በብጥብጥ የተነሳ ብድራቸውን መክፈል ያልቻሉ ባለሀብቶች የመክፈያ ጊዜ እንዲራዘምላቸው መመሪያ ተሰጠ

0
626

ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገሪቷ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ ሥራቸው በመስተጓጎሉ የተነሳ ብድራቸውን በአግባቡ መክፈል ያልቻሉ ባለሀብቶች የመክፈያ ጊዜያቸው እንዲራዘም ለንግድ ባንኮች መመሪያ መተላለፉን የብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

ባለፈው ረቡዕ የካቲት 13 የብሔራዊ ባንክ ገዥ የሆኑት ይናገር ደሴ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንዳስታወቁት፤ በአገሪቷ የነበረው አለመረጋጋት የንግድና እንቅስቃሴ ምርት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደሩ ባንኩ ይህንን ለማድረግ መገደዱን አሰታውቀዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ የሚገኙ የንግድ ባንኮች ከ292 ቢሊየን ብር በላይ ብድር ለተለያዩ ዘርፍ ላይ ለሚገኙ ባለሀብቶች ሲያቀርቡ ከ271 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ሰብሰበዋል።

በያዝነው በጅት ዓመት ጨምሮ በባለፉት ዓመታት በአገሪቷ የነበረው አለመረጋጋት የባንኮች እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ቢኖረውም የሁሉም ንግድ ባንኮች የተባለሹ ብድሮች በአማካይ ከአምስት በመቶ በላይ ሆኖ ተመዝገቧል።

ይሁን እንጂ በነበረው አለመረጋጋት የተነሳ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የአገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች ንብረት መውደሙ አይዘነጋም። በተመሳሳይ የተለያዩ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች የሚያካሔዱት ንግድ እንደተስተጓጎለባቸው ይታወሳል።

በአገሪቷ በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተነሳ በሆቴል ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች በሦስት ወራት ብቻ ከ300 ሚሊየን ብር በላይ በማኅበራቸው በኩል እንዳጡ መግለፃቸው አይዘነጋም።

ብድር እንዲራዘም ከሰጠው መመሪያ ባሻገር በፋይናንስ ዘርፍ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት የባንኪንግ፣ ኢንሹራንስ እና ማይክሮ ፋይናንስ አዋጆቾን የማስተካከል እርምጃዎች መውሰድ መጀመሩንም ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ሐሙስ መግለጫ በሰጠበት ወቅት አሳውቋል።

ከሚደረጉ ማሻሻዮች መካከል በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆኑ የውጭ ዜጎች በአገሪቷ የፋይናንስ ዘርፍ ላይ እንዲሳተፉ ማድረግን እንደሚጨምር ባንኩ ገልጿል። ከዚህ ባሻገር የፋይናንስ ዘርፉ ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት እንዴት መመራት እንዳለበት የሚያትት ፍኖተ ካርታ ብሔራዊ ባንክ እያዘጋጀ መሆኑ ታውቋል።

በተጨማሪ በተንቀሳቃሽ ንብረቶች ባንኮች ብድር መስጠት እንዲችሉ ባንኩ ረቂቅ ሕግ እያዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል። ሕጉ ፀድቆ ተግባራዊ ከሆነ ድህነትን ለመቀነስ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሏል።

በሌላ በኩል በአገሪቷ የካፒታል ገበያ ለማስጀመር ጥናት መጀመሩን የባንኩ ገዥ ይናገር በመግለጫቸው ወቅት ተናግረዋል። በተጨማሪም መንግሥት ለቻይና በየዓመቱ በአጭር ጊዜ መክፈል የሚጠበቅበት ብድር በመራዘሙና የሚከፈለው ወለድ በመቀነሱ የኢትዮጵያ መንግሥት መክፈል ያለበት ዕዳን በእጥፍ እንደቀነሰው የብሔራዊ ባንክ አስታወቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 15 የካቲት 16 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here