ብርቱካን ገበያ ላይ እስከ 75 ብር እየተሸጠ ነው

0
1062

• ኢትዮጵያ በዓመት 1 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ የብርቱካን ምርት ወደ ውጪ ትልካለች

በአዲስ አበባ የብርቱካን ዋጋ በከፍተኛ ሁኔት የዋጋ ጭማሪ በማሳየት የአንድ ኪሎ ብርቱካን ዋጋ ሰባ አምስት ብር መግባቱ ታወቀ።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በፒያሳ የሚገኙ አትክልትና ፍራፍሬ ቤት ነጋዴዎች እንደተናገሩት ብርቱካን ከሚመረትባቸው ቦታዎች በምንፈልገው መጠን እያገኘን አይደለም ሲሉ ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት ባሳለፍናቸው ሳምንታት ውስጥ የኻያ አምስት ብር ዋጋ ጭማሪ አድርገን አንድ ኪሎ ብርቱካን በሰባ አምስት ብር እየሸጥን ነው። አሁን ከተከሰተው ከፍተኛ እጥረት አንፃር ምንም ዓይነት የዋጋ መቀነስ አይኖርም። ይሁንና በሚመጡት ኹለት ሳምንታት ውስጥ ይህ እጥረት በትንሹም ቢሆን ካልቀነሰ የአንድ ኪሎ ብርቱካን ዋጋ የ25 ብር ጭማሪ በማድረግ 100 ብር እንደሚገባ ነጋዴዎቹ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

ብርቱካኖቹን በአብዛኛው የምናመጣው ከአዋሽ ፣ ከሸዋሮ ቤት መርሳ አማራ ክልል እንዲሁም ከሀረር ክልል እንደሆነ የገለጹት ነጋዴዎቹ፤ ከአዋሽ የሚመጣው ብርቱካን ባሌንሺያ የሚባለው ብርቱካን ሲሆን በሀረር መስመር የሚመጣው እጅግ በጣም ጣፋጭ የሆነው ኤሬር የሚባለው እና በብዙዎች ዘንድ ተፈላጊ የሆነው የብርቱካን ዓይነት ነው። ይሁንና ከሁሉም አገሮች የምናመጣቸው ብርቱካኖች የሚመጡበት ዋጋ ከ50 እስከ 55 ብር ሲሆን ሁሉም የብርቱካን ዓይነቶች የሚሸጡትም በተመሳሳይ ዋጋ ነው ብለዋል።

ለብርቱካን ምርት እጥረት ነጋዴዎቹ እንደ ምክንያት የጠቀሱት ብርቱካኖቹ በእርሻ ላይ እንዳሉ በተባይ ስለተጠቁ መሆኑን ጠቅሰዋል። አዲስ ማለዳ በግብርና ሚስቴርና የአትክልት፣ ፍራፍሬና አበባ ልማት እና ቴክኖሎጂ ትራንስፈር ዳይሬክትር አብደላ ነጋሽ ስለጉዳዩ ለተጠየቁት ሲመልሱ ውሱን የምርት ዝርያ መኖር፣ በሽታና የተባይ ማጥቃት እና የዘር እጥረት በምክንያትነት ገልጸዋል።

ብርቱካን እጥረትን አስመልክቶ አንድ ኪሎ ብርቱካን በ75 ብር እየገዙ አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው መካከል ሰብለ ማሞ “ብርቱካን ለብዙ ነገር ስለሚያስፈልገኝ አብዛኛውን ጊዜ እጠቀማለው፤ ነገር ግን አሁን ካለው የዋጋ ጭምሪ አንፃር ብርቱካን የምገዛው እና የምጠቀመው አልፎ አልፎ ነው” በማለት የዋጋው መናር ያሳደረውን ተጽዕኖ ገልጸዋል።

የግሎባል አግሪካልቸራል ኢንፎርሜሽን ኔትወርክ እና የኢትዮጵያ ገቢዎችና ግምሩክ ባለሥልጣን መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ በ2017/18 (እ.ኤ.አ) 3 ሺሕ ሄክታር መሬት በማልማት 21 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ብርቱካን ማምረት የቻለች ሲሆን፤ በአራት መቶ ሄክታር መሬት ላይ 31 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በአጠቃላይ ማምረት ችላለች። ከውጪ የገባው የብርቱካን መጠን በ2017/18 የዘጠኝ ወር መረጃ እንደሚሳየው አርባ ስምንት ሜትሪክ ቶን ሲሆን ለዚህም ሰባ ሰባት ሺሕ የአሜሪካ ዶላር ወጪ አድርጋለች። ይህም በአንፃሩ በ2017/18 ካስገባችው አጠቃላይ ዓመታዊ ሰባ ስምንት ሜትሪክ ቶን እና አንድ መቶ ዐሥራ አምስት የአሜሪካ ዶላር ጋር ሲነፃፀር ጭማሪ ይታይበታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here