካ ባሕል ሳቢያ በፖለቲካ ፓርቲዎችና መሪዎች መካከል ያለው ጊዜያዊ የመተባበር ፍላጎት እንኳን ሳይቀር በማኅበረሰቡ ውስጥ በከፍተኛ ጥርጣሬ ይታያል። ይህ ደካማ አቅም በሕዝቡ ውስጥ ዝቅተኛ ቅቡልነት እንዲኖራው ብቻ ሳይሆን ያደረገው የመደራደርና የመገዳደር አቅማቸውን ውስን እንዲሆን ጭምር ገፊ ምክንያት ሆኗል።
ፓርቲዎች በጥናት ላይ የተመሠረቱ፣ የማኅበረሰቡን ችግሮች ሊፈቱ የሚያስችሉ የጋራ አጀንዳ የመንደፍ ብሎም ውስጥ ዘልቆ በመግባት ማኅበረሰቡን በእነሱ ዙሪያ በማሰባሰብና የቅቡልነታቸውን ደረጃ ከፍ በማድረግ የመደራደርና የመገዳደር አቅማቸውን ገንብተው ከሕዝ የሚጠበቅባቸውን የፓርቲ ተክለ ሰውነት እንዲይዙ አዲስ ማለዳ ትመክራልች።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚካሔደው የፖለቲካ ለውጥ አንፃር ፓርቲዎች የመደራደር አቅማቸው ሲታይ ደካማ መሆናቸውን ያሳያል። እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ከመምራትና አማራጭ ሐሳብ ከማቅረብ ይልቅ ኢሕአዴግ ወይም መንግሥት በቀደደላቸው ቦይ ብቻ የሚፈሱ መሆናቸውን ሁሉም የሚታዘበው ጉዳይ ነው። ይህም የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማስፈን የሚደረገውን እንቅስቃሴ በጣም እንደሚጎዳው አዲስ ማለዳ ታምናለች። የተቀራረበ የመደራደር አቅም ሲኖር የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚገነቡት ዴሞክራሲያዊም ሆነ አስተዳደራዊ ተቋሞች ዙሪያ መግባባት ላይ መድረስ ከማስቻሉም በላይ፥ ሁሉም ሕዝብ በወኪሎቹ አማካይነት የሚሥማማበት ስርዓት እንዲፈጠር ያግዛል። በመሆኑም የፖለቲካ ባሕላችን እንዲዳብር እና ዴሞክራሲያዊነት እንዲያብብ የፖለቲካ ድርጅቶች መንግሥት ላይ ጣት ከመቀሰር ባሻገር ውስጣቸውን በመፈተሽ ራሳቸውን ያጠናክሩ በማለት ጋዜጣችን ምክሯን ታስተላልፋለች።
ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011