መንግስት በያዝነው በጀት ዓመት በቀጣይ ወራት ውስጥ ገንብቶ ሊያጠናቅቃቸው የታሰቡት በአማራ እና ሶማሌ ክልል የሚገኙት የአይሻ እና የአረርቲ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በበጀት እጥረትና በመሰረተ ልማት መጓደል ጋር በተያያዘ መቋረጡን ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገለፁ።
በ50 ሄክታር ላይ ያረፈው የአይሻ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲቋረጥ የተወሰነው በአካባቢው ባለው ከፍተኛ የውሃ እጥረትና ይህንንም ለማድረግ ከፍተኛ ገንዘብ ስለሚጠይቅ መንግስት በክልሉ ሌላ ቦታ ሊቀይር እንደሆነ ማወቅ ተችሏል።
በሌላ በኩል በአማራ ክልል የሚገኘው የአረርቲ ኢንዱስትሪ ፓርክ በተመሳሳይ 50 ሄክታር ላይ ያረፈ ሲሆን በበጀት እጥረት ምክንያት ሊጀመር የነበረው ግንባታ ለጊዜው መቋረጡን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የልማት ክፍል የሚሰሩ ምንጮቻችን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ፤ ግንባታውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማስጀመር ዕቅድ መያዙን ምንጮች ገልፀዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ዳይሬክተር ሌሊሴ ነሜ በህዳር ወር ለሚዲያ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፥ ከሶስት ወር በኋላ ወደ ስራ ይገባሉ ተብለው ከሚጠበቁት የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል አረርቲ ይገኝበታል።
በተጨማሪም፤ በያዝነው በጀት ዓመት ይገነባሉ ተብለው ከታቀዱት አራት ኢንዱስትሪያል ፓርኮች መካከል ከ ድሬዳዋ፣ ቦሌ ለሚ፣ ባህር ዳር፣ ጂማ እና ደብረ ብርሃን ይገኙበታል።
እስከ 2012 በአጠቃላይ 30 የኢንዱስትሪ ፓርኮች በኢትዮጵያ እንደሚኖሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ አርከበ ዕቁባይ (ዶ/ር) በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያ ምዕራፍ መጠናቀቁን ተከትሎ በተደረገ የምረቃ ስነ ስርዓት መጠቆማቸው ይታወሳል።
ይህም የኢንዱስትሪ ልማትና የኤክስፖርትን እድገት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው አብራርተው ነበር። በተጨማሪም፤ ኢትዮጵያን በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ በሚደረገው ጥረት ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ገልፀው ነበር።
ከአዲስ አበባ በ113 ኪ.ሜ ርቀት በምትገኘው ደብረብርሃን ከተማ እና በተመሳሳይ ከአዲስ አበባ በ320 ኪ.ሜ ርቀት በምትገኘው በባህር ዳር ከተማ የተገነቡት ኹለት የኢንዱትሪ ፓርኮች በቀጣይ ኹለት ወራት ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል። ለግንባታው በአጠቃላይ ከኹለት ቢልዮን ዶላር ወጪ ፈሰስ የተደረገ ሲሆን ወጪ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግስት ወጪ ተደርጓል፡፡
በኢንዱስትሪ ፓርኩም ወደ ስራ ሲገባ ከሰባት ሺ በላይ የስራ ዕድል እንደሚፈጥር የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ኮርፖሬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ጥላሁን ገመቹ ተናግረዋል፡፡
ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011