ምርጫ ቦርድ መጀመሪያ አመኔታ የሚያስገኙልኝን ሥራዎች አስቀድማለሁ አለ

0
448

የሲዳማ ክልል የመሆንን ጥያቄ ሕዝበ ውሳኔ ለማካሔድም ይሁን በመጪው ምርጫ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ መጀመሪያ አመኔታን የሚያስገኙለትን ቁልፍ ሥራዎች መሥራት እንዳለበት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ።

የሲዳማ ዞን ሕዝብ የክልል እንሁን ጥያቄ በክልሉ ምክር ቤት ተቀባይነት ማግኘቱን ተከትሎ የሕዝበ ውሳኔው ቀን ቶሎ እንዲቆረጥላቸውና እንዲካሔድ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ ከዞኑ 36 ወረዳዎች በተውጣጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች የካቲት 14 በሐዋሳ መደረጉ ይታወሳል።

የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ እንዳሉት አሁን ላይ የምርጫ ቦርድን አወቃቀር ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ እያደረገ ነው። ስለሆነም የተጀመሩት የማሻሻያ ሒደቶች ማለቅና በተወካዮች ምክር ቤት መፅደቅ እንዳለባቸው የገለፁት ብርቱካን ቦርዱ ከየትኛውም ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው ለማሻሻያ ሥራዎቹ መሆኑን አሳውቀዋል። ምክንያቱ ደግሞ መጀመሪያ የአቅም ግንባታና የሕግ ጉዳዮችን ማስተካከል ስለሚያስፈልግ መሆኑን በመጥቀስ ከሁሉም በላይ “የሕዝብ አመኔታን ለማግኘት የሚያስችሉ ቁልፍ ሥራዎች መከናወን ይገባቸዋል” ሲሉ ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል። ከዚያ በኋላ የሲዳማ ጥያቄንም ሆነ የአገር ዐቀፍና አካባቢያዊ ምርጫዎችን ጉዳይ እንደሚመለከት አክለዋል።

በጥር 25 የአዲስ ማለዳ 12ኛ ዕትም እንግዳ የነበሩት ብርቱካን ሚዴቅሳ የማሻሻያ ሥራዎቹ ለሁሉም የቦርዱ ተግባራት ወሳኝ ስለመሆናቸው ሲያስረዱ “ተቋሙ ሙሉ ብቃትና ተዓማኒነት እንዲኖረው ተደርጎ መዘጋጀት አለበት” ብለው ነበር።

የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ የተቀበለው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት የሕዝበ ውሳኔው ሒደት በሕግ አግባብ እንዲፈፀምለት ኅዳር 12/2011 በፃፈው ደብዳቤ ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ ማቅረቡን አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም መዘገቧ ይታወሳል። ጥያቄው መቅረቡን ያረጋገጡት ብርቱካን ወደ ሕዝበ ውሳኔው ጉዳይ ከመግባቱ በፊት ቦርዱ የጀመራቸውን ማሻሻያዎች አጠቃሎ በተወካዮች ምክር ቤት ለማፀደቅ ሒደት ላይ መሆኑን ለክልሉ ተወካዮች እንዳስረዳም ገልፀዋል።

በሐዋሳ ስለተካሔደው ሰላማዊ ሰልፍና የሕዝቡን ፍላጎት እየተከታተለበት ስላለው አግባብ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ክፍል አዲስ ማለዳ መረጃን በስልክ የጠየቀች ሲሆን ምክር ቤቱ ጥያቄውን ባለው ሕጋዊ አሰራርና መዋቅር መሰረት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔው እንዲካሔድ ያደርግ ዘንድ ጥያቄ ማቅረቡንና “ምክር ቤቱም የሚጠበቅበትን መወጣቱን” ገልጿል።

ደብዳቤውን ከማስገባት ባለፈ ምክር ቤቱ ከምርጫ ቦርድ ጋር እየመከረበትና ተናቦ እየሠራበት መሆኑንም አሳውቋል። በሰላማዊ መንገድ የቀረበው የሕዝቡ ጥያቄ ግን ተገቢ ነው ያለው ምክር ቤቱ በቀጣይ ምርጫ ቦርድ በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሠረት ተባብሮ እንደሚሠራም አክሏል።

ምክር ቤቱ በጥቅምት 23/2011 ጉባኤው የሲዳማ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄ ሕገ መንግሥታዊ ሒደቱን ተከትሎ እንዲፈጸም መወሰኑ ይታወሳል።
በሐሙሱ ሰልፍም “የሲዳማ የክልል እንሁን ጥያቄ ሕገ መንግስታዊ ነው”፣ “ያለምልንም ደም ሪፍረንደም”፣ “ላቀረብነው የክልልነት ጥያቄ ሪፈረንደሙ በአስቸኳይ ይካሔድ” የሚሉና ሌሎች መፈክሮች ወጥተዋል።

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47 የክልል ምስረታ ጥያቄ እውን ስለሚሆንበት የሕግ አግባብ ሲያስረዳ የብሔር፣ ብሔረሰቡ ወይም ሕዝቡ ምክር ቤት ጥያቄውን በኹለት ሦስተኛ ድምጽ ሊቀበለውና ጥያቄው በጽሑፍ ለክልሉ ምክር ቤት ሊቀርብ እንደሚገባ ያስገነዝባል። የሲዳማ ጥያቄም በዚሁ አግባብ መሔዱ ይታወሳል።
አንቀጽ 47 (ለ እና ሐ) “ጥያቄው የቀረበለት የክልል ምክር ቤት ጥያቄው በደረሰው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለጠየቀው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ፣ ሕዝበ ውሳኔ ሲያደራጅ፤ ክልል የመመስረት ጥያቄው በብሔሩ፣ ብሔረሰቡ ወይም ሕዝቡ ሕዝበ ውሳኔ በአብላጫ ድምጽ ሲደገፍ” ክልል እንደሚመሰረት ያትታሉ።
የደቡብ ክልል ምክር ቤቱም ይህንኑ መነሻ አድርጎ ሕዝበ ውሳኔው እንዲከናወንለት መወሰኑን ለምርጫ ቦርድ በፃፈው የኅዳር 12ቱ ደብዳቤ አመልክቷል። ሕዝበ ውሳኔው እንዲካሔድ የሚጠይቀው ደብዳቤ ለምርጫ ቦርድ ከተፃፈም ባሳለፍነው ማክሰኞ፣ የካቲት 12 ሦስት ወር ሞልቶታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here