“ወተት በየቤቱ እያዞርኩ ሸጬ ነው ቤቴን የገነባሁት” “በከተማው አረንጓዴ ስፍራዎች ላይ በሕገ ወጥ መንገድ ቤቶች ተገንብተዋል”
ቤታቸው የፈረሰባቸው የለገጣፎ ነዋሪ የለገጣፎ ከተማ አስተዳደር ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ
በኦሮሚያ ክልል ለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር በሕገ ወጥ መንገድ ተገንብተዋል ተብለው በከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ እንዲፈርሱ በተደረጉ መኖሪያ ቤቶች ምክንያት ለዘመናት ግብር እየከፈልን እና እያለማን ከኖርንበት አካባቢ በግፍ እንድንፈናቀል ተደርገናል ሲሉ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። ነዋሪዎች እንደገለፁት በአካባቢው በኖሩባቸው ዓመታት መንገድ፣ ውሃ ፣ መብራት ወደ አካባቢው እንዲገባ በማድረግ አካባቢውን እንዳለሙ ተናግረው፤ መሰረተ ልማቶችን በሚገነቡበት ወቅት ሙሉ ወጪውን መሸፈናቸውንም ጨምረው አስታውቀዋል።
በከተማ አስተዳደሩ 01 ቀበሌ ልዩ ስሙ አባ ኪሮስ በሚባል ስፍራ ሕገ ወጥ ነው ተብሎ መኖሪያ ቤታቸው የፈረሰባቸው በሰልፍ ካሳየ ቅሬታቸውን በእንባና ሳግ በታጀበ አንደበት “ለ13 ዓመታት የኖርኩበት፣ ልጆቼን ያሳደኩበት እና ሀብት ንብረቴን ያፈሰስኩበት በእርጅና ዘመኔ የምጦርበትን ቤቴን ተነጠኩ” ሲሉ አማረዋል። በሰልፍ መኖሪያቸው ከፈረሰባቸው ሰዎች ውስጥ ከስምንት ዓመታት በታች የኖረ እንደሌለ እና የይዞታ ግብርም ለመንግሥት ይከፍሉ እንደነበር አክለዋል። ይሁን እንጂ አስተዳደሩ ግምት ተከፍሎበታል በሚል እንዳፈረሰባቸው ተናግረው ቤቱን የሸጡላቸው ሰዎች ግን ምንም ዓይነት ግምት እንዳልተቀበሉ እየመሰከሩላቸው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
በሰልፍ ከሳየ 220 ካሬ ሜትር የሚሆነው ይዞታቸው መፍረሱንና ብዙም ሳይርቅ የአምስት ልጆች እናት የሆችው ልጃቸው የምትኖርበት 300 ካሬ ሜትር ቤትም በተመሳሳይ ሁኔታ መፍረሱን ይናገራሉ። አሁን ላይ ቀድሞ ይኖሩበት በነበረው ቤትና ወደ ፍርስራሽ በተቀየረው ቦታ ላይ ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ እየኖሩ እንዳለና ልጆችም ትምህርት ካቋረጡ ቀናት መቆጠሩን አዲስ ማለዳ በቦታው በመገኘት ለመታዘብ ችላለች።
የለገጣፎን እና የለገዳዲን ወንዝ ተከትለው በተገነቡ ቤቶች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ በተወሰደ ጊዜ መኖሪያቸው የፈረሰባቸው ግለሰብ ሰለሞን ይግዛው ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት “ወተት በየቤቱ እያዞርኩ ሸጬ ነው ቤቴን የገነባሁት” ይላሉ። አያይዘውም ከ2005 ጀምሮ እንደኖሩና የሚጠበቅባቸውን ግዴታም ለመንግሥት ይከፍሉ እንደነበር ተናግረው ፤ አሁን ላይ የሚጠጉበት በማጣታቸው ንብረታቸውን እንደያዙ ሜዳ ላይ ለማደር መገደዳቸውን አስታውቀዋል። በተያያዘም የከተማ አስተዳደሩ ለዋና መንገድ በቀረቡ ቤቶች ላይ ጥናት በማድረግ ሕጋዊ አይደሉም በሚላቸው ቤቶች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የተገኘው መረጃ የሚያመለክት ሲሆን፤ አንዳንድ የከተማው ነዋሪዎችም በዚህ ላይ ስጋት እንዳለባቸውና ሕጋዊ ቢሆኑም መኖሪያቸው ላለመፍረሱ እርግጠኞች እንዳልሆኑ ይናገራሉ።
