የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከሰጣቸው ከ40 ቢሊየን ብር በላይ የሚቆጠሩ ብድሮች ውስጥ አንድ ሦስተኛው በላይ ተመላሽ እንዳልሆነ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገለፁ።
ከባንኩ የተበላሹ ብድሮች መጨመር ጋር ተያይዞ ያልተመለሰ ብድር ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው 15 በመቶ ገደብ በመራቅ 39 ነጥብ 3 በመቶ እንደደረሰ የድርጅቱ ስትራቴጂካዊ ለውጥ እና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት ክፍሌ ኃይለየሱስ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
እስከ ባለፈው በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ 39 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ያበደረው ልማት ባንክ ወደ 6 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ብድር በሰፋፊ እርሻዎች ለተሰማሩ ግለሠቦችና ድርጅቶች ቢሰጥም እንዳልተመለሰ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል። ብድሩ ሊመለስ የማይችልበት ደረጃ መድረሱንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ የሆኑት ይናገር ደሴ ሰኞ፣ የካቲት 11 ለጋዜጠኞች ጥያቄ መልስ በሰጡበት ወቅተ ተናግረዋል።
“እንዴት እንደማይመለስ ተጠንቶ የተሰጡ ብድሮች ነው ያሉት” ይናገር፤ “የተሰጠበት መንገድ በተደራጀና በተቀነባረ መንገድ ነው” ብለዋል።
በተጨማሪም ባንኩ ከገባበት ቀውስ ይወጣ ዘንድ ለኹለት ዓመታት እስከ 2009 ድረስ ለሰፋፊ እርሻ አልሚዎች የተሰጡ ብድሮች ጨምሮ በጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ በተሰጠ አቅጣጫ ጥናት እየተደረገ መሆኑን ተገልፃል። ይህም የግለሠቦች መጠቀሚያ የሆነው የሕዝብ ሀብት ለማስመለስ ለሚደረገው ጥረት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተገልጿል።
በተለይም ባንኩ ለሰፋፊ እርሻዎች የሰጣቸው ብድሮች ለሥራ ማስኬጃ እንደመዋላቸው መጠን ተመላሽነቱን አጠራጣሪ እንደሚያደርገው ምንጮች ገልፀዋል። ከ57 በመቶ በላይ የተቋሙን ብድር የወሰዱት የጨርቃ ጨርቅ አምራቾች ላይ ተመሳሳይ ችግር እንዳለ ማወቅ ተችሏል።
ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ ብድር ወስደው የጠፉት ኤልሲ ጨርቃ ጨርቅ እንዲሁም ኹለት ቢሊየን ብር ብድር ወስደው ባለመከፈሉ የተወረሰው የአይካ አዲስ ፋብሪካ ለአብነት ማንሳት ይቻላል። ከተመሰረተ 100 ዓመት በላይ የሆነው ልማት ባንክ ብድር የማስመለስ ችግር ቢኖርብትም ትርፋማ ነው።
ባለፈው በጀት ዓመት ትርፉ ወደ 367 ሚሊየን ብር ሲደርስ ወደ 66 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማስገባት ችሎ ነበር። ይሁን እንጂ ባለፈው በጀት ዓመት መጨረሻ የባንኩ የተበላሹ ብድሮች ወደ 40 በመቶ ደርሶ ነበር። ቁጥሩም በአሳሳቢ ደረጃ መጨመሩን ተከትሎ ባንኩ የተወረሱ ንብረቶችን ለማስተዳደር በ10 ሚሊየን ብር አዲስ ድርጅት ማቋቋሙ አይዘነጋም።
ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011