850 አውቶቡሶችን ለሚያስተናግደው የየካ ዴፖ ተቋራጮች እየተመረጡ ነው

0
419

ከ850 በላይ አውቶቡሶችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ እንዲያስችል በ10 ሄክታር መሬት ላይ ለሚገነባው የየካ አውቶቡስ ዴፖ ከ10 በላይ ተቋራጮች በቅድመ ጨረታ መረጣ ላይ መሆናቸውን የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ገለፀ።

የግንባታ ሥራው ኹለት ዓመት እንደሚፈጅ የታቀደውን ዴፖ ግንባታ ለማስጀመር የመጀመሪያው ምዕራፍ ጨረታ አልቆ ለውድድር የቀረቡ ከ10 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ግንባታ ተቋራጮች ባላቸው አቅም መሰረት ለቀጣይ ዙር ጨረታ እየተመረጡ መሆኑን የጽሕፈት ቤቱ የእግረኛና የብዙኃን ትራንስፖርት ሥራ ክፍል ኃላፊ ናትናኤል ጫላ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የመጀመሪያውን ዙር ግምገማ የሚያልፉት ተቋራጮችም በሚያቀርቡት የግንባታ ወጪ ገንዘብና ሌሎች ቴክኒካዊ ሰነዶች ተወዳድረው ገንቢው ተቋራጭ እንደሚመረጥ አስረድተዋል። የጨረታ ሒደቱ በታሰበው ልክ ከሔደ ግንባታውን በመጪው ግንቦት ለመጀመርም ታቅዷል።
ገርጂ መብራት ኃይል አካባቢ በሚገኘው የአንበሳ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት ግቢ ይገነባል ለተባለው ዘመናዊ የአውቶቡስ ዴፖ ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ ከሚገኙት የቃሊቲና ሸጎሌ ዴፖዎች ድምር አገልግሎት በእጥፍ በሚልቅ አኳኋን እንደሚገነባ ነው የተነገረለት።

የሸጎሌና አቃቂ ዴፖዎች እያንዳንዳቸው ከ250 እስከ 300 አውቶቡሶችን መያዝ አቅም ሲኖራቸው የየካው ግን ከ850 በላይ አውቶቡሶችን መያዝ የሚችል በመሆኑ በብዙኃን ትራንስፖርቱ ዘርፍ ላይ የሚኖረው አዎንታዊ አስተዋፅኦ ይጎላል ተብሎለታል። ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ ያሉት የአቃቂና ሸጎሌ ዴፓዎች በአንፃሩ በአንድ ጊዜ ስድስት አውቶቡሶችን ማስተናገድ የሚችል የነዳጅ ማደያ ያላቸው ሲሆን የየካው 12 አውቶቡሶችን ማስተናገድ ያስችላል ተብሏል። በአንዴ 50 አውቶቡሶችን መጠገን የሚያስችል ማዕከልም እንደሚኖረው ተነግሯል። በምስለ መንጃ (driving simulator) የሚታገዝ የአውቶቡስ አሽከርካሪዎች መለማመጃና ማሰልጠኛ ክፍል ይኖረዋልም ተብሏል።

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ የአዲሱ ዴፖ ንድፍ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ ሲሆን በዚህም መሠረት በሦስት ሺሕ 500 ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፍ ባለኹለት ክንፍና ባለ ዘጠኝ ወለል የአስተዳደር ሕንፃ ይኖረዋል። ኹለቱ ወለሎች ከመሬት በታች የሚገኙ ሲሆን 120 የቤት መኪኖችን ማቆም ያስችላሉ።

ከአስተዳር ሕንፃዎቹ አንዱ ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲከራይ ሆኖ ለዴፖው የገቢ ማስገኛ በመሆን እንደሚያገለግልም ተገልጿል።

ከአካባቢ ጥበቃ አንጻር ከአወቶቡሶቹ እጥበት የሚወጣውን ውሃ በድጋሚ አጣርቶ የሚያቀርብ የቆሻሻ ውሃ ማጣሪያ ማሽን ሲኖረው፤ ከዴፖው የሚወጣውን ፍሳሽ አጣርቶ ዝቃጩን የሚስቀርና የቀረውን ውሃ በአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በተቀመጠው ደረጃ መሠረት ወደ ከተማዋ የፍሳሽ መስመር የሚለቀቅ ይሆናል።
የዴፖው ዝርዝር የንድፍ ጥናት ‘ሲስትራ ሳ’ በተሰኘ የፈረንሳይ ኩባንያ የተሰራ ሲሆን በአካባቢ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ በተመለከተ ነጋሽ ታምሩ ዘውዴ እና ‘እንሲራድ’ ሲቪል ኢንጂነሪንግ ሶልሽንስ የተሰኙ ድርጅቶች ጥናት እንደሚያደርጉ ታውቋል።

የሸጎሌና አቃቂ ዴፖዎች የግንባታ ኮንትራት በአውሮፓዊያኑ 2016 ሲፈረም ለግንባታ ብቻ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር እንደወጣባቸው ናትናኤል ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here