በከተማ አስተዳደሩ ሕግ መሰረት ከወንዝ ዳርቻዎች ከ50 ሜትር ባነሰ ርቀት ውስጥ መኖሪያ መገንባት እንደሚከለክልና በከተማው አረንጓዴ ስፍራዎች ላይ በሕገ ወጥ መንገድ ተገንብተዋል በሚል ቤቶች ስለማፍረሱ የከተማው አስተዳደር ሕዝብ ግንኙነት ለአዲስ ማለዳ ማብራሪያ ሲሰጥ፤ ከዚህ በፊት የነበረው አስተዳደር ከሕግ ውጭ የመኖሪያ መሥሪያ ቦታዎችን ለነዋሪዎች ይሰጥ እንደነበርና ከፕላን ውጭም እንደነበር አስረድቷል። ከተማ አስተዳደሩ ጨምሮ እንደገለጸው ከዓመታት በፊት ካሳ ተከፍሎባቸው ወደ መሬት ባንክ በገቡ መሬቶች ላይ ግንባታ በመፈፀማቸው እንዲፈርሱ ሆኗል ሲል ይገልፃል። መጀመሪያ አስተዳደሩ ነዋሪዎችን ሰብስቦ እንዳወያየና እቃቸውንም አውጥተው እንዲያፈርሱ የጊዜ ገደብ እንደሰጣቸው ገልጿል። አያይዞም ይዞታቸው ከከተማው መመስረት በፊት የሆኑና ለ30 እና 40 ዓመታት በስፍራው የኖሩ 85 የሚሆኑ አርሶ አደሮችን በመለየት 500 ካሬ ሜትር እንደሚሰጣቸው የተገለፀ ሲሆን ከጥር ወር 2005 በፊት ተገንብተው ከከተማው ፕላን ጋር የሚጣጣሙ ቤቶች ደግሞ ሕጋዊ የሚሆኑበት አሠራር እንደሚኖር የከተማው አስተዳደር ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ነፃነት ከበደ ገልፀዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ሕገ ወጥ ናቸው በተባሉት መኖሪያዎች ላይ በተደረገ የማፍረስ ሒደት የሰው ሕይወት መጥፋቱን እና ግለሰቦች የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ምንጮች የተናገሩ ሲሆን የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያም በአንድ የአፍራሽ ግብረኃይል አባል በሥራ ላይ እያለ ግድግዳ ወድቆበት ሕይወቱ እንዳለፈ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጧል።
በከተማ አስተዳደሩ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በተባበሩት መንግሥታት የ‘አዲኩዌት ሐውሲንግ’ ዘጋቢ ሊሊያና ፋራህ በትዊተር ገፃቸው ቤቶችን በማፍረስ ላይ ላሉ አካላት ሰዎችን በኃይል ማፈናቀል ቤት የማግኘት መብትን የሚፃረር እንደሆነ ሊረዱት ይገባል ሲሉ አስነብበዋል።
በለገጣፎ ከተማ ቤት ማፍረሱ ማክሰኞ፣ የካቲት 12 የተጀመረ ሲሆን የከተማው ከንቲባ የሆኑት ሃቢባ ሲራጅ ከ10 ሺሕ በላይ የሚቆጠሩ ቤቶች ፈርሰው የሕዝብ መናፈሻ ይሆናሉ ማለታቸው መገናኛ ብዙሃን በሰፊው ዘግበዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011